ውበት እንደማሻሻጫነት

0
142

እውነቱን እንድናገር ከተፈለገ አዘውትሬ ወደዚያ መዝናኛ ክበብ ወይም ካፍቴሪያ የምሄደው የሴቶችን ጭን ለማየት ስል ብቻ ነው፡፡ ከአንደኛው ካፍቴሪያ ወጥቼ ወደ ሌላኛው ከሄድኩም ፍላጎቴ ተመሳሳይ ነው፤ ጭን ማየት ብቻ፡፡

እንደውም አንድ ቀን አንዲት ቆንጅዬ አስተናጋጅ ጭኖቿን ለኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የካፍቴሪያው ተጠቃሚዎች ዓይን አጋልጣ ወደኔ መጣችና “ምን ልታዘዝ?“ አለችኝ፡፡ እውነቱን ለመናገር ምን ልታዘዝ ያለችበት ድምጿ፣ ተክለ ቁመናዋ፣ ጠይምነቷና ሁለ ነገሯ ማራኪ ቢሆንም እኔን የበለጠ የማረኩኝ ግን ጭኖቿ ናቸው፡፡

 

ልጅቱ አጠገቤ ቆማ እና በትህትና አደግድጋ ምን ልታዘዝ ስትለኝ፣ እኔ ደግሞ በራሴ የውበት መስፈሪያ ውበቷን እየሰፈርኩኝ ደረጃ በማውጣት ስዘገይባት በድጋሚ “ምን ልታዘዝ የኔ ወንድም?“ ብላ ጠየቀችኝ፡፡ ሳላስበውና በፍጥነት ከአፌ የወጣው ቃል “ጭን“ የሚል ነበር።

ልጅቱ ባልኳት ነገር ግራ ተጋብታ ወይም ደንገጥ ብላ “ምን አልከኝ የኔ ወንድም?“  ስትል ተዝቆ በማያልቀው ትህትናዋ ያልኳትን ደግሜ እንዳረጋግጥላት ጠየቀችኝ፡፡ እኔም በቅጽበት በአዕምሮዬ፣ በምላሴና በሁለመናዬ የሚንከላወሱትን የልጅቱን ጭኖች ጉዳይ ለአፍታ የዘነጋኋቸው በመምሰል “ጭን“ ላልኩት ቃሌ በሚቀራረብ መልኩ “ቀጭን ሻይ“ በማለት አዘዝኳት፡፡

 

“እሺ“ ብላኝ ልታመጣልኝ ስትሄድ ዓይኖቼ ጭኖቿ ላይ ተሰክተው እንደቀሩ ናቸው፡፡

ልጅቱ ያዘዝኳትን ቀጭን ሻይ አሠርታ እስክታመጣልኝ ድረስ በሃሳቤ ስለ እሷ እና ስለ ሌሎችም የመስተንግዶ ሠራተኞች ማሰላሰል ጀመርኩኝ፡፡ ለምን እንደዚህ ገላቸውን አራቁተው እንዲለብሱ ያደርጓቸዋል? ለምንስ ልጆቹ ራሳቸው እንዲህ ዓይነት ቁራጭ ልብስ አንለብስም አይሉም? እንዴት ግን ልጆቹ የኔንና መሰሎቼን ዓይኖች መቋቋም ቻሉ? እና ሌሎችንም ጥያቄዎች በውስጤ እያወጣሁና እያወረድኩ ባለሁበት ቀጭኑ ሻይ ተሠርቶ መጣልኝ፡፡

ባለ ውብ ጭኗ ከጉልበቷ በላይ የሆነውን ቀሚስ አይሉት ሙታንታ አስሬ ወደ ታች ለመመለስ ትታገላለች፡፡ የቁራጩ ቀሚስ ስሪት ግን ከጉልበቷ በላይ እንዲውል በመሆኑ  መታየት የሌለበትን የሰውነት ክፍሏን እንድታሳይ አስገድዷታል፡፡

 

ለእኔ ዓይነቱ የጭን ማየት ሱሰኛ የአስተናጋጆቹ አለባበስ በእጅጉ የሚመቸን ቢሆንም ለብዙዎች ግን ምቾት አይሰጣቸውም፡፡ በተለይ አንድ ቀን አጠገቤ ተቀምጠው እንደኔው ሻይ ቡና እየጠጡ የነበሩ ጓደኛማቾች በአስተናጋጇ ጭን ምክንያት ሲጣሉ ስላየሁኝ፣ የተጋለጠው የአስተናጋጆቹ ጭን የጥል መንስኤም እንደሚሆን ተረድቻለሁ፡፡

 

ያን ዕለት የሆነው እንዲህ ነው፤ ሁለቱ ጓደኛማቾች እኔ አጠገብ ባለ ባዶ ወንበር ላይ ተቀመጡ፤ አስተናጋጇ መጥታ ምን ልታዘዝ ስትላቸው ሴቲቱ ስፕራይት ካላቸው ስፕራይት እንዲሆንላትና ሎሚም ካለ አብሮ እንዲመጣላት አዘዘች፡፡ ወንዱ ግን አጠገቡ  የቆመችው አስተናጋጅ የምታሳየውን የንጋት ጮራ የመሰለ ጭን እያየ ያለበትንም ቦታ ዘንግቶታል፡፡

 

ፍቅረኛው ጎኑን በክርኗ ደቃችውና “ምን እያየህ ነው? ልጅቱ ምን ልታዘዝህ እያለችህ የምትፈልገውን ለምን አትነግራትም?“ በማለት ተቆጥታ ጠየቀችው፡፡ ልጁም ዓይኖቹ ይሁኑ የልጅቱ ጭኖች ያመጡበትን ጣጣ እያሰበ “ጥብስ“ ብሎ አዘዘ፡፡ እንኳንስ ፍቅረኛዋና አስተናጋጇ ይቅሩና እኔም ራሴ ሁኔታውን ስከታተል ስለነበረ በልጁ ጥብስ ማዘዝ ከት ብዬ ሳቅኩኝ፡፡

 

አስተናጋጇ በሳቋ ደንበኛዋ እንዳይሸማቀቅ ተጨንቃ “ይቅርታ! ጥብስ የለንም፤ ካፌው ከትኩስና ከለስላሳ መጠጦች ውጪ የሉትም“ አለችው፡፡

የልጁ ዓይኖች ፈጽሞ ከልጅቱ ጭኖች ላይ መነቀል አልቻሉም፤ በዚህ ሁኔታው የተናደደችው ፍቅረኛው ደግሞ “የኔንም ስፕራይት ተይው“ አለችና “ና ሌላ ቦታ እንሂድ“ ስትል አዘዘችው ጓደኛዋን፡፡

 

“እዚሁ ይሻለናል“ ብሎ መልስ ሲሰጣት እንኳን ዓይኖቹ ፍቅረኛውን እያዩ ሳይሆኑ የልጅቱን ጭኖች እያዩ ነው፡፡

ልጅቱ የፍቅረኛዋን ፊት በመዳፏ ወደ ራሷ አዞረችና አንዴ በጥፊ አላሰችው፤ ይህ ሲሆን ልጁ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ሀፍረት ውስጥ ገባ፡፡ ያፈረው በፍቅረኛው በመመታቱ ይሁን ጭኖቿን ሲያይ በነበረችው አስተናጋጅ ፊት በመመታቱ ይሁን አይታወቅም፡፡ ሀፍረቱ ከፊቱ ላይ ገለል ሲል ደግሞ ንዴቱ ቦታውን ተረከበ፡፡

 

እሱም ፍቅረኛውን በቡጢ ነረታትና ደም በደም አደረጋት፡፡ ይህንን ያዩ የክበቡ ደንበኞች በልጁ ላይ የቁጣ መዓት አወረዱበት፡፡ ሴትን ልጅ መደብደብ አላዋቂነት እንደሆነም ነገሩት፤ የሆነውን ሁሉ እንደኔ ቁጭ ብለው ባያዩም ሁሉም በልጁ ላይ ፈረዱበት፡፡ እኔ ግን የዚህ ሁሉ ጠብ መንስኤ የአስተናጋጇ ጭኖች እንደሆኑ አውቄያለሁ፡፡

 

ከዚህ ትውስታዬ ስመለስ ቀጭን ሻይ ብዬ ያዘዝኩት ሻይ ወደ ቀዝቃዛ ውኃነት ተቀይሯል፡፡ አጨብጭቤ አስተናጋጇን ጠራኋት፡፡ ስትመጣም ሃሳብ ውስጥ ገብቼ ሻዩ ስለቀዘቀዘብኝ ከተቻለ ደግማ አስሙቃ እንድታመጣልኝ ነገርኳት፡፡ እግረ መንገዴንም ልጅቱ ወደኔ ስትመላለስ ጭኖቿን መላልሼ የማየት ዕድሉ ስለሚፈጠርልኝ በቀዘቀዘው ሻዬ ብዙም አልተከፋሁም፡፡

አስተናጋጇ በትዕዛዜ መሠረት የቀዘቀዘውን ሻይ አሙቃ እስክታመጣልኝ ድረስ እሷና መሰሎቿ የሚለብሱትን ቁራጭ ጉርድ ቀሚስ ፈቅደው ይሁን ተገድደው ልጠይቃት ወሰንኩኝ፡፡ ወዲያው ሻዬን ይዛ እንደመጣችልኝም “ቁጭ በይና ሻይ ቡና ልጋብዝሽ“ አልኳት፡፡ እንደማይፈቀድላት ስትነግረኝ ቀድሜ ያሰብኩትን ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡

 

ልጅቱ ያንን ከአስተዳደጓ ጋርም ሆነ ከዕምነቷ ጋር የሚጻረር ልብስ የምትለብሰው ለእንጀራዋ ብላ እንደሆነ ነገረችኝ፡፡ ያንን ድርጅቱ ያዘጋጀውን ልብስ መልበስ የማትፈልግ ከሆነ ሥራውን ማግኘት እንደማትችልም አሳወቀችኝ፡፡ ያንን ልብስ መልበስ፣ በልቶ የማደርና ያለማደር ጉዳይ ሆኖባት እንጂ በእሷ ፈቃድ ቢሆን ፈጽሞ ያንን ጭኗን የሚያጋልጥ ልብስ እንደማትለበስ ከምሬት ጋር ገለጸችልኝ፡፡

ከልጅቱ ምሬት ጀርባ ስላሉት አስገድዶ አልባሾች ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ወደ ሆቴላቸው፣ መዝናኛ ክበባቸው ወይም ሌሎች ድርጅቶቻቸው የሚመጡ ደንበኞች በሴቶች ጭን ይማረካሉ ብለው እንዴት አሰቡ? ብዬ ከራሴ ጋር ስጠያየቅ የራሴን ዓይኖችና የውስጤን ፍላጎቶች አስቤ ጥያቄዬን በውስጤ አከሰምኩት፡፡ ለልጅቱ ግን “የከስተመር ዓይን ይበዛባችኋል አይደል?“ አልኳት፡፡ የጥያቄዬን መልስ ጭኖቿ ላይ የያዘችው ይመስል ጭኖቿ ላይ አፍጥጬ፡፡

 

“በጣም“ አለችና እንደተለመደው አጭር ጉርድ ቀሚሷን ወደ ታች ወደ ታች ለማድረግ ሞከረች፡፡

“ጉዳዩን ለአሠሪዎቻችሁ አንስታችሁባቸው ታውቃላችሁ?“ የኔ ጥያቄ ነው፡፡

“ያማ በፍቃደኝነት ከሥራ ለመልቀቅ መንደርደር ነው“ አለችኝ፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ትላልቅ ሆቴሎችና የቱሪስት መዳረሻዎች አስተናጋጆቻቸው ከኢትዮጵያዊ ሥነ ምግባር ያፈነገጡ አለባበሶችን እንዳይከተሉ ደንብ መውጣቱን ሰምቻለሁ፡፡ ይሄው ደንብ ለምን በክልል ከተሞችና በሌሎችም ትላልቅ ከተማዎች ውስጥ እንደማይተገበር እያሰብኩ እያለሁ አስተናጋጇ “የእነዚህ እንደውም ተመስገን ነው አለችኝ“

“ምኑ ነው ተመስገን?“ ብዬ  ጠየኳት፡፡

 

“በቅርቡ ሥራ የለቀኩበት አንድ ሆቴል የደንብ ልብሳቸው ጭንን ብቻ ሳይሆን ደረትና ጡትንም የሚያሳይ ነው፤ በዚያ ላይ አስተናጋጇ ጡት ማስያዣ መልበስ እንደሌለባት የሚያስጠነቅቅ ያልተጻፈ ሕግም አላቸው፡፡ ሰው እንዴት እናት፣ እህትና ሚስት እያለው የሴት ልጅ ገላ ለአደባባይ የሚቀርብ ርካሽ ቁስ እንደሆነ አድርጎ ያስባል?“ ብላ በምሬት የተዋዛ ጥያቄዋን ወደኔ ይሁን ወደ ሁላችንም ባላውቅም ሰነዘረች፡፡

“ስህተት ነው“ ብዬ በለሆሳስ ተናገርኩና በውስጤ ራሴን መውቀስ ጀመርኩኝ፡፡ ለካስ እኔ ከካፌ ካፌ እያቀያየርኩ በዓይኖቼ የማመነዝርበት የሴቶች ጭን ሳይፈልጉት የተገለጠ ነው፤ ለካስ እኔ ለስለስ ያለ፣ ፍም የመሰለ እናም ሌላ እያልኩ ሳወድሰው የነበረው የሴቶች ጭን የእናቴ፣ የእህቴ ወይም የባለቤቴ ቢሆንስ ብዬ ያላሰብኩለት ነው፤ እያልኩ ውስጤን በፀፀት መዶሻ ቀጠቀጥኩት፡፡

 

“የሚገርምህ ነገር የኛን ጭን ብቻ ለማየት ሲሉ የሚመጡ ወንዶች እንዳሉ አረጋግጫለሁ፤ እነዚህ ጭን አምላኪ ወንዶች ታዲያ አንዴ በገቡበት ካፌ ውስጥ ሦስት ጊዜ ሻይ እየጠጡ ጨጓራቸውን ሲልጡ ይታያሉ“ አለችና ሳቅ አለች፡፡

 

ይቺ ልጅ አሽሙረኛ ቢጤ ሳትሆን አትቀርም በማለት ንግግሯን ከራሴ ጋር እያያያዝኩ በውስጤ አማኋት፡፡ ከዚህ በኋላ የሴቶችን ጭን ለማየት እያልኩ ከሆቴል ካፍቴሪያ እንደማልመላለስም ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ማድረግ ብችል የማደርገው የሴቶች ፍላጎትና መብት እንዲከበር ከሚጥሩት ጋር ሁሉ አብሬ መጣር እንደሆነ ለራሴ ነገርኩት፡፡

 

ይሄን ቃል ለራሴ በገባሁ በሴኮንዶች ውስጥ ግን ዓይኖቼ ወደ ልጅቱ ጭኖች ተሰድደው የልጅቱን ጭኖች ሲያደንቁ አገኘኋቸው፡፡ ይሄንኑ ድርጊቴን እንደ መለከፍ ወይም እንደ መረገም ቆጠርኩትና “ቃል የገባሁት ለልቤ እንጂ ለዓይኖቼ አይደለም“ የሚል መጽናኛን ተጠቀምኩኝ፡፡ የጭን ነገር እስከመቼ ሱስ፣ ጭንቀትና ሌላም እንደሚፈጥርብኝ መገመት ግን አልቻልኩም፡፡

 

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የጥር 26  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here