የባሕል አምባሳደሩ ይሁኔ በላይ

0
318

“አውራ ዶሮ ሲጮህ አትክፈችው ደጁን

እኔ ደመኛው ነኝ በልቼበት ልጁን” ቆለኛ ደገኛ ከሚለው ዘፈን የተቀነጨበ  ዛሬ የምናነሳሳው ድምጻዊ  ስራ  ነው። አባትሽ ሲመጣ ዝም በይ የሚል ሃገረሰባዊ ቅኔ።

የገና፣ የጥምቀት፣ የሆያ ሆዬ ጨዋታዎችን ተወልዶ ባደገባት ፍኖተ ሰላም ከተማ በመጫዎት የሙዚቃ ሕይወቱን ጀምሯል።  የአካባቢውን ማሕበረሰብ ሙዚቃ፣ ወግ እና ባህል በሙዚቃ ሥራዎቹ በስፋት አስተጋብቷል። ለዚህም ይመስላል ብዙዎች “የባህል አምባሳደሩ” ሲሉ የሚጠሩት። ዘጠኝ የሙዚቃ አልበሞችን ከ1982 ዓ.ም በመጀመር ለአድማጭ አድርሷል። በተለያዩ ጊዜያት በርከት ያሉ ነጠላ ዜማዎችን ለሙዚቃ አፍቃሪዎች አድርሷል።

ኩኩ መለኮቴ፣ ብብ ከፊላው፣ አሎ ሉሎ፣ ዘገሊላ፣ ግቢ ግቢ፣ ዘንገና፣ አሆ በል፣ጉዛራ፣ያገሬ ልጅ፣ ዘይሪኝ፣ ሳናሞናሙነው እና በሌሎች ሙዚቃ ስራዎቹ በስፋት ጎልቶ ይታወቃል፤ ድምጻዊ ይሁኔ በላይ።

በገና እና ጥምቀት ወቅት የይሁኔ በላይ “ዘገሊላ” ሙዚቃ በስፋት የሚደመጥበት ጊዜ ነው። “ያደግሁበት አካባቢ ችግሩን ደስታውንም የሚገልጸው በሙዚቃ ነው” ሲል ይሁኔ አነሳሱን ያስታውሳል። በፍኖተ ሰላም ከተማ በቀበሌ የሕጻናት ኪነት ጀምሮ ከወረዳ እስከ አውራጃ ባሉት እርከኖች ዘፍኗል። ወደ አዲስ አበባ ሄዶ የሙዚቃ ስራውን አሳድጓል። በኋላም ወደ አሜሪካ በመዝለቅ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ መድረክን ተቀላቅሏል። ከኢትዮጵያ ቢወጣም ያደገበትን ማህበረሰብ ባህል እና ማንነት የሙዚቃ ስራው ማዕከል አድርጓል።

በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር ቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ ኪነትም ውስጥ ዘፍኗል። በጎጃም ውስጥ በወቅቱ ከነበሩት ሰባት አውራጃዎች ውስጥ ይሁኔ ያለበት ቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ የኪነ ጥበብ ስራዎችን በውድድር በማቅረብ አንደኛ ይወጣ እንደነበርም ይሁኔ ታመኝ በየነ ጋር በነበረው ቃለመጠይቅ ተናግሯል።

በ1977 ዓ.ም ሰባቱም የጎጃም አውራጃዎች በባህር ዳር ከተማ የኪነ ጥበብ ስራዎች ውድድር ያደርጉ ነበር። በወቅቱ ይሁኔ ያለበት አውራጃ ኪነት አንደኛ በመውጣት ሲያሸንፍ ይሁኔ ዓይን ውስጥ ገባ። የግሽ ዓባይ ኪነት ቡድን መሪዎች ይሁኔ ቡድኑን እንዲቀላቀል አነጋርገሩት።

የሚፈልገው፣ ለዓመታት የሚመኘው እድል እጁ ገባ። በወቅቱ ይሁኔ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ በመሆኑ ትምህርቴን እንዴት ላደርግ እችላለሁ ብሎ ባህርዳር እንዴት መኖር እንደሚችል ማሰብ ጀመረ። በ30 ብር ወርሐዊ ደመወዝ እንቅጠርህ ብለው አግባቡት። ፍኖተ ሰላም የሚኖሩ ቤተሰቦቹን ተለይቶ መኖርን ሲያስብ ግራ ተጋባ። በኋላም የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ እናንተ ጋር ተመልሼ እመጣለሁ ብሎ ግሽ ዓባይን ሳይቀላቀል ቀረ። ወደ ፍኖተ ሰላምም  ተመልሶም ትምህርቱን ቀጠለ።

12 ክፍል ትምህርቱን አጠናቅቆ በፍኖተሰላም አቅራቢያ በምትገኝ ባከል ገብርኤል ቀበሌ መሰረተ ትምህርትን ለሁለት ወራት አስተማረ። በወቅቱ በወር የሚከፍሉትን 40 ብር ደሞዝ ድምር 80 ብር ይዞ  ወደ ግሽ ዓባይ ለመቀላቀል ባህርዳር ከተማ እንደገባ ለታማኝ በየነ አጫውቶታል።

ይሁኔ የፍኖተሰላም ከተማ ዙሪያ ገጠር ቀበሌ ማህበረሰብ አኗኗርን፣ ባህል እና ወግን በማየት ነው ያደገው። የገጠር እናቶች ገበያ ሲመጡ ይመለከታል፣ በሚገባ ያስተውላል። ይህ ባህል እና ዘይቤ ውስጡ ገብቷል። “ባላገሩ ከገበያ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሲሄድ እንዴት እንደሚያወራ፣ እንዴት እንደሚጫዎት፣ እንዴት እንደሚያፏጭ ደስ ስለሚለኝ ተከትዬው ያለምንም ስራ ብዙ ኪሎ ሜትር ሄጄ አርሶ አደሩን ሸኚቼ ወደ ቤቴ እመጣ ነበር” ሲል የልጅነቱን ዘመን ያስታውሳል።

ከባላገሩ ያስተዋለውን ለጓደኞቹ በንግግር እና በድርጊት ያሳያቸዋል። በዚህም የትኩረት ማዕከል መሆን ቻለ። ሲጫዎት ብዙዎች የሚያደንቁት እና ክብብ የሚያደርጉት ሆነ።

ይሁኔ በ1979 ዓ.ም ግሽ ዓባይ ኪነትን እንደተቀላቀለ ከሰማኸኝ በለው፣ አንሙት ክንዴ (ሀብቱ ንጋቱ)፣ ብዙ አየሁ ጎበዜ፣ ዓለምወርቅ አስፋው  በጋራ ሆነው “አንቱዬዋ” የሚል ሙዚቃዊ ድራማ በይሁኔ ደራሲነት ቀረበ። ይህ ስራ ለይሁኔ በላይ የመጀመሪያ ዓይን መግለጫው ሆነ። ለይሁኔ ይህ ዘፈን በብዙ ሕዝብ እንዲታወቅ ያደረገው ስራ ሆነ። ይህን ስራ ይሁኔ እና ጓደኞቹ በባህርዳር ስቴዲዮም በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ አድናቆት ቀርቦላቸዋል። በኋላም አዲስ አበባ በፊልም ተቀርጾ ሲሰራጭ የበለጠ ዝነኞች አደረጋቸው። ይሁኔ ለካሴት እና ለክለብ ስራዎች መታጨት ጀመረ።

የአለማየሁ ቦረቦር እና አበበ ተሰማ ዘፈኖችን ይወዳል። ደበሎ፣ ባርኔጣ፣ ባህላዊ አልባሳትን ማስተዋወቅ ይወዳል። “ዘፈኖች ሁልጊዜ በባህል አንድ ነገር ማስተዋወቅ አለባቸው ብዬ አምናለሁ፣ የማይታወቀው ላይ ባተኩር ደስ ይለኛል። ከዘፈንነት ባለፈ ማስታወቅ፣ የማይታወቅን ባህል ማጉላት አለብኝ ብዬ አምናለሁ” የሚለው ይሁኔ በዘፈኖቹ ያደገበትን አካባቢ በማስተዋወቅ ገፍቶበታል።

በ1980 ዓ.ም “አንቱየዋ” ሙዚቃ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በምስል ተቀረጸ። ይህም ይሁኔ አልበም እንዲሰራ እውቅና ፈጥሮለታል።  አዲስ አበባ ሄዶ  አልበም ለመስራት የግሽ ዓባይ ኪነት ቡድን አለቆቹን ሲጠይቅ 15 ቀን ተሰጠው። ቀኑ አለፈ። ሁለት ወር ሞላው። ወታደር ተልኮበት ወደ ባህርዳር መልሰው ወሰዱት።  በዚህ ሒደት አልፎ በ1982 ዓ.ም ይሁኔ “ያገሬ ልጅ” የሚለውን አልበም በካሴት ሲያወጣ 1500 ብር ተከፈለው። እሱ ግሽ ዓባይ ኪነት ውስጥ ይሰራ ስለነበር  “ዘፈኑ ከአውቶብስ መኪና ተከፍቶ ስሰማው ደነገጥሁ” ሲል ያስታውሳል። በግሽ ዓባይ ኪነት ቡድን አራት ዓመታትን ብቻ አገልግሏል። በ1982 አልበሙ እንደወጣ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። ግሽ ዓባይን ለቆ ሄደ። በ1984 ደግሞ ኢትዮጵያን ለቆ አሜሪካ ገባ። ይሁኔ ልዩ የእስክስታ ችሎታም አለው። በራሱ ጥረት ሰዎችን በማየት ጎበዝ ተወዛዋዥ ሆኗል።

ይሁኔ በላይ በግሉ ከሰራቸው ዘጠኝ የሙዚቃ አልበሞች በተጨማሪ፣ ከፍቅር አዲስ ነቅዐጥበብ፣ የሺእመቤት ዱባለ፣ አሰፉ ደባልቄ ጋር በቅብብል ዘፍኗል። ከማሪቱ ለገሰ፣ ሀብተሚካኤል ደምሴ፣ እያዩ ማንያዘዋል ጋርም ስብስብ ስራዎችን በካሴት አሳትሟል።

“ኢትዮጵያን የሎው ፔጅስ” ቢዝነስ ዳይሬክተሪ የሚስቱ የሽእመቤት ተስፋዬ ድርጅት ነው። የኢትዮጵያዊያን መረጃ ማሰራጫ እና ማሳዎቂያ  ተቋም ነው። ይሁኔ ከወይዘሮ የሺ እመቤት ፍቅር እና ሰላም የተባሉ ሁለት ሴት እና ወንድ  ልጆች አሉት። የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ አሜሪካ  በተገኘበት መድረክ ነው ከሚስቱ ጋር የተዋወቁት።  ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ በ1993 ዓ.ም ነበር ወደ ኢትዮጵያ  የተመለሰ።

ይሁኔ መልካም ትዳር፣ ሰብዕና እና ጥሩ የኢኮኖሚ አቅም ያለው ዘፋኝ ነው። ለትምህርት ባለው ጉጉት በኮምፒዩተር ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪውን አግኝቷል። በበጎ አድራጎት ስራዎች እና ሰዎችን በመርዳት በስፋት ይሳተፋል። ወደ ሙዚቃዎቹ እንለፍ።

 

የባህል አምባሳደርነት እንዴት?

ከይሁኔ በላይ ሙዚቃዎች  ጋር ነው ያደግሁት። 1994 ዓ.ም  እኔ ባደግሁበት ቀበሌ የመሰረተ ትምህርት ይሰጥ ነበር። ይህ ጊዜ  የይሁኔ ሙዚቃ በጋራው እና ሸለቆው ሁሉ የሚደመጥበት ጊዜ ነበር። የመሰረተ ትምህርት አስተማሪዎች ሬዲዮ ከፍተው የይሁኔን ሙዚቃ ስንሰማ ከዙሪያቸው አንጠፋም ነበር። ያለ ስራችን መምህራኑን ስንከተል እንውል ነበር። ወደ ቋሪት የሚሄድ እና የሚመለስ ሎንችና መኪና  ሲመጣ ሙዚቃውን ለመስማት ስንል ዓይናችንን አቧራ እስኪሸፍነን፤ መኪናው ቀድሞም ከዕይታ ውጪ እስኪሆን ድረስ በሩጫ እንከተለው ነበር። 1993 ዓ.ም የወጣው “ብብ ከፊላው” ሙዚቃ አልበም  የልጅነቴ ትዝታዎች አሉበት። 1995 ዓ.ም ጅጋ ከተማ ስገባ መስመር እና ማደያዎች የሚቆሙ መኪናዎች ሁሉ ይህንን አልበም በብዛት ይከፍቱት እንደነበር ትዝ ይለኛል።

ይሁኔ የባህል አምባሳደር ነው ሲባል የሙዚቃዎቹን ጭብጥ፣ መልዕክት ግጥም፣ ዘይቤ፣ ቅኔ፣ ጭፈራ፣ ቃላት አጠቃቀም እና ሌሎች ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። የባህል የአምባሳደርነት ማሳያ ሙዚቃዎችን በወፍ በረር እንቃኛቸው። አንዳንዶች ሙዚቃዎች ብቻቸውን የሚተነተኑ፣ ለባህል ጥናት እና ምርምር የሚውሉ ናቸው። በግልብ ዕይታ ብቻ ለማስታወስ ያህል አነሳሳቸዋለሁ።

ራሱ ይሁኔም እንደሚለው ያደገበትን አካባቢ በማጥናት አዲስ ነገር ለማስተዋወቅ ጥረት አድርጓል። አይደፈሬ የማህበረሰብ ጉዳዮችን አንዳንድ ጊዜ በቅኔ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በይፋ ለመግለጽ ሞክሯል። “ያገሯ ሰማይ” ሙዚቃ ግጥሞችን ለመግቢያነት  እንመልከት።

“ለወፍም ለዶሮም ተወችው ስጡን

አታውቀውምና እሽ ማለቱን

አጓጉል ጨዋታ ለምዳ ፉክክር

መስኩ ላይ ባስጠራት ሸሸች በቆንጥር”

“ግቢ ግቢ”  የሚለው አልበም የይሁኔ ሦስተኛ አልበም 1985 ዓ.ም ነበር ለሕዝብ የደረሰው። “አብሮ ማደጉን” የሚለው ሙዚቃ ውስጥ የማህበረሰቡን የጋብቻ አረዳድ በፍቅር ሙዚቃ ውስጥ እናይበታለን። አብሮ አደጎች ብዙ ጊዜ አይጋቡም። የፍቅር ግንኙነት ጀምረዋል። ይሁኔ “ፍቅር ጉድ አፈላ” በሚል የሚያነሳሳው የአብሮ አደጉ ፍቅር በርትቶበታል። እሷ ደግሞ ግዴለም እህት እና ወንድም እንሁን ስትል ትመክረዋለች። እሱ ደግሞ አይሆንም እንጋባ ነው የሚላት። “ስንዴ ባገር ሞልቶ በጓያ ቆርቤ፤ ያምሸከሽከኛል አልሄድ እንደ ልቤ”፤ ስንዴ እና ጓያ አንዳች ተምሳሌታዊ ትርጉም አላቸው። ስንዴ ለቁርባን የሚያገለግል የተባረከ ሰብል ነው። ለቅዱስ ተግባርም ይውላል። ጓያ የወጥ እህል ነው። ገለባው ላይ ሰዎች ከተኙበት ይሰብራል፣ ሽባ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። ምርጫ  ማጣት ካልሆነ በቀር ጓያ ለወጥ አይመረጥም። አተር፣ ሽንብራ እና ባቄላ ይቀድማሉ።

ስንዴ ነጭ ነው። ጓያ ደግሞ ጥቁር። ምናልባት የሁለቱን ፍቅር ስንመለከት በነጭ ስንዴ መወከሉ፣ ለተቀደሰ ዓላማ መዋሉ በወግ እና ስርዓት የሚመራውን ማህበረሰብ ወክሎ ቀርቦ ሊሆን ይችላል። ስንዴ በይፋ ለቅዱስ ቁርባን ይውላል። ፍቅርም በይፋ ካልሆነ በቀር በድብቅ ወንጀል ነው። እንደ ዘመኑ ተፋቅሮ መጋባት አልነበረም። የጓያውን ስንመለከት የተከለከለ ነገርን እናይበታለን።

ጥቁር ድብቅ ነገርን ያሳያልና። አብሮ አደግን ማፍቀር ተፈጥሯዊ ቢሆንም በማህበረሰብ እሴት ግን እህት እና ወንድምነት እንዲጠነክር ነው የሚፈለገው። የሩቅ ሃገር ሰው ዘር እና ወገን ጠይቆ አፈላልጎ እንዲያገባ ነው የሚደረገው። ይሁኔ የገጠመው እንደ እህት ማየት የነበረበትን ልጅ አፍቅሮ ባህል እና እሴትን ጥሶ መሰናክል ነው። “ያምሸከሽከኛል” ሲል የድብቅ ፍቅር የበለጠ የበረታበት መሆኑን፣ የሚያውቁ ሰዎች አፍ ውስጥ መግባቱን ለመቋቋም ጉልበት ማጣቱን ያሳያል። “ወዳጅ አልሁሽ እንጂ ለብቸኝነቴ፤ የእህት ፍቅርንማ መቼ አጣሁ ከቤቴ” ቢላትም እሽ ልትለውና ሚስቱ ልትሆን አልቻለችም። አብሮ አደግን ማግባት በማህበረሰቡ የተፈቀደ ባለመሆኑ፣ ቤተሰቦቿ ንቀውታል። ሊያገባት ቢፈልግም እንኳን አልፈቀዱም። የዘፈኑን ግጥሞች እየሰማን ስንቀጥል ሁለቱ ጥንዶች ለካንስ ከመፋቀር ያለፈ አካላዊ ንክኪ ፈጽመዋል። “ዘመድ አዝማዶችሽ ካልዳሩሽ ደግሰው፣ በጓሮ እንደ ጀመርን በጓሮ እንጨርሰው” ብሎ ይሁኔ ምስጢር ያወጣል።

ሌላው “ግቢ ግቢ” ዘፈን በወቅቱ ብዙ ፓለቲካዊ ግምቶች እና ትንተናዎች ተሰጥተውበታል። የተወሰኑ ቅኔያዊ ግጥሞችን ቀንጭበን እንመልከት።

“ጸጉሯን አራት መቶ ገምቼላታለሁ

ደረቷን ሦስት መቶ ገምቼላታለሁ

ዳሌዋን መቶ ሃምሳ ገምቼላታለሁ

ከዳሌዋ በታች አልገመትሁላትም

በዓይን ያላዩት ነገር እምብዛም አያስዋሽም”

ይህ ግጥም የሰርግ ዘፈን የሚመስል ስሜት አለው። ባላገሩ ክብብ ብሎ ሲበላ እና ሲጠጣ የሚጨዋዎተው የትፍስሕት ዘፈን። በሰርግ ቤት ሙሽሪት ከሙሽራው ቤት እንደገባች ሲዘፈን ግጥሙን እድምተኛው የሚደረድረው ይመስላል። ጸጉሯ፣ ቆንጆ ነው፣ ደረቷም ሸጋ ነው፣ ዳሌዋስ ቢሆን ውብ አይደል፤ እንግዲህ ከዳሌ በታች ደግሞ ሙሽራው ዓይቶ ይንገረን የሚል ይመስላል። በገጠሩ ማህበረሰብ አንዲት ልጅ ከወንድ ጋር ሩካቤ ስጋ ሳትፈጽም ነው የምትዳረው። በዚህ ሙዚቃ ውስጥ ግን ልጅቱ ቆንጆ ናት ግን እንዲያው ክብረ ንጽሕናዋ ግን ያለ አይመስለኝም፣ ያጠራጥረኛል ብሎ የሚያስብ ሰርገኛ የገጠመውን ግጥም እናገኛለን።

“ድሪውንም ሽጪው ፈቅጄልሻለሁ

ጠልሰሙንም ሽጪው ግዴለም ብያለሁ

የእጅ አምባሩን ሽጪው ፈቅጄልሻለሁ

የእግር መስቀሉን ተይ እቃወመዋለሁ”

ይህም ግጥም ቅኔ ለበስ ነው። ውድ የማጌጫ እቃዎችን ፍቅረኛው ወይም ሚስቱ እንድትሸጥ ፈቅዶላታል። ድሪ፣ ጠልሰም፣ አምባር እንድትሸጥ ይፈቅድና መስቀሉን እምቢ ይላል። ከመስቀሉም የእግሩን ነው። እግር መስቀል ብልግና ነው። አትባልጊብኝ ለማለት ነው ይህ ሁሉ ነገር ለካንስ።

“ግቢ ግቢ” በሚለው ሙዚቃው ውስጥ እኔ ከወደድኋት ዝንጀሮም ትሁን ብሎ ለፍቅር ቁርጠኛነቱን ይናገራል። ሆኖም የልጅቱ ቤተሰቦች አያገናኙትም። አብዝተው ይከላከሉታል። ማህበረሰባችን ጋብቻን በብዙ መስፈርቶች ይመለከተዋል። ዘር፣ እምነት፣ ሀብት፣ ስም እና ዝናን ያያል ከጋብቻ በፊት።

“አባትሽ በአጥር ላይ የወረወሩኝ

እናትሽ በሰፌድ ዓይን ዓይኔን ያሉኝ

ወንድምሽ በሽጉጥ ትኩሶ ሳተኝ

አያትሽ በምርኩዝ አንዴ ዠለጡኝ

ወደል ውሻ አይደለሁ ሊጥ አልደፋሁኝ

አንቺን አንቺን ስል ነው የተገኘሁኝ”

የልጅቱ ቤተሰቦች ልጃቸውን የማይፈልጉት፣ ለማግባት መስፈርታቸውን የማያሟላ ወንድ ሲከታተልባቸው በግነዋል። እናት፣ አባት፣ ወንድም፣ አያት ሁሉም ጠላት አድርገው አሳደውታል።

በዚሁ “ግቢ ግቢ” አልበም ውስጥ ሳናሞናሙነው በሚለው ሙዚቃው ይሁኔ ሌላ ልጅ ወዶ እንደገና ቤተሰቦቿ ሲከላከሉት እናያለን። እባክሽ ዛሬ ጽደቂብኝ ብሎ ቢለምናትም እንኳን ይህች ልጅ ከቤት መውጣት የቻለች አትመስልም። ሳናሞናሙነው ማለት ስጋዊ ተራክቦ ማድረግን የተሸከመ ቃል ነው።

“አባትሽ አይሙቱ ለእኔም አባት ናቸው

እንዳትመጪ አስቀሩሽ እኔ ምን አልኋቸው

እናትሽስ ምነው እኔን መጥመዳቸው

ቆንጆ አምጠው ወልደው ያስወጉኝ እሳቸው”

ብሎ በፍቅሯ እንዲያነክስ ያደረገውን ጓያ አሁንም ይጠቅሰዋል። በሁለቱም ሙዚቃዎች ውስጥ ሴት ልጅ ከወላጆቿ ጉያ ወጥታ ከባህል እና እሴት ውጪ ወንድ ጋር መገናኘት እንደማትችል አይተናል። ወላጆች ለስርዓት ያላቸውን ቀናኢነት፣ ለሞራል እና እሴት መጠበቅ የማያደርጉትን ጥረት አስተውለናል።

“አሆ በል” በሚለው ሙዚቃው ይሁኔ አሁንም ፍቅር የቀናው አይመስልም።  ቀደም ሲል ጓያ እና ስንዴ ብለን ያነሳነው ቅኔ ለበስ ግጥም ተመልሶ ያመጣዋል። ጓያ መሰል ሰባሪ ፍቅሯ አሁንም ተመልሶ ይዞታል። ቀደም ሲል በስንዴ የመሰለውን የገሀድ ፍቅር አሁን ደግሞ   በሽንብራ ተክቶት እሷን ለመርሳት ሲቸገር እናያለን። ከሞላው ቆነጃጅት፣ የውበት  ማሳ መሀል ገብቶ አሁንም ያለአቅሙ መውደዱን ይነግረናል። ፍቅሩን በይፋ ለማውጣት አይችልም። ፍቅሩን ግን ውስጥ ውስጡን መጀመሩን ይናገራል። የልጅቱ ፍቅር ቢጸናበት እና እንደጓያ የሰበረው ቢመስለንም ቅሉ ይሁኔ አንዳች ምስጢር ሹክ ይለናል። በድብቅ የወደዳት ልጅ ጋር ከባድ ፍቅር ውስጥ መውደቁን፣ በሽንብራ እንደወከላት ሴት በይፋ ፍቅሩን ማጣጣም ባይችልም እንኳን ልጅቱ ጋር አካላዊ ንክኪ ፈጽሟል። “ነካክቼ ቀረሁ ጓያዋ ሰበረችኝ” የሚለው ቅኔ ነው። የድብቅ ጅምር ፍቅር ለመርሳት የእግር እሳት እንደሆነበትም ነግሮናል።

እሸት በዓይኔ በዓይኔ ውል ብሎብኝ

“ ዘመም ዘመም ሲል አዝመራው ታይቶኝ

ከማሳው ገብቼ ሲያቅነዘንዘኝ

መጠርጠር ሲገባኝ ሽምብራ መስላኝ

ጓያ ፍቅር ሆና ወገቤን  ይዛኝ

ነካክቼ ቀረሁ መነሻም የለኝ”

“አሎ ሉሎ” አልበም የአልበሙን መጠሪያ ሙዚቃ ጨምሮ ሌሎች ባህል ቀመስ ዘፈኖች ቀርበውበታል። ቅበጪልኝ ሙዚቃ የአብሮ አደግን ፍቅር በማነሳሳት በባላገሩ አካባቢ ያሉ ባህሎችን ያነሳሳል። የስንዴ እንኩቶ  በመብላት የገጠር ልጆችን ትዝታ፣ የጎረቤት ልጅን ፍቅር ፣ ያነሳል።

… ይቀጥላል

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here