በዓላት ለህብረ ብሔራዊነት

0
178

ኢትዮጵያ በአለም ቅርስነት በርካታ የመስህብ ቦታወችን፣ የማይዳሰሱ ሐይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔወችን  በማስመዝገብ ተጠቃሽ ከሆኑ ሀገራት ተርታ ተጠቃሽ ናት። በክልላችንም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር አብያተ መንግስታት ሕንፃወች፣ የስሜን ብሔራዊ ፖርክ፣ የጣና ገዳማት  ይገኛሉ። ከእነዚሕ በተጨማሪም በማይዳሠሡ ቅርስነት በሃገራችን ከተመዘገቡት መካከል የመስቀል እና የጥምቀት በዓልም በክልላችን በድምቀት ይከበራሉ።

ሃገራችን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ በርካታ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት ያላት ስትሆን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምሕርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ)  ከመዘገበው አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል ክዋኔው ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሚታይበት መከባበር እና መተሳሰብ የሚንፀባረቅበት ዘር እና ጎሳ የማይለይበት የመቻቻልና የፍቅር በዓል ተብሎ ይጠቀሳል።

በጥር ወር ከተከበሩ እና እየተከበሩ ካሉ ሐይማኖታዊ እና ባሕላዊ  ክዋኔወች መካከል የጥምቀት በዓል በክልላችን በስፋት እና  በድምቀት ተከብሯል። በተለይም በጎንደር እና በምንጃር ሸንኮራ በርካታ ታዳሚወች ከየአካባቢው በመምጣት እና በመሠባሠብ በዓሉን በድምቀት አክብረዋል፡፡ የቃና ዘገሊላም  በሁሉም የክልሉ አካባቢወች፣ የግዮን ክብረ በዓል በሰከላ በድምቀት ተከብረዋል። እነዚሕ ክብረ በዓላትም የክልሉን ገቢ በማሳደግ በኩል ሚናቸዉ ከፍ ያለ ነው፡፡ ክዋኔወቹም    ከሀይማኖታዊ አከባበራቸው ባሻገር እንደገቢ ማስገኛምና ለማህበረሰቡ ዋነኛ ጌጦች በመሆን ተጠቃሾች  ናቸው ።

እነዚህ ክብረ በዓላትም የማሕበረሰቡ ወግ እና ባሕል በአደባባይ የሚገለጡባቸው፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሚታይባቸዉ መተሳሰብ፤ መከባበር እና መረዳዳት የሚንፀባረቅባቸዉ፣ ማሕበረሰቡን በአንድነት ያጋመዱ    ክዋኔወች በመሆን መከናወናቸውን   የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አሳውቋል።

ይሁንና ከቅርብ አመታት ወዲሕ የጎብኝወች ቁጥር በተለይም በክልላችን በእጅጉ አሽቆልቁሏል። ምክንያቶቹ ደግሞ በኮረና ባይረስ ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ላይ ደግሞ በክልሉ ውስጥ የተከሰተው ግጭት  ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው።

በየዓመቱ በርካታ ጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ ሐገራዊ ምጣኔ ሐብታቸውን የሚደጉሙ ሐገራት  የሚጠቀሱ ሲሆን እነዚህ ሐገራትም ከዘርፉ ዳጎስ ያለ ገቢ ያገነኛሉ። ስታቲስታ የተሰኘው ድረ ገፅ እንዳስነበበውም እ. አ. አ በ2023 ከ266 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሰወች የስራ እድል የፈጠረ፣ ይህም በዓለም የተፈጠረውን የስራ እድል ስምንት  ነጥብ ዘጠኝ በመቶ የሸፈነ፣ አምስት በመቶ የዓለምን አጠቃላይ የምርት ውጤት ድርሻ የያዘ እና ከዘጠኝ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኘ እንደነበር እና በተጠናቀቀው 2024 ዓመትም በዘርፉ ከ11 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አመላክቷል።

ቱሪዝም በክልላችን ጥሩ የገቢ ምንጭ ሆኖ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ግን  በተከሰተው ግጭት አማካኝነት ከፍተኛ  የሆነ መቀዛቀዝ ገጥሞታል። ምክንያቱም ቱሪዝም   ከሌሎች ዘርፎች በተለየ ሁኔታ ፍፁም ሰላምን የሚፈልግ ዘርፍ ስለሆነ በማለት ቱሪዝም ፋክት የተሰኘው ድረ ገፅ አመላክቷል። ይህንን መቀዛቀዝ ለማስወገድ እና ወደ ነበረበት ድምቀት ለመመለስም  በክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የተጀመሩ ተግባራት ይበል የሚያስብሉ ናቸው።

ከታሕሳስ ወር መጨረሻ ጀምሮ በክልላችን በርካታ ሀይማኖታዊ በዓላት ተከብረዋል፡፡ በቀጣይም የሚከበሩ ባሕላዊ እና ሐይማኖታዊ በዓላት አሉ የመርቆርዮስ ክብረ በዓል በደብረ ታቦር፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል በአዊ፣ የአስተርዮ ማርያም ንግስ በመርጡለማርያም እና በደረስጌ ማርያም፣ ጥርን በባሕርዳር እስከወሩ መጨረሻ ድረስ የሚከበሩ እና በጉጉት እየተጠበቁ ያሉ ክብረ በዓላት ናቸው።

የቱሪዝም ዘርፉ በጎብኝወች እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ እና እንቅስቃሴ የሚኖረው ደግሞ ጎብኝወች አስተማማኝ ሰላም እና ለደሕንነታቸው ዋስትና እንዳላቸው ሲሰማቸው የሚተገብሩት በመሆኑ እንደሆነ በመረዳት የየአካባቢያችንን ሰላም በማረጋገጥ በኩል ከፍተኛ ባለድርሻ መሆናችንን ተገንዝበን ሰላምን ለማስፈን እና የቱሪስት ቁጥር ለማሣደግ እና ከዘርፉ የሚገኘዉን   አብሮነት፣  ህብረብሄራዊነት እንዲሁም ገቢዉን  ለማግኘትና ለማስቀጠል ሁላችንም በጋራ   እንረባረብ።

በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here