ልጆችን ከአንድ በላይ ቋንቋ እንዲናገሩ ማስቻል፣ በተለይም ለዓዕምሮ ዝግመት ተጠቂዎች የተለያዬ አስተሳሰብ እና አመለካከቶችን ተረድተው የማገናዘብ ዓቅምን እንደሚያሳድግላቸው ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::
በአሜሪካ የሚያሚ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ባካሄዱት ጥናት ከአንድ በላይ ቋንቋ የሚናገሩ ልጆች ስሜታቸውን በመቆጣጠር የተለያዩ ተግባራትን የመፈፀም ዓቅም እንደሚያዳብሩ አረጋግጠዋል::
ልጆችን ከአንድ በላይ ቋንቋ እንዲናገሩ ማስቻል ከማስፈፀም ዓቅም ችሎታ ጋር እንደሚቆራኝ እና ይህም የዓዕምሮ ዝግመት ምልክቶችን እንደሚያሻሽል ነው ያሰመሩበት – ተመራማሪዎቹ::
በታዳጊዎች ላይ ማህበራዊ የግንኙነት ችግሮች እና የመፈፀም አቅምን መገደብ፣ ተደጋጋሚ ባህሪያትን ማሳየት የመሳሰሉትን ለማሻሻል ዓቅም ይፈጥራል- ከአንድ በላይ ቋንቋ መናገር መቻል::
ከተመረጡ ቤተሰቦች የሚገኙ ከ100 የሚበልጡ ከፊሎቹ የዓዕምሮ ዝግመት (ኦቲዝም) ተጠቂ እና ከፊሎቹ ተጠቂ ባልሆኑ የጥናቱ ናሙና በተካሄደባቸው ልጆች – ወላጆች ከአንድ በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ልጆቻቸው የተገኙ ለውጦችን እንዲመዘግቡ ተደርጓል::
በክትትሉ ከተመዘገቡ ለውጦችም ታዳጊዎቹ የሚከለከሉትን የመግታት፣ የተለያዩ አመለካከቶችን መረዳት የሚያስችላቸውን ደግሞ ለማስቀጠል ዓቅም ማዳበራቸው ነው በማጠቃለያ ውጤትነት የተቀመረው::
በካሊፎርኒያ እና ሎስአንጀለስ ዩኒቨርሲቲ ኘሮፌሰር እና የዓዕምሮ ዝግመት እና ተዛማጅ ጉዳቶች ህክምና ማዕከል ዋና ስራ መሪ ከአንድ በላይ ቋንቋ ተናጋሪነት በታዳጊዎች ላይ አወንታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ በግኝትነት ነጥሮ መውጣቱን አረጋግጠዋል::
የዓዕምሮ ዝግመት ባለባቸውም ሆኑ ከሌለባቸው ታዳጊዎች ወላጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋም ሆነ በአዲስ ቋንቋ ከመግባባት እንዲታቀቡ እንደሚያደርጉ ደርሰውበታል:: ለዚህ ምክንያቱ ሊከብዳቸው ወይም ይጠጥርባቸዋል ከሚል መሆኑን ነው ያረጋገጡት::
በመጨረሻም ታዳጊዎች ከአንድ በላይ ቋንቋ በቤት ውስጥ እንዲናገሩ ማስቻል ጥቅም እንጂ ጉዳት የሌለው መሆኑን በማጠቃለያነት አስምረውበታል- ተመራማሪዎቹ::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም