ከ18 ወራት በላይ ዕድሜ የወሰደው የአማራ ክልል የሰላም እጦት ዛሬም መፍትሔ ይበጅለት ዘንድ ከግለሰብ እስከ ምክር ቤቶች ድረስ መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል። ይህ የሰላም እጦት በክልሉ ሕዝብ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ እና መስተጋብር፣ በልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።
ያጋጠመውን የሰላም መደፍረስ ለማስተካከል የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት የሕግ ማስከበር ዘመቻ ሲወስድ ቆይቷል፡፡ በሕግ ማስከበሩ የሚገኘው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው ሕዝቡን የሰላም ባለቤት ማድረግን አላማው ያደረገ ተደጋጋሚ ውይይት አካሂዷል፡፡
ታጣቂ ኀይሎችም ሰላማዊ መንገድን ምርጫቸው እንዲያደርጉ እና ችግሮችን በሰላማዊ ንግግር እንዲፈቱ መንግሥት ውይይት እና ድርድር እንዲያደርጉ ጥሪ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በዚህም የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል፡፡ አሁንም ክልሉን ወደነበረበት የሰላም ሁኔታ ሊያሸጋግሩ የሚችሉ የሰላም እና ደኅንነት ሥራዎች መኖራቸው ተገልጿል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከየካቲት 4 እስከ 6/2017 ዓ.ም ባካሄደበት ወቅት የክልሉ ሰላም እጦት እየፈጠረ ያለው ቀውስ ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ማብቂያውም በቅርቡ ሊሆን እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል፡፡
በጉባኤው የጸጥታ ችግሩ የፈጠረው የመንገድ መዘጋት በምርት አቅርቦት እና ስርጭት ላይ ጫና መፍጠሩ ተነስቷል፡፡ ይህም በቀን ሥራ የሚተዳደሩ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ሕይወት እንዲጎሳቆል አድርጓል፡፡ የጸጥታ ችግሩ በሕንጻ ግንባታ እና በሌሎችም የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚሰማሩ ባለሐብቶች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉ በአባላቱ ተነስቷል፡፡
የጸጥታ ችግሩ የሚፈጥራቸው አባባሽ ምክንያቶች በሕዝቡ ሕይወት እና የልማት ሥራዎች ላይ የሚፈጠረው ጫና እየበረታ እንዲሄድ የሚያደርግ በመሆኑ በሁሉም አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን ትኩረት አድርጎ መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
መፍትሔ አጥቶ የቀጠለው ግጭት አማራ ክልል በትምህርት፣ በጤና፣ በምጣኔ ሐብት… ወደ ኋላ እንዲቀር፣ የሕጻናት የነገ ሕይወት እንዲጨልም… ማድረጉም በአባላት ተነስቷል፡፡ “በተለይ የሁሉም ልማቶች መሠረት የሆነው ትምህርት የችግሩ በትር ክፉኛ አርፎበታል፤ የካቲት ላይ ሆነን 40 በመቶ ተማሪዎች ብቻ መመዝገባቸው እጅግ ያሳዝናል! ችግሩ የሚጎዳው ልጆቻችንን ነው፤ ክልሉ በተማረ የሰው ኅይል ያለውን ተወዳዳሪነትም የገደበ ነው“ በማለት አባላት በቁጭት አንስተዋል፡፡
የጸጥታ ችግሩ በ2016 ዓ.ም በከልሉ ውስጥ ከሚገኙ 10 ሺህ 910 ትምህርት ቤቶች ውስጥ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸውን ሲያከናውኑ የከረሙት 7 ሺህ 444 ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡ በዚህም ቁጥራዊ አኃዝ መሠረት 3 ሺህ 466 ትምህርት ቤቶች ዓመቱን ሙሉ ሳይከፈቱ ባጅተዋል ማለት ነው፡፡
ችግሩ በዚህ ዓመትም ቀጥሏል፡፡ በምክር ቤቱ እንደተገለጸው ከሆነ በ2017 ዓ.ም በጥቅል መዝግቦ ለማስተማር በዕቅድ ተይዞ ከነበረው ከሰባት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ውስጥ እስካሁን ከ4 ሚሊዮን 213 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች ትምህርት የሚጀመርበትን ጊዜ እንደናፈቁ ዓመቱን ማጋመሳቸው ተገልጿል፡፡
“በሰላም እጦቱ እየወደመ እና እየጠፋ ያለው ንብረት፣ የሰው ሕይወት፣ ክልላዊ ገጽታ እና የጋራ እሴት ጭምር ነው፡፡ ለክልሉ አንጻራዊ ሰላም የመንግሥት ጥረት የሚደነቅ ነው፤ አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ማስቀጠል እና ክልሉ ይታወቅበት ወደ ነበረበት የሰላም ሁኔታው ለመመለስ ሕዝቡ በከፍተኛ ተነሳሽነት ሊሠራ ይገባል“ በማለትም የምክር ቤት አባላት አንስተዋል፡፡
የሁሉም እምነት የሃይማኖት አባቶች እና አስታራቂ ሽማግሌዎች ወደ ትጥቅ ግጭት የገቡ ኅይሎች ሰላማዊ መንገድን እንዲመርጡ በማድረግ ረገድ ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸውም አባላቱ ጠይቀዋል፡፡
የሕግ፣ ፍትሕ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የክልሉን ሰላም በዘላቂነት በራስ አቅም ለማረጋገጥ አዲስ ኀይል በአዲስ የማሰባሰብ እና ነባሩን ለማብቃት እየተከናወነ ያለውን ሥራ በጥንካሬ አንስተዋል፡፡ የሰላም እጦቱን ለመፍታት እተሠራ ካለው የሕግ ማስከበር ሥራ ጎን ለጎን ሕዝቡ ስለ ሰላም ያለውን አስፈላጊነት ተረድቶ ሚናውን እንዲወጣ የሚያደርጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ለክልሉ አሁናዊ አንጻራዊ ሰላም በአጋዥነት ተጠቁሟል፡፡
ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታም የሕዝቡ ሚዛናዊነት እየተሻሻለ መምጣቱን ቋሚ ኮሚቴው ማረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡ ይህ ወቅት የክልሉ ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት በእጅጉ እየተፈተነ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የሰላም ችግሩን የሰላም በሮችን በማስፋት በውይይት እና ድርድር መፍታት እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው እምነቱ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በ2016 ዓ.ም የክልሉ ሕዝብ በአስከፊ የሰላም እጦት ውስጥ ማለፉን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ክልሉ ወደተሟላ ሰላም አለመመለሱን ገልጸዋል፡፡ ችግሩ በክልሉ ሕዝብ ላይ ቀላል የማይባል ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ማድረሱ ተመላክቷል፡፡ ይህም የክልሉ ሕዝብ ከልማት እንዲነጠል በማድረግ ድህነትን ለማሸነፍ የሚደረገውን ጥረት ማስተጓጎሉን፣ ሕዝቡ ነጻ እና ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖረው፣ ማኅበራዊ መስተጋብሩ እና እንቅስቃሴው ተገትቶ እንዲቆይ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡
የሰላም እጦቱ በክልሉ ሕዝብ የልማት እና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ በመቀልበስ ክልሉ ይታወቅበት ወደ ነበረው የሰላም ሁኔታ ለመመለስ ከክልሉ ሕዝብ እና ከፌዴራል መንግሥት ጋር የተከናወነው ሥራ ውጤት ማምጣቱን አስታውቀዋል፡፡ ይህም የክልሉ መንግሥት ሊደርስበት የሚችለውን የመፍረስ አደጋ ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ የቻለ መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡
አሁን እየተከናወነ ያለውን የሰላም መልሶ ግንባታ አጠናክሮ በማስቀጠል ክልሉን ወደ ነበረበት የሰላም ሁኔታ ለመመለስ አሁንም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህም የክልሉን የጸጥታ ኀይል የማጠናከር እና ልዩ ልዩ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ከመንግሥት አካል በተጨማሪ ሁሉም የክልሉ ሕዝብ ትኩረት አድርጎ ሊሠራ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አማራ ክልልን ጨምሮ እንደ ሀገር እየተፈጠሩ እና ሕዝቡን ረፍት እየነሱ ያሉ የሰላም እና ደኅንነት መናጋት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ኢትዮጵያ ብሄራዊ (ገዥ) ትርክትን እንደ መውጫ መንገድ አድርጋ እየተጋች ነው፡፡ ያለፉ የታሪክ እጥፋቶችን ማረም ደግሞ ለብሔራዊነት ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ እየተሠራበት ነው፡፡ ለዚህም እውን መሆን አሁናዊ የሰላም መደፍረሶች መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል፡፡ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ደግሞ ተልዕኮውን ወስዶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወደ አንድነት ሊያመጡ የሚችሉ ሐሳቦችን እንዲያዋጣም እያደረገ ይገኛል፡፡
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ምድር ሰላምን ለማስፈን እና አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት፣ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት በሀገር አንድነት ውስጥ ለመገንባት እና ለማስጠበቅ፣ ሀገር አቀፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲፈፀሙ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በእጅጉ ወሳኝ መሆኑን ያምናል፡፡ በመሆኑም እየተፈጠሩ ያሉ ሰው ሠራሽ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መተማመንን መሰረት ባደረገ መልኩ እና በአካታችነት መርህ ተመካክሮ ለሀገራዊ ችግሮች ሀገራዊ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋልል፡፡ “ነፍጥ አንግበው በጫካ የሚገኙ ወገኖች እና ‘በሀገር ጉዳይ ላይ ይመለከተናል’ የሚሉ አካላትም በሐሳብ የበላይነት ማሸነፍን አስቀድመው ወደ ሐሳብ መንሸራሸሪያ ሜዳው እንዲመጡ!” በማለት ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም