ወይዘሮ መሠረት ዓለሙ ይባላሉ:: ተወልደው ያደጉት በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዳንግላ ከተማ አቅራቢያ ነው:: የ49 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋዋ ወይዘሮ መሠረት ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን እንዲማሩ የአርሶ አደር ወላጆቻቸውን ድጋፍ አላጡም:: ከ12ኛ ክፍል ትምህርታቸው በኋላ በኮምፒዩተር ሳይንስ ዲፕሎማ ማግኘት ችለዋል፤ ትዳር የጀመሩትም በዚሁ ጊዜ ነበር::
ወ/ሮ መሠረት በገበያ አሥተዳደር (ማርኬቲንግ ማኔጅመንት) የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመያዝ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ እያሉ የሕይወት መስመራቸውን የሚቀይር አንድ ማስታወቂያ አነበቡ:: ማስታወቂያው በእንጅባራ ከተማ የመንጃ ፈቃድ ማሠልጠኛ ተቋም እንደተመሠረተ እና ተቋሙ መንጃ ፈቃድ ማውጣት ለሚፈልጉ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ክፍት መሆኑን የሚገልጽ ነበር። ይሄው ማስታወቂያ ቀልባቸውን የሳበው ወ/ሮ መሠረት የዲግሪ ትምህርታቸውን በይደር አቆይተው (ዊዝ ድሮዋል ሞልተው) መንጃ ፈቃድ ለማግኘት ሥልጠና ጀመሩ:: በተያዘለት የጊዜ ሠሌዳ ሥልጠናውን በብቃት አጠናቀውም መንጃ ፈቃዳቸውን አገኙ::
አሽከርካሪ መሆን የልጅነት ህልማቸው እንደነበረ የሚናገሩት ወ/ሮ መሠረት የመንጃ ፈቃዳቸውን በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ያቋረጡትን የዲግሪ ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ ችለዋል:: ዲግሪያቸውን በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ቢይዙም የሕይወት ጥሪያቸው ለአሽከርካሪነት ስለነበረ ባጃጅ ገዝተው የአሽከርካሪነት ሥራን ‘ሀ’ ብለው ጀመሩ::
ባለታሪካችን ሥራቸውን ከባጃጅ ወደ ታክሲ ከፍ በማድረግ ማሽከርከር ጀመሩ:: ለአምስት ዓመታት ያህል የሠሩባትን ታክሲያቸውን ሸጠው በሌላ ዘርፍ ቢሰማሩም አዋጭ ባለመሆኑ ወደ ቀደመ የአሽከርካሪነት ሙያቸው ተመልሰዋል:: ከሕይወት ጋር በመታገልና ሠርቶ በመለወጥ የሚያምኑት ወ/ሮ መሠረት ባሁኑ ወቅት ባጃጅ ገዝተው በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የታክሲ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ::
