የእንስሳት መኖ ለምርታማነት

0
191

ኢትዮጵያ የቀንድ ከብት፣ በግ፣ ፍየል እና ግመልን ጨምሮ ከ174 ሚሊዮን በላይ የእንስሳት ሃብት ያላት ሀገር መሆኗ ይነገርላታል። ከአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ማስፋፊያ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው የእንስሳት እርባታ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 47 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል። ይሁን እንጂ የሀገራችን የእንስሳት ሃብት የምርታማነት ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ ለምግብ ዋስትና እና ለምጣኔ ሃብት ዕድገት የሚጠበቀውን ያህል አስተዋፅኦ እያበረከተ አለመሆኑ ይነሳል።

የእንስሳት ሃብቱ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል። የእንስሳት ሃብቱ ከፍተኛ የገበያ እንቅስቃሴ  እና ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር አይነተኛ ሚናን ይጫወታል።

ዘርፉ በምጣኔ ሀብት ዕድገት ያለው አስተዋፅኦም ከፍተኛ ነው። የእንስሳት ሃብት ከምግብነት ባሻገር ተረፈ ምርታቸው የመሬት ለምነት እንዲሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታን ይሰጣል።

በሌላ መልኩ ከኋላቀር አሠራር፣ ከዝርያ አለመሻሻል፣ ከመኖ እጥረት፣ ከገበያ ተደራሽነት እና ተወዳዳሪ ምርታማነት ጋር በተያያዙ ችግሮች ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም ካላት የእንስሳት ሃብት ብዛት አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረትም አነስተኛ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል። በመሆኑም ዘርፉ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለውጪ ምንዛሪ ያለውን ድርሻ በመገንዘብ ችግሮችን መፍታት  የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው  ተግባራዊ  እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። በአማራ ክልልም ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ለውጥ እንዲመጣ እየተሠራ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ክልሎች መካከል ከፍተኛ የእንስሳት ቁጥር የሚገኝበት የአማራ ክልል ለዳልጋ ከብት፣  (ለበግ፣ ለፍየል፣)ለዶሮ፣ ለዓሳ እና ለንብ ሃብት ልማት እጅግ ምቹ እንደሆነ ይታወቃል።

በክልሉ እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ማስፋፊያ ጽ/ቤት የመኖ ልማት፣ ዝግጅት እና አጠቃቀም ባለሙያው አቶ አበበ ምትኬ ለበኵር  እንደገለጹት ክልሉ ለእንስሳት እርባታ እና ለሰብል ልማት ምቹ የአየር ንብረት፣ በቂ የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር ውኃ ባለቤት ነው። አርሶ አደሩም ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን የእንስሳት ልማቱን የገቢ ምንጭ አድርጎ እየሠራበት ያለ ዘርፍ ነው። ክልሉ ባለው ከፍተኛ የእንስሳት ቁጥርም ከጠቅላላው የሃገሪቱ የእንስሳት ሃብት ብዛት 30 በመቶ  ሽፋን አለው::

ክልሉ ባለው የእንስሳት ሃብት እና ፀጋ ልክ አልምቶ በመጠቀም በኩል መሠረታዊ ችግሮች  መኖራቸውን ባለሙያው ጠቁመዋል:: በመሆኑም   ዘርፉን  የተረዳ እና የተገነዘበ አመራር እና ባለሙያ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

መሠረተ ልማት፣ የገበያ ትሥሥር፣ መኖ፣ ዝርያ ማሻሻል፣ የእንስሳት በሽታ፣ ኋላ ቀር እና ልማዳዊ የአረባብ ዘዴ ዘርፉን ከፈተኑት መሠረታዊ ችግሮች መካከል መሆናቸውንም  ባለሙያው አመላክተዋል። ምንም እንኳን በሃገሪቱ በእንስሳት ሃብት ተጠቃሚነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ መሆኑ ቢገለጽም ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ለእንስሳት ሃብቱ ልማት የሚደረጉ የጤና ጥበቃ፣ የዝርያ ማሻሻል፣ የመኖ ዝግጅት… መሻሻሎች ቢታዩም ገና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ባለሙያው አብራርተዋል። ዘርፉን በጥራት እና በስፋት በዘመናዊ መልኩ በማሳደግ እና በኢንቨስትመንት ደረጃ ከማልማት በተጨማሪ የእንስሳት መኖ በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት ግንባር ቀደም ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።

የእንስሳት ዘርፉን ለማዘመን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም እየተመዘገበ ያለው ውጤት ወቅቱ ከሚጠይቀው አኳያ አነስተኛ መሆኑን የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽ/ቤት መረጃ ያሳያል። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቶች የእንስሳት መኖ ጥራት እና አቅርቦት ማነስ፣ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች አለመስፋፋት እና የእንስሳቱ አያያዝ አለመዘመን ተጠቃሾች ናቸው። የእንስሳት መኖ አጠቃላይ ለእርባታ ተግባር ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከ60 እስከ 80 በመቶ  እንደሚይዝ መረጃው አክሏል።

አቶ አበበ እንዳብራሩት በክልሉ የሚገኘው ይህ ከፍተኛ የእንስሳት ቁጥር  የሚያስፈልገውን መኖ በመጠን እና በጥራት ለማምረት የሚያስችሉት መልካም አጋጣሚዎች ቢኖሩም ፀጋዎችን ተጠቅሞ በአግባቡ በማምረት በኩል ደግሞ ክፍተቶች ይስተዋላሉ::

ለእንስሳት ሃብት ልማቱ መኖ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዝ መሆኑን ያነሱት ባለሙያው የመኖ መገኛ ምንጮችም በርካታ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። ከነዚህም መካከል የሰብል እና የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርት፣ የግጦሽ መሬት፣ ለሰው ምግብነት የሚውሉ ምርቶች እንዲሁም የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን ጠቅሰዋል።

ጽ/ቤቱ የመኖ ብዜት ማዕከላትን እና የመኖ ችግኝ ጣቢያዎችን በማቋቋም  በማሕበራት እና በግለሰቦች የመኖ ዝርያዎች እየለሙ መሆኑን አስረድተዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት የአርሶ አደሩ ግንዛቤ የእንስሳት መኖ ልማትን በተመለከተ ዝቅተኛ እንደ ነበር ያስታወሱት ባለሙያው አሁን ላይ የሚያስገኘውን ጥቅም በመረዳት የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን በማልማት ላይ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል::  በተለይም በሰሜን እና ደቡብ አቸፈር ወረዳዎች የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን አልምተው በመጠቀም ለውጥ ያመጡ አርሶ አደሮች አብነት መሆናቸውን አንስተዋል:: ከእነዚህ የመኖ ዝርያዎች መካከል ሮደስ፣ ዲሾ፣ ናፒር፣ ላብ ላብ፣ ፒጂምፒ፣ ከሎባስ /ዝሆኔ/ ሳር እና ሌሎች የሳር ዝርያዎች በበርካታ አርሶ አደሮች እየተለመዱ እና ጥቅም እየሰጡ ናቸው ብለዋል::

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በአማራ ክልል በስፋት እና በብዛት ለእንስሳት መኖ በመሆን ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የሰብል ተረፈ ምርት ሲሆን 46 በመቶ ያህሉን ይሸፍናል። ሆኖም በውስጡ የያዘው የንጥረ ነገር ይዘቱ እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ለስጋ፣ ለወተት እና ለዕንቁላል ምርት የሚሰጠው ውጤት አነስተኛ ነው። በመሆኑም ይህን የሰብል ምርት አሻሽሎ መጠቀም አስገዳጅ መሆኑን አብራርተዋል።

ሌላው ለእንስሳት መኖ እያገለገለ የሚገኘው የግጦሽ መሬት ሲሆን በአግባቡ ባለመጠቀም ምክንያት ልቅ የሆነ የግጦሽ መሬት መጠቀም ውጤታማ እያደረገው አለመሆኑን ተናግረዋል:: በመሆኑም የግጦሽ መሬትን አሻሽሎ መጠቀም እና የማሻሻያ ዘዴዎችን መከተል ይገባል ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን አጋርተዋል። የግጦሽ መሬትንም የወል እና የግለሰብ በሚል በመለየት ደብተር እየተዘጋጀ መሆኑን አመላክተዋል።

ምጥን መኖን ቀደም ባሉት ጊዜያት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረበት አሠራር ትክክል ያልሆነ እና በባለሙያ የታገዘ እንዳልነበርም ባለሙያው አስረድተዋል። በዚህም መኖ የንጥረ ነገር ይዘቱ /ፕሮቲን/ በትክክል ሳይጠና  እየተዘጋጀ ሲቀርብ እንዳልነበር አመላክተዋል:: ይህም በእንስሳት ልማቱ ላይ የሚጠበቀውን ውጤት እንዳያመጣ ማድረጉን ገልፀዋል። ገንቢ ንጥረ ነገር፣ ኀይል ሰጭ፣ የማዕድን እና የቫይታሚን ይዘቱን አመጣጥኖ ያልያዘ መኖ ለእንስሳት ልማቱ ውጤት ያመጣል ብሎ ማሰብ እንደማይቻል ተናገረዋል። ከኢንዱስተሪ ተረፈ ምርት እና ለሰው ምግብነት ከሚውሉ ምርቶችም የእንስሳት መኖ እየተዘጋጀ ሲሆን ፋጉሎ እና ፉርሽካ ለዚሁ ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት  በክልሉ የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ እየተሠሩ ያሉ መልካም ሥራዎችን ባለሙያው አቶ አበበ ጠቅሰዋል። ባሁኑ ወቅት 32 ፈቃድ የተሰጣቸው መኖ  የሚያቀነባብሩ ዩኒየኖቾ፣ የልማት ድርጅቶች እና የግል የመኖ ማቀነባበሪያዎች እንዳሉ አክለዋል። ይህም እንስሳቱ የሚፈልጉትን ንጥረ ነገር ይዘታቸው እየተመጠነ እንዲደርሳቸው በማድረግ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል።

ሌላው በእንስሳት ሃብቱ ላይ ጫና እያሳደረ የሚገኘው በክልሉ የሚከሰቱ ግጭቶች እና በዝናብ እጥረት ሳቢያ  ድርቅ ነው፤ ይህም መኖን በተገቢው መንገድ ለማምረትም ሆነ ለማሰራጨት እንቅፋት መፍጠሩን  አቶ አበበ አመላክተዋል:: ችግሩን በጊዜዊነት ለመፍታትም አርሶ አደሮች እንስሳቸውን ወደ አጎራባች ወረዳዎች ይዘው እንዲሄዱ የማመቻቸት ተግባር ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል። በቀጣይም እንደዚህ አይነት ችግር ሲያጋጥም ምን አይነት መፍትሔ መወሰድ እንዳለበት ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here