ካዳስተር ምንድን ነው?

0
660

ካዳስተር ማለት የመሬት ይዞታን መሠረት ያደረገ የመሬት መረጃ ሥርዓት ነው። የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚንስቴር በማሕበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው የመሬት ባለይዞታው ማንነቱን የሚገልጽ የቀበሌ መታወቂያ፣ ቦታው በፍርድ ቤት ክርክር የሌለበት፣ የባንክ ዕዳ የሌለበት መሆኑን እና ትክክለኛ የቦታውን ልኬት የሚያሳይ የቅየሳ ሰነድ ይዞ በመቅረብ ማስመዝገብ ይችላል። ሙሉ በሙሉ የተሟላ መረጃ ካለው ከአምስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት (ማስረጃን) ማግኘት ይችላል።

የባለይዞታው የመሬት መረጃ  በዋናነት በሁለት መልኩ ይሰባሰባል። ከእነዚህም አንዱ የካርታ መረጃው የይዞታውን መገኛ ቦታ፣ ወሰኑን፣ ስፋቱን፣ ቅርጹን፣ አጐራባች ይዞታዎችን እና አዋሳኝ መንገዶችን የሚያሳይ ነው፡፡ ሌላው የባለይዞታው ማንነት (ሥም፣ አድራሻ፣ ጾታ፣ የጋብቻ  ሁኔታ)፣ በይዞታ ላይ ያለው መብት፣ ክልከላ እና ኃላፊነት፣ ቦታው የሚሰጠው አገልግሎት እና ደረጃውን ያካትታል።

ካዳስተር ሕጋዊ፤ ፊስካል እና ሁለገብ ወይም ሁሉን አቀፍ ተብሎ በሦስት ይከፈላል። ሕጋዊ ካዳስተር ተብሎ የሚጠራው ለእያንዳንዱ ሕጋዊ ወሰን ለተለየለት ይዞታ፣ የይዞታ መብት፣ ክልከላ እና ኃላፊነት የሚያመለክት መረጃ ከይዞታው ካርታ ጋር አጣምሮ የያዘ ወቅታዊ የመሬት ይዞታ መረጃ አያያዝ ሥርዓት ነው።  ሕጋዊ ካዳስተር እንደ አስፈላጊነቱም የትኛው ይዞታ በማን እና በምን አግባብ ተይዟል? የሚለውን በማጣራት የባለይዞታው የይዞታ ዋስትና የሚረጋገጥበት አሠራር ነው።

በይዞታው ላይ ስላረፈው ቋሚ ንብረት ዝርዝር መረጃ እና የመሬቱን ወቅታዊ ግምት ከይዞታው ካርታ ጋር የሚይዘው የካዳስተር አይነት ደግሞ ፊስካል ካዳስተር ይባላል፡፡  ለቦታ እና ለንብረት ግብር ክፍያ የሚያገለግል ሥርዓት ነው።

ሁለገብ ወይም ሁሉን አቀፍ የካዳስተር ዓይነት የሚባለው ዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝ ዘዴ  በሁለቱ የካዳስተር ዓይነቶች የተገለፁትን መረጃዎች በአንድ ላይ የሚይዝ ነው።  በተጨማሪም የመሠረተ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ሌሎች መረጃዎችን እና ካርታን አካቶ የሚይዝ የመረጃ ሥርዓት ነው።

ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃው እንደሚያመላክተው በተለይ በከተሞች መተግበር የጀመረው ሕጋዊ ካዳስተር የመሬት መረጃን በዘመናዊ መንገድ በማደራጀት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋለውን የባለይዞታውን እና የተቋሙን የተወሳሰበ ችግር በመሠረታዊነት ይፈታል። ከዚህ ባለፈ የካዳስተር ሥርዓቱ በሚፈጥረው የመረጃ ምሉዕነት በከተማ መሬት ይዞታ የሚስተዋለውን  በዜጐች መካከል የሚፈጠር የፍርድ ቤት ክርክር ይቀንሳል። በመሆኑም ባለይዞታው ከሚያወጣው ወጭ፣ ከሚደርስበት መጉላላት እና ድካም ይድናል፤ ትክክለኛ ፍርድም ያገኛል።

ካዳስተር ለባለ ይዞታዎች የመሬት መረጃ ሲፈልጉ ውጣ ውረድ ሳይገጥማቸው በቀላሉ እንዲያኙ ያስችላቸዋል። ከመሬት ጋር ተያያዞ የሚያጋጥመውን የመረጃ ጉድለት ሰበብ በማድረግ ጥቂቶች ይበለጽጉበት የነበረውን  እና ሕጋዊ ባለ ይዞታዎችን ለተለያዩ ጉዳቶች ይዳርግ የነበረውን የአሠራር ችግር የሚያስቀር አሠራር ነው።

በተለይ ከተማ አስተዳደሮች የሚያስተዳድሩትን መሬት ቆጥረው እንዲያውቁ፣ የትኛውን መሬት ለየትኛው አገልግሎት ማዋል እንዳለባቸው አቅደው ለመምራት እና በተገቢው መንገድ ለማደራጀት ከፍተኛ እገዛ እንዳለው በመረጃው ተጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም የከተማ  አስተዳደሮች ዋነኛ ሀብት የሆነውን የመሬት ግብር እና ኪራይ በተገቢው መንገድ እንዲሰበስቡ ያስችላል። ይህም ገቢውን ለከተሞቻቸው መሠረተ ልማት ግንባታ በማዋል እና በማሳደግ ነዋሪውን የልማቱ ተጠቃሚ ያደርጋል።

የመሬት መረጃን በተደራጀ እና በዘመነ መንገድ መያዝ መንግሥት አዳዲስ ፖሊሲዎችን፣ አሠራሮችን እና ሕጐችን ለማመንጨትም ግብዓት ሆኖ እንደሚያገለግል መረጃው ጠቁሟል።

ካዳስተር የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥን ባለሀብቶች እምነት ስለሚያሳድር ሀብታቸውን ልማት ላይ ያፈሳሉ፣ ይህን ተከትሎም ነዋሪው ተጠቃሚ ይሆናል፣ ከተሞች ያድጋሉ፣ የልማት ማዕከል ይሆናሉ።

ሕጋዊ ካዳስተር በመረጃ ላይ በመመርኮዝ በተለይ በከተሞች የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የቋሚ ንብረት ሃብት ወደ ገበያ እንዲገባ ከማስቻል ባለፈ ዜጎች የዕድገቱ አካል እና ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው። ይህ ደግሞ መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ እና ልማታዊነትን ለማረጋገጥ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ዘመናዊ እና የተደራጀ የከተማ የመሬት ይዞታ ምዝገባ ሥርዓት እውን መሆን ውስን የሆነውን የከተማ መሬት በተገቢው መንገድ ለተገቢው አገልግሎት ለማዋል ብሎም በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለመስጠትም ያስችላል። ከዚህም በላይ የኅብረተሰቡን የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ዋስትናን በማረጋገጥ የከተሞች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስቀረት ዋነኛ መፍትሔ ነው።

የከተማ መሬት መረጃ ሥርዓትን በከተሞች ተግባራዊ ማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉትን የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች ለማድረቅ፣ ለልማት የተመቻቸ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመፍጠር፣ ሕገ ወጥነትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል፣ የከተሞችን የገቢ አቅም ለማሳደግ፣ በይዞታ የመጠቀም መብትን እና የንብረት ባለቤትነት ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ቀልጣፋ፣ ግልፅና ተጠያቂነት ያለበት የመሬት አስተዳደርን ለማረጋገጥ እንዲሁም የከተማ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት እና በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያስችል ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ነው።

በከተሞች ትልቁና ዋነኛ ሀብት መሬት ነው፡፡ እነዚህ መሬቶች ደግሞ የተዛባ ሥርዓት ያላቸው፣ የፋይል አደረጃጀቱም ጉራማይሌ የሆነበት፣ ለብዙ አደጋዎች የተጋለጠ፣ አልፎ ተርፎም የመልካም አስተዳደር ችግር መፈልፈያ የሆነበት እና ለሙስና ትልቁን በር የከፈተ ነው፡፡ ይህንን ሀብት ከዚህ ሁሉ አደጋ ጠብቆ ሥርዓት ባለው ሕጋዊ ካዳስተር መዝግቦ በመያዝ ችግሮቹ ተፈትተው ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ያስችላል። መሬትን በዘፈቀደ አሳልፎ እንዳይሰጥ ያደርጋል።፡፡

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here