የትራምፕ ውሳኔዎች

0
168

አርባ ሰባተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ34 ክሶች ጥፋተኛ የተባሉ የመጀመሪያው የአሜሪካ መሪ ናቸው። ሆኖም ይህ ሁሉ ፕሬዝዳንት ከመሆን አላገዳቸውም። ትራምፕ ለምርጫ ቅስቀሳ ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን ቅድሚያ አሜሪካ የሚለውን ፖሊሲያቸውን ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ከገቡ በኋላ ተግባራዊ እያደረጉት ነው። በርካታ ውሳኔዎችንም አሳልፈው የዓለምን ሕዝብ ግራ አጋብተውታል።

ከሰሞኑ ዓለማችን ካስተናገደቻቸው ሁነቶች መካከል አነጋገሪው  የትራምፕ በአሜሪካ የሚኖሩ ሕገ ወጥ ስደተኞችን በጅምላ ወደ ሀገራቸው የመመለስ ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ስደት ዛሬ አልተጀመረም፤ የሰው ልጅ ራሱ እና ቤተሰቡ የተሻለ ሕይዎት እንዲኖሩ ለማድረግ ከሀገር ሀገር ተዘዋውሮ ይሠራል፤ ይኖራልም።

ሆኖም ይህ ሁሉ ነገር የሚሆነው በሀገራቱ በጎ ፈቃደኝነት ላይ ሲመሠረት ነው። አሜሪካም በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ ገብተው እየኖሩ ነው፤ ወንጀልም እየፈጸሙ ነው ያለቻቸውን የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን ከሀገሪቱ ለማስወጣት ቆርጣ ተነስታለች።  በዚህም ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በመጀመሪያው የትራምፕ የ100 ቀናት የፕሬዝዳንትነት ቆይታ ወደ መጡበት ሀገር ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ትራምፕ በሃይማኖት ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች ላይ ፍተሻ ማድረግ የሚከለክለውን ፖሊሲ እንደሚያስቆሙም ተናግረዋል። አብዛኛዎቹ ሰነድ አልባ ስደተኞች በእነዚህ ተቋማት ተጠልለው ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል። ለአንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት የዘለቀውን በአሜሪካ የተወለደ ማንኛውም ሰው የአሜሪካ ዜግነት ያገኛል  የሚለውን ሕግም እንደሚሽሩት ቃል ገብተዋል።

ከዚህ ጋር  በተገናኘ አሜሪካ  ከኮሎምቢያ መንግሥት ጋር የነበራት እሰጥ አገባ ትኩረትን ስቦ ነበር።  ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም ዕቃዎች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ በመጣላቸው እና ከሳምንት በኋላም ወደ 50 በመቶ ከፍ እንደሚል፣ አለፍ ሲልም በኮሎምቢያ መንግሥት ባለስልጣናት፣ አጋሮቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው ላይ የጉዞ እገዳ እና አፋጣኝ የቪዛ ስረዛ እንደምታደርግ  ትራምፕ በማስጠንቀቃቸው ኮሎምቢያ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉ ዜጎቿን ልትቀበል ግድ ብሏታል።

የኮሎምቢያዉ ፕሬዚዳንት ጉስታቮ ፔትሮ በሀገራቸው ላይ ታሪፍ ከመጣሉ ቀደም ብሎ አሜሪካ ያባረረቻቸውን በሁለት ወታደራዊ አውሮፕላን የተጫኑ ስደተኞችን ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ መከልከላቸው የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ የኮሎምቢያዉ ፕሬዚዳንት ስደተኞች እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው በወታደራዊ አውሮፕላን እጃቸው እና እግራቸው በሰንሰለት ታስሮ መምጣታቸው አበሳጭቷቸው ስለነበር ነው  አውሮፕላኑን እንዳያርፍ የከለከሉት።

ሌላው ዓለም አቀፍ ስጋትን የፈጠረው የትራምፕ ውሳኔ ለልማት የሚደረገውን ድጋፍ የተመለከተው ነው፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የውጭ ፖሊሲያቸው ውጤታማነት እና ወጥነት እስኪገመገም ድረስ ለ90 ቀናት አሜሪካ የምታደርገውን የውጭ የልማት ድጋፍ እንዲቆም አዘዋል። አሜሪካ ከመላው ዓለም ትልቋ ዓለም አቀፍ እርዳታ ለጋሽ ስትሆን በአውሮፓዊያኑ በ2023 ብቻ 68 ቢሊዮን ዶላር (ስምንት ነጥብ አራት ትሪሊዮን ብር ገደማ) ማውጣቷን ቢቢሲ ዘግቧል።

ይህ የሚቆመው ዕርዳታ ከልማት እስከ ወታደራዊ ድጋፍ ድረስ የሚደረገው ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል። ለድንገተኛ የምግብ ዕርዳታ እንዲሁም ለእስራኤል እና ለግብጽ ከሚደረገው ወታደራዊ ድጋፍ በስተቀር ሁሉም የውጭ ልገሳዎች እንደሚቆሙ ነው የተገለጸው። አንድ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት  ውሳኔው በአሜሪካ ልገሳ በሚደረግላቸው የውጭ ዕርዳታ ፕሮግራሞች ላይ ከባድ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ሌላው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የወሰዱት እርምጃ ታሪፍን በተመለከተ ነው፤ ለአሜሪካ ምርቶች ቅድሚያ ለመስጠት ቃል በገቡት መሠረትም ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ቀላል የማይባል ታሪፍ እንደሚጥሉ ይጠበቃል። ይህም ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ ለሚያስገቡ ሀገራት ድንጋጤን ፈጥሯል። ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ 10 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት ሀገራት ምርቶችም ታሪፉ እንደማይቀርላቸው ነው የተነገረው።

ለአብነትም ካናዳ እና ሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሚገቡትን ሕገ ወጥ ስደተኞች እና ፌንታኒል የተሰኙ ዕጾችን መቆጣጠር ካላስቻሉ በሁለቱ ሀገራት ምርቶች ላይ 25 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አስጠን ቅቀዋል።

ዋናዎቹ ሦስቱ የአሜሪካ የንግድ አጋር የሆኑት ቻይና፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ ዋና የገፈቱ ቀማሾች ሲሆኑ በነዚህ ሀገራት ላይ ታሪፍ መጣሉ የሀገራቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ ሊጎዳ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ በምርቶቹ ተጠቃሚ አሜሪካዊያን ላይም የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ አይቀርም ተብሏል።

ቻይና  አብዛኛውን ከአሜሪካ የምታገኘውን ገንዘብ ጦሯን ለመገንባት ትጠቀምበታለች ብለው የሚያስቡት ትራምፕ ይህንን ለማስቀረትም ወደ አሜሪካ በምትልካቸው ዕቃዎች ላይ ታሪፍ በመጣል ሊገድቧት ሞክረዋል። በዚህም ምክንያት ቤጂንግ ላይ ታሪፍ ለመጣል የደረሱበትን ውሳኔ ትክክለኛ መሆኑን ነው የገለጹት።

“ከቻይና የሚበልጥ አንድ በጣም ትልቅ ኃይል አለን፤ እሱም ታሪፍ ነው” የሚሉት ትራምፕ ይህንን በመጠቀም ቻይና ላይ ጫናዎችን ለመፍጠር እየሞከሩ ነው፡፡ ሆኖም ስላሉባቸው ችግሮች በመነጋገር  ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የጣሉት ታሪፍ አሜሪካ ከአንዳንድ ሀገሮች የምታስገባቸውን ምርቶች መጠን እንዲቀንስ አድርጓል። ሌሎች ሀገራት ወደ አሜሪካ የሚልኩት የምርት መጠን ደግሞ ጨምሯል።

ቢቢሲ እንደዘገበው እ.አ.አ ከ2018 በፊት ወደ አሜሪካ ከሚገቡ ምርቶች ከ20 በመቶ በላይ የቻይና ምርቶች ናቸው። ይህ አሃዝ አሁን ላይ ከ15 በመቶ በታች ደርሷል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት የማይዋጥላቸው ትራምፕ አረንጓዴ የኃይል ማመንጫዎችን የተቹ ሲሆን የነፋስ ኃይል ማመንጫዎችን “ከተፈጥሮ ጋዝ አንጻር ወጥ ያልሆኑ” ብለዋቸዋል።  የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፓነሎች የሚይዙትን የቦታ ስፋት ደግሞ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል። በጆ ባይደን ጊዜ ለአረንጓዴ ልማት የሚውሉ የተፈረሙ የገንዘብ ሰነዶችን እንደሚሰርዙ ነው የተነገረው።

በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሸከርካሪዎችንም ለማስወገድ ቃል ገብተዋል። ዘ ኮንቨርሴሽን ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን ከዓለም ጤና ድርጅት ለማውጣት መወሰናቸው በአፍሪካ ውስጥ በጤና ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እየተገለጸ ነው። ትራምፕ የአሜሪካን ገንዘብ፣ ድጋፍ እና ሀብቶችን ለዓለም ጤና ድርጅት መስጠቱ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በጤና ድርጅቱ ላይ ትልቁ ተጽዕኖ የሚመጣው የአሜሪካን የገንዘብ ድጋፍ በማጣት ነው። እስካሁን ድረስ አሜሪካ ከድርጅቱ አጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ 18 በመቶውን በማዋጣት ቀዳሚዋ ለጋሽ ሀገር ነበረች።

ሌላው ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤልና በሀማስ ላይ የሰጡት አስተያየት አነጋጋሪ ሆኗል። በተለይ አጠቃላይ የጋዛን ሕዝብ ወደ ግብፅ እና ዮርዳኖስ እንዲሰፍሩ መጠየቃቸው ፍልስጤማዊያንን ሆነ ብሎ ሀገር ለማሳጣት ነው የሚል አንድምታን ፈጥሯል።

የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነትን የተመለከተው ጉዳም ትኩረትን ስቧል፤ የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት   “በአፋጣኝ መቆም አለበት” የሚሉት ትራምፕ የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፍጹም ወደዚህ አውዳሚ ጦርነት መግባት አልነበረባቸውም ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ሌላው አነጋጋሪው ሁነት የመንግሥት ሠራተኞችን በገዛ ፈቃዳችሁ ሥራ ልቀቁ የሚለው ትዕዛዛቸው ነው። ይህ  የመንግሥት ሠራተኞች ሥራ የመልቀቅ አማራጭ የአሜሪካ  መንግሥትን እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር (12 ነጥብ አራት ትሪሊዮን ብር ገደማ) ለማዳን እንደሚያስችል ተገልጧል። የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር እ.አ.አ እስከ የካቲት 6 ቀን 2024 ጊዜ ድረስ ሥራቸውን ለመልቀቅ ከተስማሙ የስምንት ወር ደመወዛቸውን እንደ የስንብት ፓኬጅ እንደሚያገኙ ተነግሯል።

ሆኖም የፖስታ ቤት ሠራተኞች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት እንዲሁም የተወሰኑ የብሔራዊ ደህንነት ሠራተኞች በዚህ ፓኬጅ እንዳልተካተቱ ታውቋል።

ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በተደጋጋሚ በአርክቲክ ውቅያኖስ የሚገኘውን እና በዓለማችን ትልቁን የግሪንላንድ ደሴት ለመጠቅለል ፍላጎት እንዳላቸው ሲያንፀባርቁ ነበር። ስልጣናቸውን ሲጨብጡም  ትራምፕ ከግሪንላንድ በተጨማሪ የፓናማ ‘ካናል’ እና ካናዳን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ እንደሚሹ ተናግረዋል።

የዴንማርክ እና የአውሮፓ ባለሥልጣናት በበኩላቸው “ግሪንላንድ ለሺያጭ አትቀርብም፤ የግዛት አንድነቷም መጠበቅ አለበት” ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here