የአስነባቢው ጉዞ

0
132

“የታሪክ፣ የሥነ ልቦና፣ የቢዝነስ፣ የፍቅር፣ የሳይንስ፣ የዕምነት እና ሌሎች መጽሐፎች አሉኝ። መጽሐፍ ፈላጊ …” እያለ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በተለያዩ ቀበሌዎች እየዞረ መጽሐፎችን ይሸጣል:: አበበ መኮንን ይባላል:: ተወልዶ ያደገው በአማራ ክልል በሜጫ ወረዳ ውስጥ ነው:: ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱንም የተማረው በዚያው በሜጫ ወረዳ ውስጥ ነው:: በ2011 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናውን ወስዶ በጥሩ ውጤት በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የመማር ዕድልን አግኝቷል፤ ነገር ግን በወቅቱ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዷል::

አበበ በትምህርት ላይ እያለ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የመማር እና በሚሠለጥንበት የትኛውም የሙያ መስክ ራሱን እና ሀገሩን ለማገልገል ከፍ ያለ ህልም ነበረው:: ከትምህርቱ በኋላ ራሱን በሥራው ዓለም ውስጥ አስገብቶ ወላጆቹን የመደገፍም ራዕይም አንግቦ ነበር፤ እነዚህ ምኞቶቹ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በማቋረጡ ሥጋት ላይ ቢወድቁም አበበ ግን ለራሱ የሰጠው ቦታ ትልቅ ነው:: ህልሙም፣ ራዕዩም አብረውት አሉ::

አበበ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በተለያዩ አከባቢዎች እየተንቀሳቀሰ መጽሐፎችን ይሸጣል:: መጽሐፍ ለመሸጥ ያነሳሳው ገፊ ምክንያት ደግሞ ራሱን ከዕውቀት ላለማራቅ እና በምክንያት ካቋረጠው የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ ባልተናነሰ መልኩ ከመጽሐፎች ዕውቀት ለማግኘት እንደሆነ ይናገራል::

አበበ የመጽሐፍ ማዞር ሥራውን የጀመረው በስድስት ሺህ ብር የመነሻ ካፒታል ነው፤ ይህንኑ የመነሻ ካፒታሉን አስመልክቶ ሲያስረዳ “በትንሽ መጽሐፎችና  በትንሽ የመነሻ ገንዘብ ሥራውን መጀመር ይቻላል” በማለት ሥራው ብዙ ገንዘብ የማይጠይቅ መሆኑን ይናገራል:: ለሱ የመነሻ ካፒታል ምንጭ የሆኑት ወላጆቹ መሆናቸውንም ነግሮናል::

አበበ የመጽሐፍ ማዞር ሥራ ድካም ቢኖረውም ሳይደክሙ ማግኘት እንደማይቻልም ያምናል፤ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የመጽሐፍ አንባቢዎችን አገኝባቸዋለሁ በሚላቸው ቦታዎች ሁሉ እየተንቀሳቀሰ መጽሐፎችን ለአንባቢ ዕይታ ያቀርባቸዋል:: አበበ በኪሎ ሜትር በቀን ይሄን ያህል እጓዛለሁ ብሎ መገመት ቢሳነውም ከጥቂት ጊዜያት እረፍት በስተቀር ቀኑን ሙሉ መጽሐፍ እያዞረ እንደሚሸጥም ነግሮናል::

ከ20 እስከ 60 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ መጽሐፎችን በቦርሳና በእጆቹ ተሸክሞ አንባቢዎችን ፍለጋ ይንከራተታል፤ የባሕር ዳር ጸሐይም ሆነ ብርድ ለእሱ ምኑም አይደሉም:: አበበ ራሳቸውን ሥራ አጣን ብለው ከሚፈርጁ ወጣቶች ተርታ መመደብ ስለማይፈልግ መጽሐፍ አዙሮ መሸጥን ሥራው እና እንጀራው አድርጎ ቀጥሎበታል::

“በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በርካታ አንባቢዎች አሉ ባይባልም ውስን አንባቢዎች ግን አሉ” የሚለው አበበ አብዛኛዎቹ አንባቢዎች የሚመርጧቸው መጽሐፎች ከሥራዎቻቸው ጋር የሚቀራረቡ ወይም ለሕይወታቸው የሚያስፈልጓቸውን እንደሆነም በሥራ ሂደቱ ታዝቧል::

አንዳንድ አንባቢዎች መጸሐፎችን ሳይመርጡ ማለትም ሁሉንም ዓይነት ይዘት ያሏቸውን መጸሐፎች እንደሚያነቡ የገለጸው አበበ የዚህ ዓይነት አንባቢዎች ቁጥር ግን በጣም ትንሽ እንደሆነ አንስቷል:: የአበበ ትዝብት በዚህ ብቻ የተገታ አይደለም፤ አንዳንድ አንባቢዎች ማንበብ የሚፈልጓቸው መጽሐፎች  ውድ በመሆናቸው ምክንያት ዋጋቸው የሚቀንሱ መጽሐፎችን ገዝተው ለማንበብ ሲገደዱ ማስተዋሉንም ገልጾልናል::

በእሱ ምልከታ ብዙ ሰዎች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ ያሳልፋሉ፤  መጽሐፍ በማንበብ ቢያሳልፉ ግን የተሻለ ዕውቀት እና ግንዛቤ እንደሚኖራቸው ይናገራል:: የመጽሐፎች መወደድ ለብዙ ሰዎች አለማንበብ አንዱ ምክንያት እንጂ የመጨረሻው ምክንያት ሊሆን አይችልም የሚለው አበበ ብዙ ሰዎች ገንዘባቸውን ለመጸሐፍ ከሚያወጡ ይልቅ ለሱስ ለሚዳርጉ ነገሮች ማለትም ለጫት፣ ለመጠጥ፣ ለሲጋራ፣ ለቁማር እና ለሌላም እንደሚያወጡ መታዘቡን ገልጾልናል::

እውነተኛ መጽሐፍ የማንበብ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ከመጽሐፍ መደብሮች መጽሐፎችን እየተዋሱ ጭምር ያነባሉ፤ ከጓደኞቻቸው እየተዋሱ ያነባሉ:: ወደ ሕዝብ ቤተ መጽሐፎች እየሄዱ ያነባሉ እንጂ መጽሐፎች ስለተወደዱ ማንበብ አልቻልንም ብለው ማንበባቸውን አያቆሙም ሲል ወጣቱ ትዝብቱን አጋርቶናል::

ብዙ ወጣቶች በፑል ቤት፣ በከረንቡላ ቤት፣ በዲ ኤስ ቲቪ ቤት፣ በውርርድ (ቤቲንግ) ቤት እና በሌሎችም ቦታዎች እንጂ በማንበቢያ ቦታዎች እንደማይታዩ የገለጸው አበበ በተለይ የማኅበራዊ ገጾች ላይ ተጥደው በሚውሉ ወጣቶች ምግባር እንደሚያዝንም ገልጾልናል:: ማኅበራዊ የትሥሥር መረቦችን በአግባቡ የሚጠቀሙባቸው ወጣቶች አትራፊዎች መሆናቸውን የሚናገረው አበበ ብዙዎቹ ወጣቶች ግን ማኅበራዊ ገጾችን የሚጠቀሙት ለአይረቤ ጉዳዮች መሆኑንም ተናግሯል::

አበበ ራሱን ከብርቱ አንባቢዎች ተርታ እንደማይፈርጅ ገልጾልናል፤ ምክንያቱ ደግሞ እሱ በመጽሐፍ ማዞር ሥራው በጣም ስለሚደክመው ለንባብ ትኩረት ሰጥቶ ማንበብ አለመቻሉ ነው:: ያም ቢሆን ግን ባገኘው አጋጣሚ እና በዕረፍት ሰዓቱ ከሚያዞራቸው መጽሐፎች ውስጥ ብዙዎቹን ስለማንበቡ ነግሮናል:: ወደ ፊት ደግሞ መጽሐፎችን በብዛት በማንበብ ከአንባቢዎች ተርታ መካተት ከመፈለጉም በተጨማሪ በንባብ ከሚገኙ ጥቅሞች ተጋሪ ለመሆን ጽኑ ፍላጎት እንዳለውም ገልጾልናል::

አበበ በመጽሐፍ ሺያጭ ብዙ ገቢ የማይገኝ ቢሆንም እሱ ግን የሚያገኘውን ገቢ በአግባቡ በማሥተዳደር ላይ ይገኛል፤ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው ከሚያገኘው ገቢ ላይ እየቆጠበ በአድማስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በርቀት ትምህርት የማኔጅመንት የ4ኛ ዓመት ተማሪ መሆኑ ነው::

ከወራቤ ዩኒቨርሲቲ ያቋረጠውን ትምህርት እየሠራ በመማር ላይ የሚገኘው አበበ በትምህርትም ሆነ በሌላ ጉዳይ ከአቅማችን በላይ በሆነ ምክንያት ያቋረጥነውን ነገር አቅማችን በፈቀደ ጊዜ መቀጠላችን የጥንካሬያችን መገለጫ ነው የሚል አስተያየቱንም አጋርቶናል::

ሥራን ሳይንቁ መሥራት ለነገ ሕይወት መንገድ የመጥረግ ያህል አስፈላጊ ነው ያለው አበበ በተለይ ወጣቶች ሥራ አጣሁ ከሚል ሰበብ ወጥተው በአቅማቸው መሥራት በሚችሉት ሥራ ላይ መሠማራት እንዳለባቸው መክሯል::

ወጣቶች መጽሐፎችን በብዛት ማንበብ እንዳለባቸው እና ከመጸሐፎች በርካታ ዕውቀት እንደሚገኝ ተሞክሮውን አካፍሎናል፤ አንዳንድ ወጣት አንባቢዎች ከዕድሜያቸው በላይ አሳቢ እና ተናጋሪ እንዲሆኑ ያስቻላቸው የንባብ ልምዳቸው መሆኑን መታዘቡንም ገልጾልናል::

አብዛኛው መጸሐፍ የሚገዙት ደንበኞቹ ዕድሜያቸው ከ40 በላይ እንደሚገመቱ ያነሳው አበበ የወጣቶች ቁጥር ግን አነስተኛ መሆኑን ነው የነገረን:: እሱ እያዞረ የሚሸጣቸውን መጸሐፎች ከተለያዩ የመጸሐፍ መደብሮች እንደሚገዛቸው በመግለት፣ በመጸሐፍ መደብሮች ያጣቸውን እና በአንባቢ ደንበኞቹ የተፈለጉ መጸሐፎችን ደግሞ ከአዲስ አበባ በስልክ እየደወላ እንደሚያስመጣም አጫውቶናል::

የመጸሐፍ አዟዋሪዎች በመጸሐፉ ዋጋ ላይ ያለውን የገንዘብ መጠን እየሰረዙ ራሳቸው የፈለጉትን ዋጋ ይለጥፉበታል የሚል ቅሬታ ይነሳል፤ ለዚህም አበበ ሲመልስ ይህንን የሚያደርጉ የመጸሐፍ አዙዋሪዎች የሉም ማለት አልችልም፤ ግን ደግሞ ሁላችንም የመጸሐፍ አዟዋሪዎች በጅምላ መወቀሳችንም ትክክል አይደለም ብሏል::

ከዚህ በተጨማሪም መጸሐፎችን ከመጸሐፍ መደብሮች የምንረከብበት ዋጋ እና በመጸሐፉ ላይ ያለው ዋጋ ተመሳሳይ የማይሆኑበት አጋጣሚ አለ:: በተለይ መጸሐፎቹ በገበያ ላይ የሌሉና ቆየት ያሉ ከሆኑ መጸሐፍ መደብሮቹ ለኛ የሚያስረክቡበት ዋጋ በመጸሐፉ ላይ ከሰፈረው ዋጋ ጋር ላይመሳሰል ይችላል (ይጨምራል) በማለት በመጸሐፎች ዋጋ ዙሪያ ለሚነሳው ቅሬታ ትዝብት አዘል ምላሹን ሰጥቶናል::

አበበ በመጨረሻም የሚከተለውን መልዕክቴን ላስተላልፍ በማለት  “ወጣቶች ከፊታቸው ላስቀመጡት ዓለማ በትንንሽ ምክንያቶች መዛል የለባቸውም” ብሏል::

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here