በዓለማችን ከሚገኙት 45 ሺህ የሸረሪት ዝርያዎች ብቸኛው ቅጠላ ቅጠል ወይም እፅዋት በል (ካርኒቨረስ)ባጋሀሪ ኪኘሊንጊ የተሰኘው መሆኑን ኦዲት ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
በማእከላዊ አሜሪካ እና ሜክሲኮ በሚገኝ ደን ብቻ የሚኖረው ድር የማያደራው የሸረሪት ዝርያ እስከ ስድስት ሚሊ ሜትር ርዝመት ያለው ነው:: የሸረሪት ዝርያው የግራር ዛፍ ቅጠል ወይም ቀንበጥን ለምግብነት እንደሚያውል ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በ2001 እ.አ.አ በኮስታሪካው የብራንዲስ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ ነው:: በ2007 እ.አ.አ በአሜሪካ ፔንስላቫኒያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በሆነው ክሪስቶፈር ሚሃን ሸረሪቱ ቅጠላቅጠል በል መሆኑ ዳግም ተረጋግጧል::
የሸረሪት ዝርያዎቹ እንደሌሎቹ ድር የማያደሩት ነፍሳትን በማጥመድ ለምግብነት ስለማያውሉ ነው፤ ሲጓጓዙም በሸረሪት ድር ላይ በመንጠልጠል ሳይሆን በመዝለል ከቦታ ቦታ እንደሚጓጓዙ ተመላክቷል::
ባጋሀሪ ኪኘሊንጊ የተሰኘው የሸረሪት ዝርያ በአብዛኛው የግራር ዛፍ እንቡጥ ቀንበጦችን ነው ለምግብነት የሚያውለው:: እምቡጥ ለጋ ቅጠሎችን ቀረጣጥፎ ለሚበላው ሸረሪቱም ዋነኛ አስፈሪ ተቀናቃኞች አሉበት – ጉንዳኖች::
ጉንዳኖች የግራር ዛፍ እምቡጥ ቅጠሎችን ቀረጣጥፈው በማጓጓዝ አጠራቅመው የሚበሉ በመሆናቸው ከባጋሀሪ ኪኘላንጊ ጋር መፋጠጣቸው አልቀረም:: ሆኖም ተንኳሽ በቡድንም ሆነ በነጠላ የሚያጠቁት ጉንዳኖች ሸረሪቶቹን እንደሚያሸነፏቸው ነው የተገለፀው::
ባጋሀሪ ክኘሊንጊ ሸረሪቶች ጉንዳኖችን ተፋልሞ መርታት አይሆንላቸውም፤ አይሞክሩትምም፤ ለምግብነት የሚያውሉት ብቸኛ ቀምበጥ ግራርን በመሆኑ የወረሩት ጉንዳኖች የሚበቃቸውን ቀረጣጥፈው ቀጣናውን እስኪለቁ መጠበቅ ግድ ይላቸዋል::
ሸረሪቶቹ በርቀት ጉንዳኖቹ ከቀንበጦቹ መራቃቸውን እና ግራሩ ከስጋት ነፃ መሆኑን ሲያረጋግጡም ቀንበጡ ላይ ተጣብቀው ለጋ ቅጠል እና እመቡጡን እንደሚበሉ ነው ያረጋገጡት – ተመራማሪዎቹ::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም