የመሬትን ለጋስነት ለማስቀጠል

0
148

እንደ መንደርደሪያ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዓለም ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና ከፍተኛ ሙቀት እየተፈራረቁባት ትገኛለች::የመሬት መንሸራተት እና መደርመስም በሀገራችን ሳይቀር ተከስቶ ዜጎችን ለሞት እና መፈናቀል ዳርጓል::ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ የሰው ልጅ ለእግሩ መረገጫ፣ በሕይወት ለመኖር የስንቁ መሠረት ለሆነችው መሬት የሰጠው የደኅንነት ዋስትና ዝቅተኛ በመሆኑ ነው የሚሉት በርካቶች ናቸው::ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር ተከትሎ ለእርሻ የማይውሉ መሬቶችን ለእርሻ ለማዋል፣ የማገዶ እና የግንባታ ፍጆታ መጨመር መሬት ደኅንነቷ ስጋት ውስጥ እንዲገባ አድርጓታል፤ ዛሬም የሰው ልጅ ደኅንነቱን ጠብቆ የተፈቀደለትን ዕድሜ ይኖር ዘንድ የማንቂያ ደወሏን እያሰማች ነው::

ደቡብ ኮሪያ ለማንቂያ ደወሉ ቀድሞ ምላሽ በመስጠት እና ውጤታማ ሥራ በማከናወን በቀዳሚነት የምትነሳ ብትሆንም ኢትዮጵያም  ትኩረት ሰጥታለች::የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ሥራ ደግሞ ለፍጡራን ሁሉ መኖሪያ እና ማኖሪያ ለሆነችው መሬት ዋና መሠረት ተደርጓል::ይህም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በዋናነት የአፈር ክለትን በመጠበቅ እና በጎርፍ እና በወንዞች ሙላት ታጥቦ የሚሄደውን ኬሚካላዊ ይዘት በመታደግ ምርታማነት እንዲያድግ ያደርጋል::

 

የአፈር መሸርሸር ተጽእኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ

በዓለም ላይ በከባድ ዝናብ እና በጎርፍ ምክንያት በሚያጋጥም ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር በየዓመቱ ከስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደምታጣ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ከፍተኛ ተመራማሪው ኃይሉ ክንዴ (ዶ/ር) ከበኲር ጋዜጣ ጋር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል::ይህም ለ34 በመቶ የሰብል ምርት መታጣት እና ለሦስት ነጥብ ሰባት በመቶ የዋጋ ንረት ይዳርጋል፡፡

ኢትዮጵያ ምን ያህል የባከነ መሬት አላት

ኢትዮጵያ በመኸር እና በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬትን ከበቂ ውኃ ጋር አቀፋ የያዘች ሀገር ናት::ይሁን እንጂ እንደ ሀገር 54 ሚሊዮን ሄክታር መሬት፣ አማራ ክልልም ካለው አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 63 በመቶ የሚሆነው የተጎሳቆለ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል::

በጋዜጠኛ ስለአባት ማናዬ የተጻፈው የዓባይ ፖለቲካ እና የባዕዳን ተልዕኮ መጽሐፍ በዓባይ ወንዝ ብቻ የምታጣው የደለል አፈር መጠን 1 ጥብ 3 ቢሊዮን ቶን ነው። ይህ ከሀገር ውጪ ይዞት የሚወጣው ነው። ከዚህ ውጭ ሌሎች ወንዞች ምን ያህል ለም አፈርን ወደ ሐይቆች እና ባህሮች ይገብራሉ የሚለው ሌላው የሚጤንበት ጉዳይ ነው። ይህም የሚያሳጣው ምርታማነትን፣ ሐይቆችን እና ባህሮችን ነው። የሐይቆች እና ባህሮች በደለል መሞላት ደግሞ ሀገሪቱ ያላትን የውኃ ሐብት እንድታጣ ከማድረግም ባሻገር የአሳ ሐብት እና ሌሎች የውኃማ አካላት እንስሳትን ያሳጣል። ይህም ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲቀንስ፣ የሥራ ዕድል መፍጠሪያነቱንም እንዲያጣ ያደርገዋል።

ኢትዮጵያ ለምን ከፍተኛ መሬቷ ተጎሳቆለ፣ ሁሉን አብቃይ ለም አፈሯስ ለምን የውጭ ሀገራት ሲሳይ ሆነ ተብሎ ሲጠየቅ ምላሹ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ላይ የሚሠራው ሥራ አናሳ መሆን፣ ግንዛቤውም ካለማደጉ ጋር የሚያያዝ ነው::

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ መቼ እና እንዴት ተጀመረ?

አቶ እስመለዓለም ምህረቱ በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሐብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር ናቸው::የተቀናጀ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ የተለያዩ ስያሜዎች ይዞ ዛሬ ድረስ ሲደርስ ጅማሮውን የሚያደርገው ከ1960ዎቹ መጨረሻ፣ ከ1970 ዎቹ መጀመሪያ ዓ.ም ጀምሮ ነው ይላሉ::

የድርቁን ተጽእኖ መቋቋም ደግሞ ለአጀማመሩ ገፊ ምክንያት ነበር::“ምግብ ለሥራ” በሚል እንደተጀመረ አቶ እስመለዓለም አስታውሰዋል::ከ1980 ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ ተፋሰስን መሠረት አድርጎ ሲሠራበት ቆይቷል::ከ1997 (98) ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በፌደራል ደረጃ ወጥ የሆነ መመሪያ ተዘጋጅቶለት ወደ ሥራ ተገብቷል::

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በልዩነት በ2003 ዓ.ም እንደተጀመረ ተደርጎ እየተነገረ ያለው ንግርት ምናልባትም ሁሉም የድርሻን አውቆ እንዲሠራ የተደረገበት በመሆኑ ነው::በወቅቱ ለሥራው ውጤታማነት እና አርሶ አደሩ ችግሩን አውቆ በባለቤትነት እንዲያስቀጥለው ሆኖ ሥራው በዘላቂነት እንዲሠራ ለአርሶ አደሩ የ15 ቀናት ስልጠና መሰጠቱን ያስታውሳሉ::

የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራው ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎን እያገኘ ዛሬን ደርሷል::የክልሉ ግብርና ቢሮ የ2017 ዓ.ም የበጋ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራን ጥር 15 ቀን በሰሜን ወሎ ዞን ዋድላ ወረዳ አስጀምሯል::336 ሺህ ሄክታር መሬት እና ዘጠኝ ሺህ 87 ተፋሰሶች የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራው አካል ናቸው::አቶ እስመለዓለም ለበኵር ጋዜጣ በስልክ እንዳስታወቁት የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራው በሁሉም ዞኖች፣ በ125 ወረዳዎች እና በአንድ ሺህ 419 ቀበሌዎች እየተከናወነ ነው፡፡

የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደርም ከዳንግላ ከተማ እና ዙሪያ ወረዳው ውጪ ባሉ አሥር ወረዳዎች የተቀናጀ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ እያከናወነ ይገኛል::የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አዲሱ ስማቸው እንዳስታወቁት በአዲስ እና በነባር ዘጠኝ ሺህ 524 ሄክታር መሬት እና 471 ተፋሰሶችን ለማልማት እየተሠራ ነው::ሥራው ይከናወንባቸዋል ከተባሉ 204 ቀበሌዎች ውስጥ ምክትል ኃላፊዉ ለዚህ ዘገባ ከበኵር ጋዜጣ ጋር በስልክ ቃለ መጠይቅ እስካደረጉበት ጊዜ ድረስ በ104 ቀበሌዎች ሥራዉ እየተከናወነ ነው::

ምን ውጤቶችን አስገኘ?

አቶ በላይነህ አሊጋዝ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር የጓንጓ ወረዳ ሰሜን ደገራ ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው::የተቀናጀ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራን ለራሳቸው ብለው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል::ያገኙትን ጥቅምም በዝርዝር ያስረዳሉ፤ አሸዋማ አፈር ኖራቸው ለሰብልም ሆነ ለከብት ሳር ማብቀል ተስኗቸው የነበሩ መሬቶች ዛሬ ተመልሰው ወደ እርሻ ገብተው የተሻለ ምርት እየተገኘባቸው መሆኑን ተናግረዋል::ይህ የሆነው በየጊዜው የሚሠራው የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ በዝናብ እና ጎርፍ ታጥቦ በወንዞች ይወሰድ የነበረውን ደለል አፈር በመሬቱ ላይ በማስቀረቱ ነው::

በቀደሙት ዓመታት ቀድሞ የተሠራው የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ በዘር ወቅት በዘር ለመሸፈን ሲባል ተመልሶ ይደፈን እና ይፈርስ እንደነበር አርሶ አደሩ ያስታውሳሉ::ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ ውዳቂ መሬቶች ወደ ሰብል፣ አትክልት እና ፍራፍሬ እያስገባ መሆኑን በተግባር በማየቱ ራሱ ለተሠሩ ሥራዎች ጠባቂ እና ከለላ እየሆነ መጥቷል ብለዋል::ከምርት ውጪ የሆነ መሬትን በተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ ለመመለስ ጥረት ሲደረግ ቢያንስ የአፈር ለምነቱ በአስተማማኝ ደረጃ እስኪመለስ ጊዜ ድረስ ከልማት ውጪ ሆኖ እንዲቆይ አርሶ አደሩም ባለቤት ሆኖ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል::

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ በበኩላቸው ማኅበረሰቡ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሐብት ልማት ጥበቃ ሥራን ባህሉ አድርጎ ያለማንም ጎትጓች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል::ይህም የባህሪ ለውጥ የመጣው አርሶ አደሩ እየተሠሩ ባሉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች እየመጣ ያለውን ለውጥ በተግባር በመመልከቱ ነው ብለው ያምናሉ::

በየዓመቱ እየተሠሩ ያሉ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራዎች የአፈር ለምነትን በመመለስ፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የተፋሰሶችን ሕልውና በማስጠበቅ እና የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ በማድረግ ረገድ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ማሳያ እያነሱ ምክትል ኃላፊዉ ያስረዳሉ::በተለይ እየተሠሩ ያሉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች የአፈር ክለትን በ50 በመቶ መቀነስ መቻሉን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና የልሕቀት ዲዛይን እና ቁጥጥር ባለሥልጣን  ጥናትን መሠረት አድርገው አስታውቀዋል::የውኃ ስርገት መጨመር መቻሉን፣ የጠፉ ምንጮች መመለሳቸውን፣ ያሉትም ኅይላቸው መጎልበቱን ኃላፊዉ ጠቁመዋል::የተስተካከለ የአየር ንብረት በመፍጠር እና ያለውን በማስቀጠል ረገድ የታየው ለውጥም ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል::በቂ የእንስሳት መኖ ምንጭነትን መፍጠርም ተችሏል::

አቶ እስመለዓለም በበኩላቸው የአፈር እና ውኃ እቀባ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራው በሰብል፣ በአትክልት፣ በፍራፍሬ፣ በቅመማ ቅመም፣ በእንስሳት እና አሳ ዘርፍ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ማድረጉን  ተናግረዋል::ይህም የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ የሕዝብ ባለቤትነት እንዲያገኝ ማድረጉን ገልጸዋል::

የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ከፍተኛ ተመራማሪዉ ኃይሉ ክንዴ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከ2003 እስከ 2014 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ተግባራዊ ያደረገችው የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ የአፈር ለምነት እንዲሻሻል ማድረጉን በጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋል::ይህ ውጤት የተመዘገበው ግን  በጥንቃቄ በተያዙ፣ በሕግና ደንብ እየተመሩ ባሉ፣ የተፋሰስ ኮሚቴ ባላቸው እና ማኅበረሰቡ በስፋት በተሳተፈባቸው 92 ተፋሰሶች ላይ በተካሄደ ጥናት ሲሆን የለምነት መጠኑ በ21 በመቶ ከፍ ማለቱን ነው በማሳያነት ያነሱት:: ይህም የአፈር ለምነቱን ለመጠበቅ ይወጣ የነበረውን የአፈር ማዳበሪያ ወጪ ዝቅ እንደሚያደርገው ያምናሉ፡፡

የቢሮዉ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) የተሻለ ሥራ በተሠራባቸው አካባቢዎች 72 በመቶ የምርት ጭማሪ መመዝገቡን የበጋ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ ገጸ በረከት አድርገው አንስተዋል፡፡

ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች

በየዓመቱ የሚከናወነው የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ በምርታማነት እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እያበረከተ ያለውን አዎንታዊ ተጽእኖ ለማስቀጠል መታረም ያለባቸው ክፍተቶች መኖራቸውን የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አዲሱ ስማቸው አስታውሰዋል:: ቀዳሚው ክፍተት ያሉት የእንስሳት እርባታ ሂደቱን ነው::አሁን ያለው የእንስሳት እርባታ ዘዴ ለልቅ ግጦሽ መስፋፋት ቀዳሚ ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ::ይህም ለመሬት መራቆት እና ለአፈር ክለት እንደ ትልቅ ስጋት አስቀምጠውታል:: በተጨማም በየጊዜው እየተሠሩ ያሉ የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራዎች እንዲፈርሱ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አረጋግጠዋል:: በየጊዜው የሚሠሩ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራዎች በዘላቂነት ለውጥ እንዲያመጡ ከተፈለገ የእንስሳት እርባታ ሂደቱን ማዘመን እንደሚገባ ጠቁመዋል::

የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ በሚከናወንባቸው አካባቢዎችም ኢኮኖሚያዊ ጠቃሚነት ያላቸውን እጽዋቶች በመትከል አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል:: ብሄረሰብ አስተዳደሩ እያንዳንዱን የተፋሰስ ልማቶች ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበር በማሸጋገር የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል:: በዚህ ዓመት ብቻ 23 ተፋሰሶችን ወደ ማኅበራት መሸጋገራቸውን ጠቁመዋል::

እንደ ክልል እየተሠራ ያለው የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይ መሆኑን ለማሳወቅ የተሠራው ሥራ አሁን ላይ መልካም ለውጦች እንደተመዘገቡበት ያስታወቁት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሐብት ልማት  ጥበቃእና አጠቃቀም ዳይሬክተሩ አቶ እስመለዓለም ናቸው:: ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በምን አይነት መንገድ መከናወን አለበት በሚል ጥናት ማካሄዱን አስታውቀዋል:: የጥናቱ አብዛኛው ግኝትም የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ በዘመቻ መልክ መከናወን እንዳለበት የደረገፈ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የጥናቱ 15 በመቶ ግኝት ሥራው መቀጠል እንዳለበት፣ ነገር ግን አሠራሩ መስተካከል እንደሚኖርበት ያመላከተ ነው:: አርሶ አደሩ ከሚኖርበት አካባቢ ብዙ ርቀት ሄዶ መሥራቱ አርሶ አደሩን ለጉልበት ኪሳራ እና ድካም መዳረጉ የተመላከተበት ግኝት ነው፡፡

አሠራሩ መስተካከል አለበት የተባለበት ሌላው ምክንያት የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ ወደተጠቃሚነት  ሊሸጋገር  ይገባል  የሚል ነበር፡፡

አራት በመቶ የሚሆነው የጥናት ውጤት ደግሞ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራው በግል ካልሆነ መቆም እንዳለበት የሚጠይቅ እንደነበር አስታውሰዋል:: ነገር ግን የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ በቅብብሎሽ የሚሠራ እንጂ ሁሉም በየግሉ ማሳ ላይ ማከናወኑ ውጤታማ እንደማይሆን አቶ እስመለዓለም ገልጸዋል:: የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የተፈጥሮ ሚዛንን አስጠብቆ ለመጓዝ፣ የውኃማ አካላትን በደለል ከመሞላት እና ከመንጠፍ በመከላከል አርሶ አደሩን በሚሠሩ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራዎች ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here