የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2017 የትምህርት ዘመን የስድስት ወራትን ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
በግምገማው ላይ የመነሻ ሐሳብ ያቀረቡት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በ2017 የትምህርት ዘመን ዓመት በክልሉ ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፤ ይሁን እንጂ መመዝገብ የተቻለው 40 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን በማንሳት ቀሪዎቹ (አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን) ያልተመዘገቡ ተማሪዎች ናቸው።
ዶክተር ሙሉነሽ አክለውም ከተመዘገቡት ተማሪዎች መካከል 400 ሺህ ያህሉ ወደ ትምህርት ገበታ አልገቡም። በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ደግሞ 136 ሺህ ተማሪዎች ትምህርት ቤት የፈረሰባቸው በመሆኑ ወደ ትምህርት ቤት አልሄዱም።
ባለፈው ዓመት ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ዕቅድ ቢያዝም በዓመቱ ውስጥ ማስተማር የተቻለው 58 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ይህ ሁሉ ችግር ተደማምሮ ታዲያ የትውልድ ክፍተት እየፈጠረ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፤ ዛሬ ካላስተማርን ሀገር ገንቢ ትውልድ፤ ቤት ገንቢ ኢንጂነር፤ ፖለቲከኛ እና ሥራ ፈጣሪ አዕምሮዎች ያሳጣናል ብለዋል።
የትውልድ ክፍተት መፈጠሩን በማንሳት ይህም ከባድ ውድቀት የሚያመጣ እና የነገን ጉዞ የሚያደበዝዝ ነው በማለት የችግሩን ስፋት ገልጸውታል።
ትምህርት ባለመኖሩ ተማሪዎች ለተለያዩ ችግሮች (ስደት፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ጾታዊ ጥቃት እና ተስፋ መቁረጥ) እንዲጋለጡ ማድረጉን ዶክተር ሙሉነሽ ተናግረዋል።
በመሆኑም ይህንን ተረድቶ መላው የትምህርት ማኅበረሰብ እና መሪዎች ከሕዝቡ ጋር በመሆን ክስተቱን በማውገዝ ለሀገር ተረካቢ ተማሪዎች የነገ ተስፋ መረባረብ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ በተካሄደ ግምገማ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ እንዳይመጡ በማድረግ የሚገኝ ድልም ሆነ ዕድል እንደሌለ የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኢየሩስ መንግሥቱ ተናግረዋል፤ በመሆኑም ሰላምን በማጽናት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ እንደሚገባ ነው በውይይቱ የተነሳው።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም