የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምሥረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው። በዓሉ ከጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 20 በሚሆኑ ሁነቶች ይከበራል። በዩኒቨርሲቲው የምሥረታ በዓል ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
“የ70 ዓመታት የትምህርት ልህቀት እና የ100 ዓመታት የጤና አገልግሎት” በሚል መሪ መልዕክት የሚከበረው የዩኒቨርሲቲው የምሥረታ በዓል ለሚቀጥሉት አምስት ወራት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ተብሏል፡፡ በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፋት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው በተደራሽነት ያሳየውን ዕድገት ያክል ሀገር በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ትምህርት ለማዋሐድ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ተቋሙ በሕክምና አገልግሎት እና ከምርምር ሥራው ባሻገር ለማህበረሰቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) ናቸው። ዩኒቨርሲቲው በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ ለጎንደር ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ምስጉን ምሩቃንን በማፍራት በምርምር፣ በሕክምና እና በማሕበረሰባዊ አገልግሎት ሰፊ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው መቋቋሙም ሆነ ማደጉ ከሕዝብ ፍላጎት የመነጨ ነበር ያሉት ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ ደንቢያ እና አካባቢው የተስፋፋው የወባ በሽታ እና እሱን ለመከላከል የሠለጠነ የሰው ኀይል ማስፈለጉ ለዛሬው ትልቅ ሀገራዊ ተቋም መሠረት ሆኗል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ጥንታዊ ከሚባሉ ሀገሮች መካከል አንዷ ናት ያሉት ፕሬዚዳንቱ “ከተቋም ግንባታ፣ ከተቋም አመራር እና ከተቋማት ቀጣይነት አኳያም ያለን ባሕል በሚገባ ሊፈተሽ ይገባል” ብለዋል።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር)ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ70 ዓመታት ጉዞው በሀገሪቱ ዕውቀት እና ፈጠራ እንዲስፋፋ በማድረግ ፈር ቀዳጅ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል። ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉም ለኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም