ርዕደ መሬት በታሪክ ዕይታ

0
141

~ ካለፈው የቀጠለ

ርዕደ መሬት አደገኛ ከሆኑት የተፈጥሮ አደጋዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር እድሜ እንዳለው፣ ክስተቱን በአግባቡ ለማጥናት ደግሞ ሳይንሳዊ ምርምር የተደራጀ ግንዛቤ ማስጨበጥ መቻሉን እና በምድራችን በየዘመኑ የተከሰቱ ርዕደ መሬቶች የትኞቹ እንደነዘሩ ባለፈው ሳምንት አስነብቦናል። ቀጣዩ እና የመጨረሻው ክፍል ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ የተከሰቱ ርዕደ መሬቶችን ይዳስሳል፤ መልካም ንባብ።

የኢትዮጵያ ጥንታዊ የታሪክ ፀሐፊዎች የጌቶቻቸውን የልደት ቀን ወይም የንግሥና ቀን ከአንዳች አስደናቂ የተፈጥሮ ክስተት ጋር ማገናኘት ይወዱ ነበር። ዘመናዊ የታሪክ ፀሐፍት የጥንት ባልደረቦቻቸውን ምናልባትም የጌታቸውን የሕይወት ታሪክ ለማሳመር ሲባል የተወሰኑ የመሬት መንቀጥቀጦችን እና የበራሪ ኮከቦችን መከሰት በየፁሁፋቸው ይጨምሩበት እንደነበር ይጠረጥሯቸዋል። ነገር ግን በአማካይ በየቀኑ ሁለት ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ በሚከሰትባት ምድር የፈጠራ ሀሳብ መፍጠር እና መጨመር አያስፈልጋቸውም ።

ዛሬ ላይ በአዲሱ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የጥንት የታሪክ አዋቂዎች የመዘገቧቸው እውነታዎች ሊገኙ ይችላሉ። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ የርዕደ መሬት ታሪክ በሚል ርእስ ፈረንሳዊው ፒየር ጉዊን የፃፈው አዲስ የኢትዮጵያ መዋእለ ዜና የተደራጀ ማስረጃን ይዟል። ፒየር ጉዊን አዲስ አበባ ያለው ጂኦሎጂካል ኦብዘርቫቶሪ መስራችና ዳይሬክተር ሲሆን የኢትዮጵያ ጅኦፊዚክስ አባትም ይባልለታል።

ፈረንሳይ ሀገር በሞንትሪል ከተማ የተወለደው ጉዊን ስለኢትዮጵያ ውስጣዊ የመሬት እንቅስቃሴ ብዙ እውቀት ካላቸው በጣት ከሚቆጠሩ ሰዎች አንዱ ነው። በኢትዮጵያ ለ30 ዓመታት ያህል እንደ ጅኦፊዚስት እና እንደ አስተማሪ ሆኖ አገልግሏል። በርካታም የምርምር ስራዎችን ፅፏል።

በ1968 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፒየር ጉዊን የመጀመሪያ ስራው የሆነውን ‘ሴስሚክ ዞኒንግ ኢን ኢትዮጵያ’ የተሰኘ መፅሀፍ አሳትሟል። መፅሃፉ የኢትዮጵያ የርዕደ መሬት ካርታ ነው።  32 ከተሞችን እና መንደሮችን እንዲሁም 60 ግድቦችን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 650 አካባቢዎች የተከሰቱ የርዕደ መሬት ማግኒቲዩድ እና የመከሰት እድሎችን ይዟል። በኢትዮጵያ የመሬት ንዝረት አደጋዎችን መመዘን ካለው ድግግሞሽ እና አብዛኛው ማህበረሰብ ከተራራ ስር የሚኖር ከመሆኑ አንፃር የመሬት ንዝረት ስጋትን ማጥናት በተለየ ሁኔታ አስፈላጊ ነው። በርዕደ መሬት የተነሳ በሚፈጠር የመሬት መንሸራተት መንደሮች ሙሉ በሙሉ የሚወድሙባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ተመዝግበዋል። በ1834 ዓ.ም  አንኮበር ሙሉ በሙሉ በርዕደ መሬት የተነሳ በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት ወድማ ነበር።

በአንድ የመናዊ የታሪክ አዋቂ የተፃፈ አንድ መረጃ እንደሚያሳየው የመጀመሪያው የከርሰ ምድር እንቅስቃሴ የተመዘገበው በቀይ ባህር ጠረፍ  በ1392 ዓ.ም ነበር።  በዚህ እሳተ ገሞራ በርካታ ተራሮች እና ሰፊ የእርሻ መሬት መፈጠር እንደቻለ ተጠቅሷል በፁሁፉ።

በኢትዮጵያ ርዕደ መሬት በተደጋጋሚ የሚከሰት ሲሆን በዋናነት በአፋር ምእራባዊ ጠረፍ እና  ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ነው።

የኢትዮጵያ የርዕደ መሬት ታሪክ አጀማመር እንደሚያሳየው በ1836 ዓ.ም የርዕደ መሬት ክስተት በአንኮበር የታየበት እና ተከትሎ የተፈጠረው ርዕደ መሬት ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ እንዳወደማት ተዘግቧል። በ1846-47 ዓ.ም  ደግሞ የንዝረት ማዕከሉ ወደ አሸንጌ ሐይቅ ተሻግሮ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። በ1876 ዓ.ም የደረሰው ርዕደ መሬት ማእከሉ በምፅዋ ጠረፍ የታየ ሲሆን ከተማዋ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድታ እንደነበር የፒየር ጉዊን መፅሃፍ መዝግቦታል። በ1898 ዓ.ም ደግሞ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከ75 እስከ 100 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው የሲርና አውራጃ በርዕደ መሬት መዐት ተናውጣ ነበር።  ይህ  ክስተትም በሬክተር ስኬል 6.8 የተለካ ነበር። ከመሬት ነውጡ በኋላ የአዲስ አበባ ነዋሪ በፍርሃት ተሸብሮ ነበር። ንዝረቱ አደገኛ የነበረ ቢሆንም የጎላ ጉዳት ግን አላደረሰም። ምክንያቱም ከተማዋ ከተቆረቆረች ገና 10 ዓመቷ ስለነበር ብዙም ያደገች ባለመሆኗ የሚፈርስ ሕንፃ ያልነበረ  መሆኑን ፒየሪ ጉዌን ፅፎታል። ይህም ክስተት በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተከሰቱት ትልቁ እና ንዝረቱ በስፋት እንደተሰማ  ይነገርለታል።

በ1952 ዓ.ም 6.3 የሚለካ ርዕደ መሬት ከሻሸመኔ በስተ ምእራብ አቅራቢያ ያለን ቦታ መትቶት ነበር። በቀጣዩ ዓመትም ንዝረቱ ማእከሉን ወሎ በማድረግ ማጀቴን አውድሞ፤ ካራቆሬን ክፉኛ ጎድቷት አልፏል። የወሎዋ መዲና ደሴ በ1956 ዓ.ም በርዕደ መሬት እንደተመታችም ታሪክ ያስረዳል። መረጃው እንደሚያሳየው ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ጋር ሲነፃፀር ይህ አካባቢ 75 በመቶው የንዝረት መነሻ እንደነበር ነው።

ይህ የንዝረት ቀበቶ እንደ አለመታደል ሆኖ ብዙ ሕዝብ ከሚኖርባቸው አካባቢዎች ጋር የተቆራኘ ነው። የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ በሚገናኝበት አፋር ላይ ከፍተኛ የእሳተ ገሞራ እና ርዕደ መሬት ይስተዋልበታል።

ካለፉት አሥር ዓመታት በፊት ከተከሰቱት ርዕደ መሬቶች ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበው ዘንድሮ በአፋር ሰሜን አዋሽ ላይ የተከሰተው በሬክተር ስኬል 5.7 የተለካው ርዕደ መሬት ነው። ከአዋሽ ሰሜን አካባቢ ጀምሮ 54 ኪሎ ሜትር የሚያካልል 8 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ያለው ርዕደ መሬት ተመዝግቧል።

ከዛሬ 70 ዓመታት በፊት በደቡብ ኢትዮጵያ ጊዶሌ አካባቢ 6.0 የሚለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ ጉዳት ደርሶ ነበር። በሌላ በኩል ከዛሬ 63 ዓመታት በፊት በአማራ ክልል አቦምሳ ላይ የደረሰው 5.9 የተለካው ርእደ መሬት የሚታወስ ሲሆን ትልቅ ጉዳት እንዳስከተለም ይነገራል።

ጠንካራ የሚባለው በ1981 ዓ.ም ነሀሴ ውስጥ ከጅቡቲ በስተምእራብ 133 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘው ዲኪል ላይ 6.5 በሬክተር ስኬል የተለካው የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሆነ ተመዝግቦ ይገኛል። ይህ ከ1892 ዓ.ም ወዲህ 100 ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተከሰተው ትልቁ ርዕደ መሬት ተብሎለታል።

ኢትዮጵያ እስካሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ርዕደ መሬቶች አጋጥመዋታል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ በርካታ ርዕደ መሬት ተከስቷል። የዘርፉ ምሁራን  ያለፉትን ክስተቶች በመገንዘብ ጉዳትን በሚቀንስ አግባብ መዘጋጀት እንደሚገባ ያሳስባሉ።

 

(መሠረት ቸኮል)

በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here