ወ/ሮ መሠረት ለሙያቸው መነሻ የሆናቸው የሦስት ሰዓት መንገድ በእግራቸው እየተመላለሱ መማራቸው እንደሆነ ያስታውሳሉ፤ በወቅቱ በተሽከርካሪ አጭር የሆነው መንገድ ለእግረኞች ምን ያህል ድካም እንደሚፈጥር እያዩ በማደጋቸው “ሳድግ አሽከርካሪ እሆናለሁ” የሚል ሃሳብን እንዳጫረባቸው ይገልጻሉ:: ሌላው ምንም እንኳን በኮምፒዩተር ሳይንስ ዲፕሎማ እና በማርኬቲንግ ማኔጅመነት ደግሞ ዲግሪያቸውን ቢይዙም በመንግሥት ወይም በግል ተቋም ውስጥ ተቀጥረው የመሥራት ፍላጎት አልነበራቸውም:: በዚሁም መሠረት ባጃጅ ገዝቶ በማሽከርከር ወደ ግል ሥራቸው አተኩረዋል::
ወ/ሮ መሠረት አሽከርካሪነታቸው የቤት ውስጥ ሥራዎችን ከማከናወን፣ ልጆቻቸውን ከመርዳት እና ከሌሎችም ማኅበራዊ ጉዳዮች አላራቃቸውም:: አብዛኛውን የቤት ውስጥ ሥራ በምሽት እንደሚሠሩ የገለጹት ወይዘሮዋ ልጆቻቸውን ቁርስ አብልተው፣ ወደ ትምህርት ቤት (በራሳቸው ባጃጅ) ለማድረስም እንዳልተቸገሩ ገልጸውልናል:: ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ መሠረት፤ ሁለቱ ወንድ ልጆቻቸው መንታ ሲሆኑ አንዷ ደግሞ እሳቸው እና ባለቤታቸው በፈቃደኝነት ያሳደጓት ልጃቸው ናት::
ብዙ ሴቶች እሳቸውን ባጃጅ ሲያሽከረክሩ ሲያዩዋቸው እንደሚገረሙና አንዳንዶችም እነሱም ቢጀምሩት በሙያው ይሳካላቸው እንደሆነ እንደሚጠይቋቸው ወይዘሮዋ አንስተዋል:: “ለአንድ ሥራ ሙሉ ፍላጎት ካለን ለመሥራት አንቸገርም:: እኔ አሽከርካሪ ለመሆን ከፈለኩ በኋላ የትኛውም ምክንያት ለሥራዬ እንቅፋት እንዲሆንብኝ አልፈቀድኩም” ሲሉም የዓላማ ሰው መሆን ካሰብንበት እንደሚያደርሰን ይመክራሉ:: “በተለይ ሥራን የወንድ እና የሴት ብሎ የመከፋፈል አስተሳሰባችን ከውስጣችን ሊወገድ ይገባዋል” ሲሉም ወ/ሮ መሠረት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
በአንድ ሥራ ላይ ስኬታማ ለመሆን ሥራውን መውደድ የግድ እንደሆነ የሚያነሱት ወ/ሮ መሠረት፤ እሳቸው 12ኛ ክፍልን ጨርሰው ሥራ ባልነበራቸው ወቅት የውኃ ዳቦ እየጋገሩ ያከፋፍሉ ነበር:: በሥራውም ጥሩ ገቢ ያገኙ እንደነበረ አስታውሰዋል:: “ሥራን ሳይንቁ መሥራትን መርኃችን ልናደርገው ይገባል” የሚሉት ወይዘሮ “ብዙ ሥራ የለንም” የሚሉ ወጣቶች ከእሳቸው ሕይወት በከፊልም ቢሆን መማር እንደሚችሉ ጠቁመዋል::
ባለቤታቸው በእሳቸው የአሽከርካሪነት ሙያ ደስተኛ እንዳልነበሩ የሚያስታውሱት ወ/ሮ መሠረት፣ የባለቤታቸው ምክንያት የአሽከርካሪነት ሙያ አደጋ ያለውና ሕይወትንም ያሳጣል ከሚል ሥጋት እንደሆነ ይናገራሉ:: ሴት ባለትዳር ሆኖ በባጃጅ አሽከርካሪነት ሙያ ውስጥ መሠማራት የራሱ የሆነ ፈተናዎች እንዳሉት የጠቆሙት ወይዘሮዋ፤ ዓላማን ከግብ ለማድረስ ግን ጽናትን እንደ መሣሪያ መጠቀም ማስፈለጉን ይገልጻሉ::
“ሰዎች ‘አንቺ ባጃጅ ይዘሽ አስፋልት ላይ የወጣሽው ሌላ ፍላጎት ኖሮሽ እንጂ የባልሽ ደመወዝ አንሶሽ አይደለም‘ የሚለውን አጥንት ሰባሪ አስተያየት እያስተናገድኩ በሥራዬ የቀጠልኩት ባለቤቴንም ሆነ ተሳዳቢዎችን በምግባሬ እና በሥራዬ አሳምኛቸው ነው” ያሉን ወ/ሮ መሠረት፤ በየትኛውም ሙያ ውስጥ የሚያጋጥምን ጊዜያዊ ችግር ተቋቁሞ ማለፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል::
“ባለቤቴ የሎደር አሽከርካሪ ነው፤ እኔም መሆን እፈልግ የነበረው በሱ ደረጃ የሎደር አሽከርካሪ መሆንን ነበር፤ ነገር ግን ባለቤቴ እንኳንስ እንደሱ የሎደር አሽከርካሪ እንድሆን ቀርቶ ባጃጅም እንዳሽከረክር ፍላጎት አልነበረውም:: መንጃ ፈቃዴን ያወጣሁትም ባለቤቴ በመስክ ሥራ ላይ እያለ ነው:: ባለቤቴ ሙያዬን ምን ያህል ከልቤ እደምወደው ካወቀ በኋላ ግን ጥንቃቄ እንዳደርግ ከመምከር አልፎ ሙያዬን መቃወሙን አቁሟል:: ልጆቼም በሥራዬ ደስተኞች ናቸው”በማለትም ለሙያው እርሳቸውም ሆነ ቤተሰቦቻቸው አጋዦቻቸው መሆናቸውን ተናግረዋል::
“ከዳንግላ ከተማ መጥቼ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ታክሲ አሽከረክር የነበርኩት ሁለተኛዋ ሴት እኔ ነበርኩ፤ ከእኔ በፊት አንዲት ልጅ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ታክሲ ታሽከረክር እንደነበረ ሰምቻለሁ፤ ከእኔ በኋላ ደግሞ አራት ሴት የታክሲ አሽከርካሪዎች በዘርፉ ተሰማርተዋል:: “በአሽከርካሪነት ሙያዬ ውስጥ ሴቶችን የማሳነስ እና የማንጓጠጥ ነገሮች የሉም አልልም፤ ያን የሚያደርጉ ሰዎች ግን ከግንዛቤ እጥረት እንጂ ከክፋት አይደለም ብዬ ማሰብን እመርጣለሁ:: አሁን ላይ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ሴቶች ታክሲም ሆነ ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ሲያሽከረክሩ ማየት ተለምዷል:: በሙያው ላይ ላሉ ሴቶች የሚሰጣቸው ክብርም ከወትሮው የተሻለ ሆኗል” በማለትም ኅብረተሰቡ ለሴት አሽከርካሪዎች ያለው ግምት መሻሻሉን አረጋግጠዋል::
ወ/ሮ መሠረት በዓመት በዓል ወቅት ዶሮ መሥራት፣ ጠላ መጥመቅ እና መሰል የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለአንድም ዓመት ሳያዛንፉ መፈፀማቸውን ይገልጻሉ፤ ከቤት ውጪ ጥሩ አሽከርካሪ እንደሆኑት ሁሉ በቤት ውስጥም ጥሩ ባለሙያ እና ጥሩ እናት ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል::
የሰላም እጦቱ፣ የቤንዚል እጥረቱ፣ የሰዓት ገደቡ እና ሌሎችም ችግሮች አሁን ላይ የአሽከርካሪነት ሙያን ፈተና ላይ እንደጣሉት የገለጹት ወ/ሮ መሠረት፤ ያም ቢሆን ግን ከከት ቁጭ ብለው የባለቤታቸውን ገቢ ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸውን የሥራ እንቅስቃሴ በማድረጋቸውና ገቢ በማመንጨታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ነግረውናል:: ወደ ፊት ደግሞ የተሻለ ሰላም ሲገኝ በተሻለ መልኩ እየሠሩ ራሳቸውን ለመለወጥ ይበልጥ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸውልናል::
“እኔ በተፈጥሮዬ የበታችነት ስሜት እንዲያድርብኝ የምፈልግ ሰው አይደለሁም፤ ወንዶች ከሴቶች የሚሻሉበት በተፈጥሮ የተቸሩት ተክለ ሰውነት ቢኖራቸውም ሴት ከወንድ ታንሳለች የሚል ሃሳብ ፈጽሞ የለኝም” የሚሉት ወ/ሮ መሠረት፤ ወላጆቻቸው አርሶ አደሮች በመሆናቸው እና እናታቸውን ጨምሮ ሌሎችም የአከባቢያቸው ሴቶች በግብርና ሥራ ላይ በስፋት ስለሚሳተፉ የሥራ እና የመንፈስ ጥንካሬን ከእነሱ መውረሳቸውን ይናገራሉ:: በዚህም ምክንያት ሴት ልጅ የማትሠራው ሥራ አለ ብለው እንደማያምኑም አንስተዋል::
ወ/ሮ መሠረት ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በምሽት ታክሲ እያሽከረከሩ በነበረበት ወቅት አንድ ቀን መጥፎ አጋጣሚ ገጥሟቸዋል፤ “አራት ሌቦች ሁለቱ መሀል አስፋልት ላይ ቆመው፣ ሁለቱ ደግሞ ከአስፋልቱ ወጥተው በመቆም ይጠባበቁኛል:: መጀመሪያ ላይ ሁለቱ ሰዎች የመሰሉኝ መሀል አስፋልት ላይ የቆመ ረዥም ነገር እንጂ ሰዎች ወይም ሌቦች አልመሰሉኝም ነበር፤ እየቀረብኋቸው ስሄድ ግን ሰዎች መሆናቸውን ተገነዘብኩ::
“ለእነዚያ ሁለት ሰዎች ረዥም እና አጭር መብራት እያበራሁ አስፋልቱን እንዲለቁልኝ ባስጠነቅቃቸውም ፈቃደኛ አልሆኑም:: ሰዎቹ በምሽት በዚህ መልኩ ተሽከርካሪ የሚጠብቁት ለመዝረፍ እንጂ ለመሳፈር እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን አልቸገረኝም:: በውስጤ ከራሴ ጋር ተነጋገርኩ፤ ታክሲዬን ባቆምላቸው ራሴን ከመዘረፍ፣ ለጾታዊ ጥቃት ከማጋለጥ እና ንብረቴንም ከማዘረፍ ስለማላመልጥ የወሰንኩት በፍጥነት ገጭቻቸው ለማለፍ ነው::
“በውሳኔዬ መሠረት የአደጋ ማስጠንቀቂያ መብራት (ሃዛርድ) እያበራሁ፣ ጥሩንባ (ትላክስ) እያስጮሁኩኝ እና በፍጥነት እያሽከረከርኩ ስጠጋቸው ሁለቱ ሰዎች ልገጫቸው እንዳሰብኩ በማወቃቸው ከአስፋልቱ ላይ በፍጥነት ገለል አሉልኝ፤ ያም ቢሆን ግን አራተኛ ማርሽ አስገብቼ በፍጥነት እየተጓዝኩ ስለነበረ ታክሲዬ አደጋ ውስጥ ሊጥለኝ ምንም አልቀረኝም ነበር” በማለት ነበር ከተደቀነባቸው አደጋ የወጡበትን ዘዴ ያካፈሉን::
ወ/ሮ መሠረት የታክሲ አሽከርካሪ በነበሩበት ወቅትም ሆነ አሁን ባጃጅ እያሽከረከሩ ብዙ ሌቦች ከተሳፋሪዎች ላይ ገንዘብ፣ ስልክ፣ ቦርሳ ወይም ሌላ ንብረት ሊሰርቋቸው ሲሉ ማስጣል እንደቻሉም ገልጸውልናል:: ሠርቶ መለወጥ እንጂ ሠርቆ መለወጥን ለሚያስቡ ወጣቶችም ቀና የሆነ ምክራቸውን አጋርተዋል::
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም