ቀድሞ ነበር እንጂ…

0
111

በቻይና ከሻንጋይ ደቡብ ምዕራብ በምትገኘው ጂንዢ (jinxi) ከተማ አቅራቢያ አዲስ በሚሰራ አውራ ጐዳና መካከል ላይ ቀደም ብሎ የተገነባን የመኖሪያ ቤት ለማፍረስ መንግሥት ባቀረበላቸው የካሳ ክፍያ ባለመስማማታቸው በሌላ አማራጭ ተገንብቶ መጠናቀቂያው ሲቃረብ ባለንብረቱ መፀፀታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል::

ከጥቂት ዓመታት በፊት በጂንዢ ከተማ አቅራቢያ ለሚሰራው አውራ ጐዳና ቅየሳው በሚያልፍበት መስመር ላይ የነበሩ በርካታ መኖሪያ ቤቶች ካሳ ተከፍሏቸው ሲነሱ  አዛውንቱ ግን የተጋነነ  ካሳ ክፍያ በመጠየቃቸው ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ይቀራሉ:: መንግሥት ያቀረበላቸው የካሳ ክፍያ 220,700 ዶላር ነበር- አዛውንቱ የጠየቁት ግን ከተወሰነላቸው በእጅጉ የበለጠ እንደነበር ነው ድረ ገጹ ያስነበበው::

በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለስልጣናት የግለሰቡን መብት ማክበር እንደሚጠበቅባቸው ይወስናሉ:: ነገር ግን አማራጭ ስልት አስቀይሰው ባለ ሁለት ፎቁ የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ባለበት ሳይነካ እንደ ቀለበት መንገድ በዙሪያው አውራ ጐዳናው ለሁለት ተከፍሎ እንዲያልፍ ነው ያደረጉት::

የአውራ ጐዳናው ግንባታ ለኗሪዎች ብሎም ለአገሪቱ የሚያበረክተውን አስተዋፆኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት የመሰረተ ልማቱ ተዘርግቶ መጠናቀቂያው ሲቃረብ ግን እምቢተኛው ባለንብረት ውሳኔያቸው የተሳሳተ መሆኑን አምነው መፀፀታቸውን ድረ ገጹ አስነብቧል::

የፎቅ ቤታቸው የላይኛው ጣሪያ ከጐዳናው ጋር እኩል በመሆኑ የግንባታ ማሽኖች ድምፅ እንደሚያውክ ተረድተዋል- ባለንበረቱ:: በሌላ በኩል ባለንብረቱ ከመኖሪያ ቤታቸው ወደ ከተማ ለመውጣት በሲሚንቶ በተሰራ ቦይ ውስጥ ለውስጥ ተሽሎክልከው ለማለፍ ተገደዋል::  ይሄ በራሱ የራስ ምታት እንደሆነባቸውም ጠቁመዋል::

በአውራ ጐዳናው መካከል እንደምስማር የተቸነከረው ባለሁለት ፎቅ ቤት ለጊዜው ባልተለመደ – ለየት ባለ ቦታ በመገኘቱ የጐብኚዎችን  ቀልብ ቢስብም አዛውንቱ ግን በቀድሞው ውሳኔያቸው በእጅጉ መፀፀታቸው ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው:: (

ታምራት ሲሳይ)

በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here