የአማራ ክልል የሰላም ሁኔታ አሁንም የሁሉም አካል አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል:: ምንም እንኳ ክልሉ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀድሞ የተሟላ የሰላም ሁኔታው ባይመለስም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ ግን እየተገለጸ ነው:: ያም ሆኖ አጀንዳነቱ አሁንም ድረስ የቀጠለው ሰላም ምንም አይነት ስጋት የማይስተዋልበት እንዲሆን ማድረግ ይገባል:: በነጻነት ወጥቶ ለመመለስ ቤተሰብን ብሎም ዘመድ አዝማድን ሰላም እንዳይነሳ ሰላም መሠረቱ ነው:: የገቢ ምንጭን የተለያዩ ተጨማሪ ሥራዎችን ተንቀሳቅሶ በመሥራት እና በማሳደግ ቤተሰብን ከኑሮ ጫና፣ ሀገር የጀመረችውን የዕድገት መንገድ ከዳር ለማድረስ ሰላምን አጀንዳ ማድረጉ ከሁሉም የሚጠበቅ ነው::
አርሶ አደሩ ወደ ተሟላ ልማት እንዲገባ፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ባልተቆራረጠ ሁኔታ ዓመቱን ሙሉ እንዲያስቀጥሉ፣ የታመመው ያለምንም የሕክምና ግብዓት እጥረት እና የመንገድ ተደራሽነት እንዲታከም፣ የመንግሥት ሠራተኛው ሕዝብ የሚፈልገውን የመልማት ጥያቄ በነጻነት ተግቶ እንዲሠራ ከሰላም በተቃራኒ የሚቆም አካል አይኖርም:: እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች እና ፍላጎቶች ዕውን እንዲሆኑ ግን የሰላም ቃሉ በልብ መልካም ፈቃድ ከአንደበት የሚወጣ ሊሆን ይገባል:: ያኔ ለሰላም የሚመጣ የትኛውም አይነት የሰላም አማራጭ ተቀባይነት አግኝቶ ንጹሀኑ ሕዝብ እየከፈለ ካለው ያልተገባ መስዋዕትነት ማዳን ይቻላል::
የአማራ ክልልን ከሰላም ቀውስ አዙሪት በማውጣት የልማት፣ የማኅበራዊ እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በተሟላ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ላለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ ለሚሆን ጊዜ በሰላም ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፣ የሰላም ጥሪም በተደጋጋሚ በክልሉ ለሚንቀሳቀሰው ኀይል ተላልፏል፣ የእንደራደር ፍላጎቶችም በተደጋጋሚ ተስተጋብተዋል፤ የሰላም አማራጭን አልቀበል ባለው ኅይል ላይ ደግሞ የተለያዩ ወታደራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ክልሉን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ጥረቶች ተደርገዋል፤ አሁንም መቀጠላቸውን መንግሥት አስታውቋል::
ሕዝቡ አሁንም ስለ ሰላም ቢጮህም አሁንም ግን ግጭቱ ዘላቂ መፍትሔ አላገኘም:: በዚህም ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳቱ፣ ሰብዓዊ ኪሳራው፣ ማኅበራዊ ችግሩ፣ ሥነ ልቦናዊ ምስቅልቅሉ እንዲቀጥል አድርጎታል:: ይህ የሰላም መደፍረስ አሁንም በማኅበራዊ ተቋማት እና በአገልግሎት ዘርፉ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ማሳያ ነው:: ለአብነት ትውልድ የሚገነባበት፣ የዕድገት መንገድ የሚጠረግበት፣ የሰላም ዘላቂ መፍትሔ የሚመላከትበት የዕውቀት አምባ በሆነው ትምህርት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ቀዳሚ ማሳያ መሆኑን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የማህበራዊ ዘርፍ ኃላፊ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ቢሮዉ የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት አስታውቀዋል::
እንደ ኃላፊዋ በ2016 ዓ.ም መማር ከነበረባቸው ተማሪዎች መካከል ትምህርታቸውን የተከታተሉት 58 በመቶ ብቻ ናቸው:: ችግሩ ዛሬም ድረስ ቀጥሎ በተያዘው የትምህርት ዘመን ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው:: በጥቅል ከተመዘገቡት ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ እስካሁ ከአራት መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም::
ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለስደት፣ ለሱስ፣ ላለዕድሜ ጋብቻ እና ለሥነልቦና ጫና መዳረጋቸውን፣ መምህራን መገደላቸውን፣ መታገታቸውን፣ ለስቃይ እና ላልተገባ እንግልት መዳረጋቸውን ኃላፊዋ ጠቁመዋል::
በአጠቃላይ በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር አሳሳቢነት ኃላፊዋ ሲገልጹ አሁንም በሰላማዊ መንገድ መፍታት ካልተቻለ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ልጆቻቸውን ዩኒቨርሲቲ አስገብተው የሚያስመርቁ የአማራ ወላጆች እንደማይኖሩ ኃላፊዋ ስጋታቸውን አስረድተዋል:: በክልሉ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎች ቁጥር በዓለም ላይ ከ106 ሀገራት፣ በአፍሪካ ከ14 ሀገራት፣ በኢትዮጵያ ከስድስት ክልሎች የሕዝብ ቁጥር እንደሚልቅም ገልጸዋል:: “ዛሬ ካላስተማርን ነገ ስንታመም የሚያክመን ሀኪም፣ ልጆቻችን የሚያስተምር መምህር፣ ቤታችንን የሚገነባ መሀንዲስ፣ በየዘርፉ የሚያስፈልገን የሰለጠነ የሰው ኅይል አይኖረንም። በመሆኑም ድርጊቱን መላው ሕዝብ ሊያወግዘው ይገባል” በማለትም የሰላም ጥሪ አቅርበዋል::
ሕዝብ የሰላም ችግሮች በሰላማዊ ድርድር እንዲፈቱ በመንግሥት በኩል እየተስተጋባ ያለው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ከመጠየቅ ጀምሮ ራሱም የሰላም ዘብ ለመሆን አጋርነቱን እያረጋገጠ ነው:: ከሰሞኑ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ዓላማ ያደረገ ሕዝባዊ ውይይት ባካሄደበት ወቅት ግጭቱ እያስከፈለ ስላለው መጠነ ሰፊ ቀውስ እና የሰላም መንገዶች ተመላክተውበታል::
እገታ፣ ዝርፊያ እና ውንብድና የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የፈጠራቸው ችግሮች መሆናቸውን በውይይቱ የተሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል:: ይህም ሕዝብ እረፍት እንዲያጣ አድርገውት የቆዩ ክስተቶች ናቸው::
ግጭቱ አሁንም ድረስ እያደረሰ ያለው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ጭምር ጠቁመዋል:: ሕዝቡ ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ያጋጠመው ማኅበራዊ መገለል ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንደዳረገው አንስቷል:: ተማሪዎች ከትምህርት እንዲርቁ፣ በሕጻናት ላይ እየተፈጸመ ያለው እገታ አሁንም ድረስ እያሳቀቃቸው እንዲቀጥል ማድረጉን ነዋሪዎች ጠቁመዋል::
አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደቀድሞው በመመለስ ሕዝቡን የሰላም ዘብ ማድረግ፣ ተራ ውንብድናን እና ዝርፊያን ነዋሪው በየአካባቢው ተደራጅቶ መጠበቅ ዋና መውጫ መንገድ ማድረግ እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል::
ለሀገር እና ለዳር ድንበር ዘብ መቆም እንጂ እርስ በእርስ መገዳደል ኢትዮጵያዊ ባህሪ አለመሆኑን ያስታወቁት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሐም ናቸው:: በቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል የተገኙት ብጹዕ አቡነ አብርሐም “ስንደማመጥ፣ ስንተባበር፣ ስንስማማ እጅግ ያምርብናል፤ ጉዳታችን አለመተባበራችን፣ አለመናበባችን፣ አለመስማማታችን እና በዘፈቀደ መመላለሳችን ነው” በማለት ለምእመኑ አስገንዝበዋል::
ሀገርን ከፍ ለማድረግ እና በሃይማኖት ጸንቶ ለመኖር ፍቅር እና ሰላምን ገንዘብ አድርጎ መሄድ እንደሚገባም ብጹዕ አቡነ አብርሐም ጠቁመዋል:: ገፊ፣ ተገፊ፣ አሳዳጅም ሆነ ተሳዳጅ ሳይኖር ሁሉም ነገር በሰላም እንዲፈታ መጸለይ እና ሰላምን ማወጅ እንደሚገባ አሳስበዋል::
በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አሥተባባሪ እና የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አስታውቀዋል:: በተቋሙ የስድስት ወራት ግምገማ ላይ የተገኙት ኃላፊዉ አሁን በሚታየው ብርሐን ተወስኖ መቀመጥ ሳይገባ በቀጣይ የክልሉን ሕዝብ የመልማት ፍላጎት ዕውን ለማድረግ የጸጥታ ኅይሉ የሚከፍለውን ዋጋ ከፍ አድርጎ መጓዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: “ወታደር በሚያደርገው ዝግጅት እና በቆፈረው ምሽግ ነው ሕይወቱን የሚያድነው” ያሉት ኃላፊዉ፣ ክልሉን በራስ ለመምራት ኃላፊነት መሸከም የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚገባም ጠቁመዋል::
የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ቁጥር እና የመልማት ጥያቄ ያለባት ሀገር ናት ብለዋል:: ይሁን እንጅ ይህንን ጥያቄ በትጥቅ ትግል ለማስመለስ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሀገርን ትርፋማ እንደማያደርግ ሚኒስትሩ ገልጸዋል:: በሰላማዊ መንገድ ችግርን መፍታት አትራፊ የሚያደርገው ሀገርን ነው ብለዋል:: በትጥቅ ትግል ፍላጎትን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ አካላትም ሆኑ መንግሥት ችግሩን በኅይል ለመቀልበስ በሚያደርገው ጥረት አትራፊ አይሆኑም:: የትጥቅ ትግል በሚደረግባቸው አካባቢዎች የሚኖረውን ሕዝብም ለከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ ከመዳረግ ያለፈ ትርጉም እንደማያመጣም ጠቅሰዋል::
መንግሥት የትጥቅ ትግል እያስከተለ ያለውን መጠነ ሰፊ ሁለንተናዊ ኪሳራ በመታደግ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማስፈን ዝግጁነቱን በተደጋጋሚ እያስታወቀ እንደሚገኝ አስታውቀዋል:: በዚህም የትጥቅ ትግል መሠረተ ልማትን ለውድመት በመዳረግ ሕዝብን ለከፋ ጉዳት እየዳረገ መሆኑን ተገንዝበው ሰላምን አማራጭ አድርገው ለመጡ አካላት ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል:: ሌሎችም ሰላማዊ ትግልን ቀዳሚ ምርጫቸው ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠይቀዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም