የከሸፈው ተሰጥኦ

0
132

ይህ ተጫዋች በትውልዱ ካሉ የላቀ ተሰጥኦ ያለው ነው፤ ኳስ የመግፋት ክህሎቱ እጅን በአፍ ያስጭናል፤ ለቡድን ጓደኞቹ በሚሰጣቸው ጣጣቸውን በጨረሱ ገዳይ ኳሶቹ ይታወቃል፤ እጅግ የተዋጣለት ግብ አነፍናፊ ጭምር ነው፤ የተጋጣሚን ቡድን ተከላካዮች የሚያሸብር አብዶኛም ነው፤ የተለየ እና ማራኪ አጨዋዎቱ አጃኢብ ያሰኛል፤ በብዙ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድም የሚወደድ ነው- ኔይማር ዳ ሲልቫ ሳንቶስ ጁኒየር።

ብራዚላዊው ጥበበኛ በብዙ ተጠብቆ የከሸፈ ድንቅ የእግር ኳስ ባለተሰጥኦ ነው። የ32 ዓመቱ ኮከብ በሦስት የተለያዩ ክለቦች 100 ግቦችን በማስቆጠር ከጥቂት የእግር ኳስ ኮከቦች ጋር ስሙን በታሪክ መዝገብ አስፍሯል። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ከፍተኛ ግብ ያስቆጠረ ብራዚላዊ ተጨዋችም ነው። እንዲሁም ለሀገሩ ብራዚል 79 ግቦችን ከመረብ በማገናኘት የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።

በማህበራዊ ሚዲያ ብዙ ተከታይ ካላቸው የእግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል ሦስተኛ ደረጃ ላይም ይገኛል። አሁን ላይ በዓለም ላይ ሦስት ታዋቂ እና ዝነኛ የእግር ኳስ ኮከቦች መካከል አንዱ ነው። 20ኛ የልደት በዓሉን ሲያከብር መቶኛ ግቡን አስቆጥሯል። ሁለት ጊዜ የደቡብ አሜሪካ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። ብራዚላዊው ኮከብ እ.አ.አ በ1992 በሳኦ ፓውሎ ከተማ ነው የተወለደው። ቤተሰቦቹ ለእግርኳስ ስፖርት ቅርብ በመሆናቸው ታዳጊው ልጃቸው እግር ኳስ ተጫዋች እንዲሆን ይፈልጉ ነበር። ታዲያ እንደ ብዙዎቹ ባለተሰጥኦ ብራዚላውያን ኔይማርም እግር ኳስን በጎዳና ላይ ተጫውቶ  ነው ያደገው።

ፍጥነትን እና በተጨናነቀ ቦታ ኳስ እንዴት መንዳት እንደሚቻል ጨምሮ የተለያዩ ቴክኒኮችን ያዳበረው ጎዳና ላይ በሚጫወተው ፉትሳል መሆኑን ግለ ታሪኩ ያስረዳል። እ.አ.አ በ2003 በ11 ዓመቱ በከተማው የሚገኘውን የፖርቹጊሳ ሳንቲስታ የወጣቶች ቡድን ተቀላቅሏል።  በዚሁ ዓመት በሳኦ ፖውሎ የሚገኘውን ትልቁን የእግር ኳስ ክለብ ሳንቶስን መቀላቀሉን መረጃዎች ያሰነብባሉ።

ሳንቶስ ፔሌን እና ሮቢንሆን ወደ ኮከብነት ያሸጋገረ ክለብ በመሆኑ ደጋፊዎቹ ከእነዚህ የቀድሞ ኮከቦች ጋር ያነጻጽሩት እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል።   በ14 ዓመቱም የሪያል ማድሪድ ወጣቶችን ለመቀላቀል ለሙከራ ወደ ስፔን አምርቶ እንደነበር የግል የታሪክ ማህደሩ ያስረዳል። ነገር ግን ሳንቶስ የተሻለ ክፍያ እና ጥቅማጥቅም በመክፈል በብራዚል ምድር እንዲቆይ አደረገ።በ17 ዓመቱ የመጀመሪያውን የፕሮፌሽናል የውል ስምምነት ከሳንቶስ ጋር ፈረመ። የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ጨዋታውንም እ.አ.አ በ2009 ማድረግ ችሏል።  በዚህ ወቅት የኔይማር የእግር ኳስ ህይወት አልጋ በአልጋ ሆነ፤ የቤተሰቦቹ ህይወትም መሻሻል ጀመር።

በ2011 እ.አ.አ የብራዚል ቁልፍ ተጫዋች ሆነ። በ2013 እ.አ.አ ደግሞ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እና በ2016 እ.አ.አ የበጋ ኦሎምፒክ ሀገሩ ብራዚል የወርቅ ሜዳሊያ እንድታሸንፍ የእርሱ ሚና የላቀ ነበር። በወቅቱ በኦሎምፒክ ታሪክ እስካሁን ክብረወሰን የሆነውን ፈጣን ግብ ማስቆጠሩም አይዘነጋም። ኔይማር በብራዚል ቆይታው ሳንቶስን ከ48 ዓመታት በኋላ የኮፓ ሌበርታዶሬስ ዋንጫ አሸናፊ አድርጎታል። የብራዚል ሴሪ ኤን፣ የካምፒዮናቶ ፓውሊስታ ዋንጫ እና ሌሎችንም ዋንጫዎች አሳክቷል። በዚህ ወቅት ነበር በርካታ የአውሮፓ ክለቦች በተሰጥኦው መጎምዥት የጀመሩት።

በርካታ የአውሮፓ ክለቦች  የመጪውን ዘመን የእግር ኳስ ኮከብ ለማስኮብለል በሳንቶስ ሰማይ ስር ማንዣበብ ጀመሩ። ሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች ቸልሲ እና ዌስትሀም ዩናይትድ ኔይማርን የግላቸው ለማድረግ ደጅ የጠኑ ክለቦች ናቸው። ይሁን እንጂ ታዳጊው አብዶኛ በ2014 እ.አ.አ በሀገሩ ምድር የሚዘጋጀው የዓለም ዋንጫ እስኪያልፍ ወደ አውሮፓ ላለማቅናት ቢወስንም የዓለም ዋንጫው ሊካሄድ አንድ ዓመት ሲቀረው የአትላንቲክ ውቅያኖስን በማቆራረጥ መዳረሻውን ካታሎናውያን ቤት አደረገ።

ባርሴሎና  ለዝውውር ትልቅ ገንዘብ በማቅረብ በ57 ሚሊዬን ዩሮ ኔይማርን ማሰፈረሙ የሚታወስ ነው። በኑካምፕም ከሊዮኔል ሜሲ እና ሊዊስ ሰዋሬዝ ጋር ድንቅ ጥምረትን ፈጠረ። ወጣቱ አጥቂ ከካታሎኑ ክለብ ጋር የላሊጋ፣ የሻምፒዮንስ ሊግ፣  የዓለም ክለቦች ዋንጫን እና ሌሎችንም ዋንጫዎች አንስቷል። በሊዮኔል ሜሲ ጥላ ስር መሆኑ ብዙም ምቾት ያልሰጠው ኔይማር ጁኒየር በ2017 እ.አ.አ ክለቡን እንደሚለቅ ይፋ አደረገ።

ባሎን ዶርን አሸንፎ ህልሙን እውን ለማድረግም በ25 ዓመቱ የፓሪሱን ሀብታም ክለብ ፓሪስን ዥርሜንን ተቀላቀለ። የፈረንሳዩ ክለብ ለዝውውሩ 222 ሚሊዬን ዩሮ አውጥቷል። ይህ ዋጋ እስካሁንም የፕላኔታችን ውዱ የእግር ኳስ ዝውውር በመሆን ክብረወሰን ይዟል።  የፈረንሳዩ ኃያል ክለብ በአዲሱ ኮከቡ አማካኝነት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ማንሳት እና በአውሮፓ አዲስ የእግር ኳስ አብዮት ለመፍጠር አስቦ ኔይማርን እስካሁን ክብረወሰን በሆነ ዋጋ ቢያስፈርመውም እቅዱ ሲከሽፍ ግን ውሎ አላደረም።

በፓርክ ደ ፕሪንስ በተደጋጋሚ የጉዳት ሰለባ ከመሆኑ ባሻገር ትኩረቱን መሰብሰብ ባለመቻሉ ውጤታማ መሆን አልቻለም። ከአራት ዓመታት በኋላ ደግሞ የቀድሞው የቡድን አጋሩ እና ጓደኛው ሊዮኔል ሜሲ ፓሪስ መድረሱን ተከትሎ ምባፔ፣ ሜሲ እና ኔይማር በአውሮፓ አስፈሪውን ጥምረት መፍጠር ቻሉ። ያም ሆኖ ግን የፈረንሳዩ ክለብ የሚፈልገው ውጤት መምጣት አልቻለም። ኔይማርም ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ የፓሪሱን ክለብ ለቆ በ2023 ነሐሴ ወር የሳውዲውን ክለብ አል ሂላልን ተቀላቅሏል።

ኔይማር ጁኒየር በፓሪሰን ዥርሜን ቆይታው አምስት የሊግ አንድ እና ሌሎችንም ዋንጫዎችን ማንሳቱ የሚታወስ ነው። ደጋፊዎች እና የክለቡ ባለሀብቶች የሚጓጉለትን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ግን በ2019/ 20 የውድድር ዘመን ጫፍ ደርሶ ሳይሳካለት መቅረቱ አይዘነጋም። ካልተሳካው የፓርክ ደ ፕሪንስ ቆይታ በኋላ በ90 ሚሊዬን ዩሮ ነው አል ሂላልን የተቀላቀለው።

ይህም ህልሙ የነበረውን የባሎን ዶር ሽልማት ሳያገኝ የአውሮፓ ምድርን መልቀቁ ብዙዎች እንዲያዝኑለት፣ እንዲበሳጩበት አድርጓል። ኔይማር አውሮፓን ለቆ ወደ ሳውዲ አረቢያ ሲያመራ ደጋፊዎቹ እና አድናቂዎቹ የእግር ኳስ ህይወቱ የተጠናቀቀ ያህል ነበር የተሰማቸው። በእርግጥም የሆነው እንደዚያ ነው ማለት ይቻላል።

በአል ሂላል ቤት በሁለት ዓመታት ውስጥ አምስት ጨዋታዎችን በማከናወን አንድ ግብ ብቻ አስቆጥሯል። ኔይማር በሳውዲ ፕሮ ሊግ በዓመት 150 ሚሊዬን ዩሮ ደሞዝ እየተከፈለው ነው ባለፉት ሁለት ዓመታት የቆየው። እንደ ብርጭቆ በቀላሉ ተሰባሪ መሆኑ  በሳውዲ አርቢያም የተሳካ ጊዜ እንዳያሳልፍ መሰናክል እንደሆነው መረጃዎች አመልክተዋል።

በተጨማሪም በሳውዲው ክለብ አል ሂላል የአጥቂውን ክብደት መጨመር የተመለከቱ የእግር ኳስ ባለሙያዎች ለእግር ኳሱ ያለው ትኩረት መቀነሱንም እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ። በፓሪስ የጀመረው የክብደት መጨመር በአል ሂላል ይበልጥ በመወፈሩ ለመተንፈስ ሲቸገር መስተዋሉን መረጃዎች አስነብበዋል።

ለደሞዝ እና ለፊርማ ረብጣ ሚሊዬን ዩሮ የከፈለው የሳውዲው ክለብ አል ሂላል ከ32 ዓመቱ ባለተሰጥኦ የሚፈልገውን ግልጋሎት ሳያገኝ ከተጫዋቹ ጋር ተለያይቷል። በቅርቡ በተጠናቀቀው በጥሩ የተጫዋቾች ዝውውርም ወደ ልጅነት ክለቡ አምርቷል።

የቀድሞ ክለቡ ሳንቶስም የንጉሥ አቀባበል አድርጎለታል። ብዙዎች የእግር ኳስ የመገናኛ አውታሮች ኔይማር ተሰጥኦውን ሳይጠቀምበት መባከኑን በስፋት እየዘገቡት ይገኛሉ። እንደ ጎል ዶት ኮም መረጃ ኔይማር  ባርሴሎናን ለቆ ወደ ፈረንሳይ ካቀና በኋላ ዓላማውን ዘንግቶ ትኩረቱን ከእግር ኳስ ውጪ አድርጎ እንደነበር ያስታውሳሉ። አብዝቶ ዳንኪራ መውደዱ እና በማህበራዊ ሚዲያ መጠመዱ የእግር ኳስ ህይወቱን አበላሽቶታል ይላል መረጃው።

ለስኬት የነበረው ርሃብ መቀነሱ እና የቅንጦት ህይወት መኖሩ በእግር ኳስ ህይወቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮ ዋጋ አስከፍሎታል። ቀስ በቀስም ሜዳ ውስጥ የሚያሳየው ክህሎት እና ብቃት እንዲወርድ አድርጎታል። ይህ መሆኑ ደግሞ አዕምሯዊ እና አካላዊ ጥንካሬው እንዲከዳው በማድረግ ለተደጋጋሚ ጉዳት ተጋላጭ እንዲሆን አስችሎታል። ኔይማር በእግር ኳስ ህይወቱ ለአንድ ሺህ 294 ቅናት (ሦስት ዓመት ከስድስት ወራት በላይ)  በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቋል። በጉዳት ምክንያት በፓሪሰን ዥርሜን ቤት ብቻ ከ100 ጨዋታዎች በላይ አምልጠውታል ነው የተባለው።

የባርሴሎና ምክትል አሰልጣኝ የነበረው  ጁዋን ካርሎስ ኔይማር ጁኒየር እንደ ሁለቱ የሀገሩ ልጆች ሮናልዲንሆ እና ሮቢንሆ እንዳይሆን መክሬው ነበር ብለዋል። ሁለቱ ባለተሰጥኦ የቀድሞ ኮከቦች  ዝናን እና ሀብትን መሸከም ተስኗቸው ተሰጥኦቸውን በአግባቡ ሳይጠቀሙበት እንደከሰሙ አይዘነጋም።

ፉትቦል ኮፓ ዶት ኮም የኔይማር የእግር ኳስ ታሪክ ለወጣት ስፖርተኞች ምሳሌ የሚሆን ሳይሆን እንደ  ተረት ማስተማሪያ ተደርጎ ሊጠቀስ እንደሚችል ያስነብባል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here