ግብዓት እና አቅርቦቱ

0
166

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የግብዓት አቅርቦት (በዋናነት የአፈር ማዳበሪያ) በአግባቡ መጠቀም ምርታማነትን ከሁለት እጥፍ በላይ ከፍ ያደርጋል። ከዚህ ባሻገር ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ደግሞ ከ35 በመቶ በላይ በተለያዩ ምክንያቶች ከማሳ ወደ ጎተራ እስኪገባ ድረስ የሚባክነውን ምርት ያስቀራል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2017/18 የምርት ዘመን ከፍተኛ የምርት ጭማሪ ለማግኘት በማቀድ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

ለዚህ ደግሞ ምርታማነትን የሚያሳድጉ አዳዲስ የግብርና እሳቤዎችን እና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ቁልፍ ተግባር መሆኑን ነው ቢሮው ያመላከተው።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና የውኃ ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሥሩ የሚከታተላቸውን የግብርና፣ የውኃ እና ኢነርጂ፣ የመስኖና ቆላማ  አካባቢ፣ የመሬት ቢሮ እና የደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም በባሕር ዳር ከተማ ከሰሞኑ ገምግሟል። በዚህም የግብርና ግብዓት አቅርቦት አሁናዊ ሁኔታ ሐሳብ ተሰጥቶበታል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቃልኪዳን ሺፈራው ለ2017/18 የምርት ዘመን አዳዲስ እሳቤዎችን እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከፍተኛ የምርት ጭማሪ ለማግኘት እየተሠራ ነው ብለዋል። ለዚህም ግብዓት  ዋነኛው  መሆኑ የተነሳ ሲሆን ለምርት ዘመኑ የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙንም አስታውቀዋል።

በቢሮው የግብርና ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ “ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ በመጓጓዝ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል። የአፈር ማዳበሪያ የጫኑ ስምንት መርከቦችም ጅቡቲ ወደብ እንደደረሱ ዳይሬክተሯ አክለዋል።

የግብዓት አቅርቦትን በተመለከተ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዳስታወቀው በጅቡቲ ወደብ ከደረሰው 313 ሺህ 260 ሜትሪክ ቶን (ስድስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ገደማ) የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 256 ሺህ 398 ነጥብ ሁለት ሜትሪክ ቶን (አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ገደማ) ወደ ኢትዮጵያ ተልኳል፤ ቀሪው ደግሞ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር በማሕበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ ለ2017/18 የምርት ዘመን እስከ አሁን ስድስት የዩሪያ እና የዳፕ ማዳበሪያ የጫኑ መርከቦች ጂቡቲ ወደብ ደርሰው ጭነታቸውን በማራገፍ የአፈር ማዳበሪያውን ወደ ኢትዮጵያ የማጓጓዝ ሥራ ተሠርቷል።

የአፈር ማዳበሪያ የጫኑ 7ኛ እና 8ኛ መርከቦች ደግሞ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ያመላከተው በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ነው። በሚቀጥሉት ቀናት ተጨማሪ 5 መርከቦች ጂቡቲ ወደብ ይደርሳሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም በአጠቃላይ ለምርት ዘመኑ ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ 13 የአፈር ማዳበሪ የጫኑ መርከቦችን ወደቡ እንደሚያስተናግድ በመረጃው ተጠቅሷል።

በተመሳሳይ ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ድፍሻ ያለው  የእርሻ ሜካናይዜሽን ነው። የአርሶ አደሩ ፍላጎትም እየጨመረ መሆኑን  የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል። ምክትል ኃላፊው ቃልኪዳን ሺፈራው እንደተናገሩት በክልሉ ሜካናይዜሽንን ማስፋት ቢታሰብም ውስንነት አጋጥሟል። ችግሩን ለመፍታይ ታዲያ መዋቅር ተሠርቶ ወደ ሥራ መገባቱን አክለዋል።

በተያያዘ መረጃ ምርታማነትን ለማሳደግ ተስፋ ከተጣለባቸው ተግባራት መካከል የበጋ መስኖ ልማት አንዱ ነው። ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በክልሉ በተያዘው ዓመት 254 ሽህ 100 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዷል። ለመስኖ ልማት የግብዓትና የግብርና ቴክኖሎጂ ፍላጎት እያደገ መሆኑን ያመላከተው መረጃው ይህን ታሳቢ በማድረግ ብድር ማመቻቸትን፣ ግብዓትን በወቅቱ እና በሚፈለገው መጠን ማቅረብን ጨምሮ ተያዩያዥ ተግባራት ተከናውነዋል ተብሏል።

በክልሉ በተያዘው ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 254 ሺህ 100 ሄክታር መሬት በማልማት ከዘጠኝ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዷል።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here