አሳሳቢው ርዕደ መሬት

0
150

ርዕደ መሬት በመሬት ውስጥ በታመቀ ኃይል ልቀት የተነሳ ሲስሚክ (Seismic Waves)  በሚባሉ ሞገዶች አማካኝነት የሚመጣ የተፈጥሮ አደጋ መሆኑን የአሜሪካው ጂኦሎጂካል ሰርቬይ (US Geological Survey) ተርጉሞታል። የምድር ንጣፎች (የምድር ቅርፊቶች) የተደራረቡ እና ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን እርስ በእርስ የሚጋጩበት ጊዜ አለ። በዚህ ወቅት ታዲያ በታመቀው ኃይል ምክንያት በሚፈጠረው ከፍተኛ ሞገድ ርዕደ መሬት ይከሰታል። በአጭር አገላለጽ ርዕደ መሬት የሚፈጠረው ከምድር  ውስጥ በሚገኙ ዓለታማ  ቁሶች ግጭት ምክንያት ነው።

የርዕደ መሬት ልኬት በሬክተር ስኬል የሚገለጽ ሲሆን አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ በመባል በሦስት እንደሚከፈል መረጃው ጠቁሟል። ከመረጃ ማዕከሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት በርዕደ መሬት ተጠቅታለች። ከዚህ ውስጥ በአስከፊነቱ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ደግሞ እ.አ.አ በ1556 በቻይና የተከሰተው ርዕደ መሬት ሲሆን የ830 ሺህ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

በአስከፊነቱ በሁለተኛነት የሚጠቀሰው እ.አ.አ 1976 በተመመሳሳይ በቻይና የተከሰተው ርዕደ መሬትም ከ242 ሺህ እስከ 655 ሺህ ሰዎችን እንደቀጠፈ ታሪክ መዝግቦታል።

ከዓለም ጤና ድርጅት ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ደግሞ እ.አ.አ ከ1998 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት የተከሰቱ ርዕደ መሬቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 750 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ሕይዎታቸውን ቀጥፏል። ከ125 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት በቱርክ እና በሶሪያ የተከሰቱ ርዕደ መሬቶች ከ36 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ያስታወሰው ደግሞ የጀርመኑ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ነው። ርዕደ መሬቱ የተከሰተባቸው አካባቢዎችም ወደ ፍርስራሽነት ነው የተቀየሩት።

የብሪታኒያ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተመራማሪ ሮጀር ሙሶንን ዋቢ አድርጎ የጀርመን ድምጽ በሠራው ዘገባ እንደተመላከተው ርዕደ መሬትን በተመለከተ ሳይንስ ያልደረሰባቸው እውነታዎች አሉ። ክስተቱም ተፈጥሯዊ መሆኑን በማንሳት ለመከላከል አስቸጋሪ መሆኑን አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ መቼ ሊከሰት እንደሚችል ቅድመ ትንበያ ለማድረግ ይቻላል። ለአብነትም በጃፓን የደረሰው ርዕደ መሬት ከመከሰቱ ከአንድ ዓመት ቀድም ብሎ ክስተቱ ሊኖር እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ቅድመ ትንበያ ሰጥተው ነበር። በተመሳሳይ እንስሳትም እንግዳ ምልክቶችን በማሳየት ርዕደ መሬት ሊከሰት እንደሚችል ምልክት እንደሚሰጡ ይነገራል። ለአብነትም ውሻ፣ ድመት፣ ዝሆን፣ አሳ፣ አዕዋፍ፣ ተሳቢ እንስሳት፣ … ይጠቀሳሉ።

ከአሜሪካው ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው ርዕደ መሬት ከተፈጥሯዊ በተጨማሪ በሰው ሠራሽ መንገድ (በግንባታ፣ በማዕድን ቁፋሮ እና በአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ) ሊከሰት ይችላል።

ከርዕደ መሬት አደጋ ጋር በተያያዘ ታዲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገራችን በተደጋጋሚ ስሟ እየተነሳ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ የሚሰማው በአፋር አካባቢ የሚከሰተው ተደጋጋሚ ርዕደ መሬት ነው። ወትሮውንም የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ለዚህ ክስተት የተጋለጠ መሆኑም ይነገርለታል።

በተደጋጋሚ የተከሰተው እና እየተከሰተ ያለው አደጋ በርካቶችን አፈናቅሏል። ችግሩን ተከትሎም ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

በአፋር ክልል በተለይ ሁለት ወረዳዎች (አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች ለችግሩ ተጋላጭ መሆናቸውን ያመላከተው ኮሚሽኑ ከስጋቱ ቀጣና ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቁሟል። በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳም ተመሳሳይ ሥራ መከናወኑን ኮሚሽኑ በመግለጫው አመላክቷል።

በተመሳሳይ ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ህፃናትን በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ሆኗል።

መደረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች

የዘርፉን ባለሙያዎች ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ እንደዘገበው ርዕደ መሬት ሲከሰት  ወይም እንደሚከሰት ምልክቶች ከታዩ የተለያዩ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይገባል፤ ርዕደ መሬቱ ሲከሰት ቤት ውስጥ ከሆንን በፍጥነት ከለላ መፈለግ (በቀላሉ የማይሰበር ጠረጴዛ ካለ ርዕደ መሬቱ እስኪቆም ከዚያ ሥር መከለል) ይመከራል። ጋዝ ካለበት፣ ከመስታወት፣ ከበር፣  ከግድግዳ እና ሊወድቁ ከሚችሉ ቁሶች መራቅም እንደሚገባ ነው ዘገባው የጠቆመው።  ጭንቅላትን በትራስ መሸፈንንም ይመክራል።

ባለሙያዎቹ በርዕደ መሬት ክስተት ጊዜ አሳንሱር መጠቀም እንደማይገባ የሚመክሩት ባለሙያዎች፣ ድንገት አሳንሱር ውስጥ ካሉም በፍጥነት መውጣት እንደሚገባ ነው ምክረ ሐሳብ የሚለግሱት።

ርዕደ መሬት ሲከሰት ከቤት ውጭ ከሆኑ ደግሞ ከሕንፃዎች፣ ከኤሌክትሪክ፣ ከስልክ ገመዶች እና ከመንገድ መብራቶች መራቅ እንደሚገባ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚመክሩት።

ርዕደ መሬቱ ሲከሰት ምንም ነገር የሌለበት ገላጣ ሥፍራ ላይ የምንገኝ ከሆነ ክስተቱ እስኪቆም እዚያው ባለንበት መቆየት ይመረጣል።  ተሽከርካሪ ውስጥ ከሆንን ደግሞ ችግሩ እስኪቆም ተሽከርካሪ ውስጥ መቆየት ይገባል።

በቅርቡ በሀገራችን  ርእደ መሬት በተደጋጋሚ መከሰቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የጥንቃቄ መልዕክቶችን በማሕበራዊ ትስስር ገጹ እያደረሰ ነው፤ ከላይ ከተዘረዘሩት የጥንቃቄ ርምጃዎች ባለፈ ከመሬት ንዝረት ክስተት በኋላም የሚከተሉትን ማከናወን እደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል።

ክስተቱን ተከትሎ ሊነሱ ከሚችሉ የእሳት አደጋ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የውኃ አደጋዎች እና ሌሎች አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ (የኃይል ማመንጫ ምሶሶዎችና መስመሮች፣ እሳት፣ ኬሚካል፣ መርዛማ ነገሮች፣ ሊወድቁ የሚችሉ ቁሶች) መኖራቸውን ማረጋገጥና ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ፤ የተጎዱ (የቆሰሉ) ሰዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ፣ የመጀመሪያ እርዳታ መስጠት፣ የተጎዱ (የቆሰሉ) ሰዎችን በጥንቃቄ እና በፍጥነት ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ነው ያለው።

የህንፃ መሠረቶች፣ ግድግዳዎች፣ ጣሪያዎች፣ የጭስ መውጫዎች፣… መሰነጣጠቃቸውንና መጎዳታቸውን በማረጋገጥ ሌላ ጉዳት እንዳያስከትሉ ጥንቃቄ ማድረግ፤ ክስተቱ የሚቀጥል መሆኑ ከታወቀም በጊዜያዊ መጠለያ መቆየት፣ አካባቢው አደገኛ መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ ሌላ ጊዜያዊ መጠለያ በማዘጋጀት ከአካባቢው መራቅ ይገባል። ለአስቸኳይ ጊዜ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ፍላጎቶች ምግብ፣ ውኃ፣ አልባሳትና መድኃኒት መኖራቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ነው።

ከዋናው ንዝረት (መንቀጥቀጥ) ተከትሎ ሊከሰት ከሚችል ዳግም የመሬት ንዝረት ለመጠበቅም በቂ ዝግጅት ማድረግ ተገቢ መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here