ትምህርት ቤቶች የዕውቀት ምንጭ ከመሆናቸውም ባሻገር ተማሪዎች የተፈጥሮ ፀጋዎችን ለይተው እንዲያውቁ እና እንዲመራመሩ የሚያደርጉ የምርምር ተቋማት ናቸው። ስለ ተፈጥሮ ሀብት ጠቀሜታም በአካባቢ ሳይንስ ትምህርት እንዲማሩ ይደረጋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ድሃና ወረዳ ሲልዳ ቀበሌ በተጀመረው የተፈጥሮ ሀብት የማስጠበቂያ መርሐ ግብር በቀበሌው የሚገኘው የሲልዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች በመገኘት ተሞክሮውን ወስደዋል።
የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ ለተተኪው ትውልድ የተሻለ ሀገርን ማስረከብ የወላጆች ግዴታ መሆኑንም በመርሐ ግብሩ የተገኙት ተማሪዎች ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ አክለውም “ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስፈልገውን ነገር እንደሚያደርጉ ሁሉ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ ራሳቸውም ተተኪ ልጆችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባቸዋል” ነው ያሉት።
የሲልዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአካባቢ ሳይንስ መምህሩ ሙላት ወዳጅ ልጆች የተፈጥሮ ሀብትን ጠቀሜታ እንዲረዱ በቃል ከማስተማር ባሻገር በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በተግባርም ጭምር እያሳዩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ወላጆች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ለሀገርም፣ ለራሳቸውም እንደሚጠቅም በመረዳት እንዲያለሙ ነው መምህሩ ያሳሰቡት።
በሲልዳ ቀበሌ ጥያ ተፋሰስ በተጀመረው የተፈጥሮ ሀብት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ተማሪዎች መሳተፋቸው ለወላጆች ትልቅ መነሣሣት ይፈጥራል ያሉት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አዲሱ ወልዴ ናቸው።
ተማሪዎቹም “የተራቆተ መሬት አንረከብም፣ ለዋግ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ያስፈልጋታል” የሚሉ እና ሌሎች መሪ ሐሳቦችን በመያዝ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃው ለተገኙ የሥራው ተሳታፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም