መካከለኛዉ ምሥራቅ እንዴት ሰነበተ?

0
118

ከ15 ወራት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሃማስ ታጣቂዎች እስራኤልን ከጋዛ የሚያዋስናትን አጥር ጥሰው በመግባት እስራኤላዊያን ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ አስከፊው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ተቀስቅሷል:: በጦርነቱም የእስራኤል ጦር በጋዛ የአየር እና የምድር ዘመቻ በመክፈት ከ47 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ሲገደሉ ከእስራኤል በኩል ደግሞ  ከአንድ ሺህ ሰባት መቶ በላይ እስራኤላዊያን ሕይዎታቸው አልፏል::

አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው የእስራኤል እና የሃማስ ተደራዳሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው አያውቁም። ሆኖም በኳታር፣ በግብፅ እና በአሜሪካ  በኩል የተኩስ አቁም ንግግር እንዲያደርጉ ለበርካታ ጊዜ ሲሞከር ቆይቷል:: ከሰሞኑ ግን ሁለቱም የተኩስ አቁም ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል:: ይህን ተከትሎም ሰላም የጠማቸው ፍልስጤማውያን ወደ አደባባይ በመውጣት የደስታ እንባ አንብተዋል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ በሦስት ምዕራፍ የሚተገበር ሲሆን በመጀመሪያው ምዕራፍ በሃማስ የታገቱ ሴቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶችን ጨምሮ 33 ታጋቾች ይለቀቃሉ። እስራኤል በምላሹ ፍልስጤማዊያን እስረኞችን ትለቃለች ተብሏል። የእስራኤል ጦር ከምሥራቃዊ የጋዛ ክፍል እንደሚወጣ እና የተፈናቀሉ ፍልስጤማዊያንም ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ የሚደረገውም በዚህ ምዕራፍ ነው:: በየዕለቱም በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገቡም ያስገድዳል።

በሁለተኛዉ ስምምነት የሚተገበረው   የመጀመሪያዉ ዙር 16 ቀን ሲሞላው ሲሆን በዚህ ዙር ተጨማሪ ታጋቾች ይለቀቃሉ:: ዘላቂ መረጋጋትን ለማምጣት የታለመለት ይህ ስምምነት የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ለቆ እንዲወጣ ያደርጋል።

ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ ጋዛን መልሶ መገንባት ላይ ያለመ ሲሆን ይህም ዓመታት እንደሚወስድ ይገመታል። በዚህ ምዕራፍ የታጋቾች አስክሬንም ይመለሳል ተብሏል።

ይሁንና የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲሳካ ሚና እንደነበራቸው የገለጹት አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሦስቱም ምዕራፎች ተግባራዊ ይሆናሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው አሳውቀዋል:: የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው እስራኤል የሁለተኛው ምዕራፍ ድርድሮች ውጤት አልባ ናቸው ወደሚል መደምደሚያ ላይ ከደረሰች ወደ ጦርነቱ ለመመለስ የአሜሪካ ድጋፍ እንዳላት መናገራቸውን  ቢቢሲ ዘግቧል::

አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው የእስራኤል ሙሉ ካቢኔ የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት እና በደርዘን የሚቆጠሩ ታጋቾችን ለመልቀቅ የወሰነው  ከስድስት ሰዓታት በላይ ስብሰባ ተቀምጦ ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ጋዛን ማን እንደሚያስተዳድር ምንም የታወቀ ነገር የለም:: ነገር ግን የፕሬዚዳንት ማሕሙድ አባስ ጽህፈት ቤት የፍልስጤም የአስተዳደር እና የደኅንነት ኤጀንሲዎች    በጋዛ ውስጥ ወሳኝ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ተናግረዋል::

እስራኤል በበኩሏ ከሃማስ ወይም ከምዕራቡ ዓለም ከሚደገፈው የፍልስጤም አስተዳደር ጋር ግንኙነት ከሌላቸው ከአካባቢው ፍልስጤማውያን ጋር እንደምትሠራ አስታውቃለች። ይሁንና እንደዚህ አይነት አጋሮች መኖራቸው ግልጽ ባይሆንም  ሃማስ ከእስራኤል ኃይሎች ጋር የሚተባበር ማንም እንዳይኖር ሲል ዝቷል።

የሰሞኑን የእስራኤል እና የሃማስ የጋዛን የተኩስ አቁም  ስምምነት  በደስታ ከተቀበሉት ሀገራት መካከል ሩሲያ አንዷ ስትሆን የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን  ስምምነቱ ተከብሮ እንደሚቆም ተስፋ ማድረጋቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል::

ፑቲን ስምምነቱን አስታራቂዎች ይፋ ካደረጉ በኋላ በይፋ አስተያየት ሲሰጡ ይህ የመጀመሪያው ነው። ፑቲን የእስራኤል ታጋቾችን እና የፍልስጤም እስረኞችን ከማስፈታት በተጨማሪ ስምምነቱ ወደ ጋዛ ተጨማሪ ምግብ፣ ነዳጅ እና መድኃኒት እንዲደርስ  መንገድ መክፈት አለበት ብለዋል።

የፍልስጤም እና የእስራኤል ግጭት በአጠቃላይ ዕውቅና ባለው ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ማዳከም እንደማይገባም አሳስበዋል::

ሁለቱ ተፋላሚ አካላት ተኩስ አቁም ለማድረግ ስምምነት ላይ በመድረስ የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ከሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች እና መንገዶች ቀስ በቀስ የሚወጣ ይሆናል። ይሁን እንጂ የፍልስጤም ነዋሪዎች የእስራኤል ወታደሮች ወደሚገኙበት ወይም ከእስራኤል ድንበር አቅራቢያ  እንዲመለሱ እንደማይፈቅድ የእስራኤል ጦር አስታውቋል።

ስምምነቱን ተከትሎ እስራኤል ልትፈታቸው ያሰበቻቸውን  95 የፍልስጤማውያን እስረኞችን ስም ዝርዝር አሳውቃለች። ከሚፈቱት መካከልም ከ21 ዓመት በታች ያሉ 25 ወንድ እና 70 ሴት እስረኞች ይገኙበታል። ፍልስጤማዊያኑ የታሰሩት ሽብርተኝነትን በመደገፍ፣ የግድያ ሙከራ በማድረግ፣ እና ድንጋይ በመወርወር በሚሉ ወንጀሎች ተከሰው ነው።

እስራኤል እና ሃማስ ተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተው  የመጀመሪያውን የእስረኞች ልውውጥ ካደረጉ በኋላ   ሰብዓዊ ርዳታ በጦርነት ወደ ተመታችው ጋዛ መግባት ጀምሯል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ  መላው የዓለምን ሕዝብ በተለይም ፍልስጤማዊያንን በእጅጉ ያስደሰተ ቢሆንም ከኔታንያሁ የቀኝ  ጥምር አጋሮች ከባድ ተቃውሞ ገጥሞታል:: ኔታኒያሁም መንግሥታቸውን ሊያሳጣቸው ይችላል ተብሏል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም  የጋዛ የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመልቀቅ  ስምምነት ተደርሶ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ከሦስት ቀናት በኋላ የእስራኤል ጦር  ዋና አዛዦች ሜጀር ጄኔራል ያሮን ፊንከልማን እና ሌተናል ጄኔራል ሄርዚ ሃሌቪ ለ15 ወራት ለዘለቀው የጋዛ ጦርነት ምክንያት የሆነውን በፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስ የተፈጸመውን የመስከረም 26ቱን ወይም የኦክቶበር 07/22024 ጥቃት መከላከል ባለመቻላቸው የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዳልተወጡ በመግለጽ ኃላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንደለቀቁ ቢቢሲ ዘግቧል::

በአውሮፓዊኑ የ2024 ዘመን መገባደጃ ላይ በወጣ ሪፖርት እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደች ባለችው ጦርነት ወደ 250 ቢሊዮን ሰቅል (67.57 ቢሊዮን ዶላር) የሚጠጋ ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ ደርሶባታል::

የእስራኤል ቢዝነስ ጋዜጣ ካልካሊስት ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ በእስራኤል ባንክ የተገመተውን የሚያንፀባርቅ እና ቀጥተኛ የወታደራዊ፣ የሲቪል ወጪዎችን እና የገቢ ኪሳራዎችን የሚያጠቃልል አሃዝ አውጥቷል ሲል አናዶሉ ዘግቧል::

በተያያዘ ሮይተርስ እንደዘገበው በተሸኘው የአውሮፓዊያኑ 2024 እስራኤል 100 ቢሊዮን ሰቅል (28 ቢሊዮን ዶላር) ለወታደራዊ ግጭቶች ማውጣቷን የሀገሪቱ  የገንዘብ ሚኒስቴር ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል:: ይህ አሃዝ የመንግሥት ብድርን እና የሀገሪቱን የዕዳ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ። ይህም የሆነው እስራኤል በጋዛ ከፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ከሃማስ እና በሊባኖስ ከሄዝቦላህ ጋር ባደረገችው ጦርነት ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚደንት ትራምፕ በዋሽንግተን ዲሲ ስልጣናቸውን ከተረከቡ ከሰዓታት በኋላ በዌስት ባንክ ብጥብጥ ተቀስቅሷል።  በሃማስ እና በሂዝቦላህ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ከሁለት ቀናት  በኋላ እስራኤል በዌስት ባንክ በአዲስ መልክ ዘመቻ ከፍታለች:: አልጀዚራ እንደዘገበው በዋናነት የጄኒን ከተማን ከአሸባሪዎች ለማጽዳት በሚል ነው የእስራኤል ወታደሮች  ዘመቻውን የጀመሩት::

እስራኤል በዌስት ባንክ ጥቃት እያደረሰች የምትገኘው በበርካታ ታንኮች፣ በቡል ዶዘሮች እና በድሮን በመተጋዝ ነው።

በሌላ በኩል እስራኤል በጄኒን የምታደርገው ወታደራዊ ዘመቻ አስከፊ መዘዝ እንደሚያስከትል ዮርዳኖስ አስጠንቅቃለች:: የዮርዳኖስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳፋዲ  እንዳሉት በሰሜን ዌስት ባንክ በጄኒን ማክሰኞ በጀመረው የእስራኤል ጥቃት ቢያንስ 10 ፍልስጤማውያን ሲገድሉ 40 ቆስለዋል::  ሳፋዲ በስዊዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ “በዌስት ባንክ ያለው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ እና የክልሉን ደኅንነት ሊያናጋ ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በተያዘው ግዛት ውስጥ የተፈጠረውን ፍንዳታ ለመከላከል ሀገራቸው እየሠራች ነውም ብለዋል። የእስራኤል ወታደራዊ መግለጫ እንዳስታወቀው በጄኒን የሚገኘው “የብረት ግንብ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ዘመቻ ለበርካታ ቀናት ሊቆይ ይችላል።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here