የአህጉሩ ዋና የመሬት አካል ባትሆንም እንደ አውሮፓውዊት ሀገር ትቆጠራለች። በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ እና በአርክቲክ ውቅያኖስ መካከል እና በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ መካከል ያለች ትንሽ የደሴት ሀገር ናት። ልብን የሚሰርቅ ተፈጥሯዊ ውበት፣ ማራኪ መልካምድራዊ አቀማመጥ ያላት፣ ሰላማዊ፣ ምቹ ሀገር ናት፤ አይስላንድ ።
አይስላንድ በ103 ሺህ ኪሎሜትር ስኩዌር ስፋት ላይ የተቀመጠች ደሴት ስትሆን የአይስላንድ ሪፐብሊክ ትባላለች። ከ380 ሺህ በላይ ሕዝብ ያላት ከአውሮፓ ምእራባዊ ጫፍ ላይ የተቀመጠች ሀገር ስትሆን በምድሪቱም ሰሜናዊው ጫፍ ላይ ያለው የሪካቪክ ከተማ መገኛ ናት።
አይስላንድ በከፍተኛ እሳተጎሞራ የተፈጠረች ሀገር ስትሆን መሬቷም ተራራማነት የሚያጠቃው እና 11 በመቶው ክፍሏም በበረዶ ቋጥኝ የተሸፈነ ነው። አስደናቂ ወይም ተስማሚ የአየር ንብረት ያላት እና ለመቁጠር የሚታክት የሙቅ ውሃ ምንጮች እና ሙቅ ፋውንቴኖች አሏት። በአይስላንድ ተፈጥሮ ያበላሻል ስለሚባል ዛፎችን መቁረጥ እና ከመንገድ ውጭ ማሽከርከር ሕገወጥ ድርጊት ነው።
የመጀመሪያ ሰፋሪዎች ኖርዲኮች እና ሴልቲኮች ናቸው። የሰፈሩትም በ9ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይገመታል። በሀገሪቱ ትውፊት መሰረት የመጀመሪያው ቋሚ ሰፋሪ ኢንጎልፈር ኤመርሰን የተባለ አንድ ኖርዌያዊ የቫይኪንግ ጎሳ አባል የሆነ ግለሰብ ከእነ ቤተሰቡ በቋሚነት ነበር። እርሱ ጎጆውን የቀለሰባት ስፍራ ዛሬ የአይስላንድ መዲና ሪካቪክ የተመሰረተችበት ነው። ከዚያ በፊት ግን ጥቂት ቀደም ብሎ አየርላንዳዊ መነኮሳት ሰፍረውበት እንደነበር ይነገራል።
ከዚያ ወዲያ የተለያዩ ጎሳዎች በተለያየ ጊዜ እየመጡ ሰፈረዋል። እናም ዛሬ በደሴቷ እስከ 15 የሚሆኑ ጎሳዎች አሉ። እነዚህ ጎሳዎችም በጋራ የሚኖር ማህበረሰብ መስርተዋል። በዚህ ስፍራ ነው በዓለም የመጀመሪያው እና አሁን ድረስ የሚሰራበት ጥንታዊው ‘አልተንጊ’ የተባለው ፓርላማ አቋቁመው ይተዳደሩ የነበረው።
የአይስላንድ ደሴት በኖርዌ መንግሥት ከዚያም በመቀጠል በዴንማርክ ከ500 ዓመታት በላይ ቅኝ ግዛት ውስጥ ነበረች። በኋላም በ1936 ዓ.ም ነፃነቷን አረጋግጣ ሉዓላዊት ሀገር ሆነች። ከዚያም ወዲህ አንድ የዓለማችን ሉአላዊነት ሀገር ሆና እስከዛሬ ቀጥላለች።
አይስላንድ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ መስህብ ያላቸው ሕዝቦች መኖሪያ መሆኗ የብዙዎችን ቀልብ ይስባል። አይስላንድ በግሎባል ፒስ ኢንዴክስ መሰረት የዓለማችን ግንባር ቀደም ሰላማዊ ሀገር በማለት ያስቀምጧታል። ግጭት የሌለባት፣ ምንም ወንጀል የሌለባት፣ ሰላሟ አስተማማኝ፣ ዜጎቿ በሰላም ወጥተው የሚገቡባት ደሴት።
ለሰላማዊነቷ ታሪክ በራሱ ምስክር ጥሎላት አልፏል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሮናልድ ሬገን እና የሶቭየቱ አቻቸው ሚካኤል ጎርባቾቭ የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት እንዲያበቃ ያደረገውን ስምምነት የተፈራረሙባት አዳራሽ የሚገኝባት ሀገር ናት። አዳራሹ ለሕዝብ እይታ ውስጡ ክፍት ባይሆንም ውጫዊ ክፍሉ አሁን ድረስ በክብር ይጎበኛል።
በአይስላንድ ምድር ቋሚ ወታደር የላትም። ሕዝቧ ሰላም ወዳድ ነው። የሚያስገርመው በአይስላንድ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የጦር መሳሪያ በሕዝቡ እጅ ቢገኝም እንስሳትን ለማደን ተግባር ብቻ ይጠቀሙበታል። ከ380 ሺህ አጠቃላይ ሕዝቧ መካከል 109ሺ የሚሆኑት ዜጎቿ ጠብመንጃ አላቸው። ይህም ሆኖ እንኳ በአውሮፓ ወንጀል የማይፈፀምባት ሀገር አይስላንድ መሆኗ ይገርማል። ሙስና እና ብልሹ አሰራሮች በደሴቷ ፍፁም ውጉዝ ናቸው።
ድንቅ ተፈጥሮ
አይስላንድ በዓለም እጅግ ልብ አማላይ ተፈጥሯዊ መልካምድር አላት። ከሰፋፊ የበረዶ ቋጥኞች እና ፀጥ ያሉ ሸለቆዎች እስከ ሰላማዊ ፍል ውሃዎች እና አስደማሚ ፏፏቴዎች የተሞላ የአይስላንድ ተፈጥሯዊ ውበት በራሱ መንፈስን የሚያድስ ሰላም እና ፀጥታ ይለግሳሉ። እነዚህ መልካምድሮች ለጎብኝዎቿ ፍፁም የሆነ የደስታ ትዝታን ያሰርፃሉ።
ፀሐይ ከእነዚህ ውብ መልካምድሮች ጋር ተባብራ በውበት ላይ ውበት አነባብራ አይስላንድን አይረሴ ታደርጋታለች። ደሴቲቷ በአንታርክቲክ ቀለበት ውስጥ እንደመገኘቷ የፀሐይ ብርሃን እንደ ወቅቱ የተለያየ ባህሪ ይዞ ይፈራረቅባታል። በሰኔ ወር ብትመጡባት ፀሐይ በሌሊትም ብርሃኗን እየሰጠች ውላ አምሽታ ሰው ምን ይለኛል ብላ ይመስላል ለአፍታ ብቻ ትጠልቃለች፤ ጠልቃ ለመውጣት ያህል። ነገር ግን ሰሟዩ ፈፅሞ አይጨልምም፣ ወዲያው ብቅ ትላለች። በታህሳስ ወር ደግሞ እያንዳንዱ ቀን ለ20 ሰዓታት ጨለማ ነው። ብዙዎች አይስላንድን ለማየት የሚወዱት ወቅት የበጋው ወራት ነው፣ ፀሐይ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ 10 ሠዓት ድረስ የምትቆይበት ወቅት። ይህ የወቅቶች መለዋወጥ የሚፈጥረው ትእይንት በራሱ ጎብኝዎች ሊያዩት የሚወዱት ነው።
ድንቅ ፖርኮች
ከመዲናዋ ሪካቪክ በስተምሥራቅ 30 ኪ.ሜ ራቅ ብሎ ቲንግቨትሊሂር ፓርክ ይገኛል። በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ውስጥ የተመዘገበ ሲሆን ብዙ አስደናቂ ነገሮችን ይዟል። ለአብነት በዓለም ረጅም እድሜ ያስቆጠረው በአይስላንድ ውስጥ በ922 ቅ.ዓ የተመሰረተው አልታንጊ የተባለው፣ አሁን ድረስ የቀጠለው ፖርላማ መነሻ ስፍራ እና የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ አህጉራት የመሬት አካል የሚለያዩበት ስፍራን የያዘ ነው።
ቫትናህይርከድል ፓርክ ደግሞ ሌላው ሲሆን በ12 ሺህ ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ባለው መሬት ላይ የተቀመጠ በአውሮፓ ግዙፉ ብሔራዊ ፓርክ ነው። ፓርኩ በአይስላንድ ትልቁን ተራራ፣ ትልቁን የበረዶ ቋጥኝ ፣ እና በአውሮፓ ግዙፉን ፏፏቴ የያዘ ሁለት ፓርኮችን በአንድ ላይ አካቶ የተቋቋመ ነው። እና ሌሎችም ፓርኮች ያሉባት ምድር ናት።
የማንበብ ፍቅር
ዘጠና ዘጠኝ በመቶው የአይስላንድ ሕዝብ የተማረ ሲሆን አብዛኛውም አንባቢ ነው። በርካታ የመፃህፍት መደብሮች በሀገሪቱ ይገኛሉ። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ጥናት የሚያደርገው አይስላንዲክ ሊትሬቸር ሴንተር የተሰኘው ተቋም ባደረገው የቅርብ ጥናት ባስነበበው መረጃ መሰረት የደሴቲቱ አብዛኛው ሕዝብ በማንበብ ፍቅር የተጠቃ መሁኑን ያስረዳል። እያንዳንዱ አይስላንዳዊ በወር በአማካይ ከሁለት በላይ መፃህፍት ያነባል። በምድር ላይ አብዛኛው አንባቢ የሚገኘው በአይስላንድ ነው። አስደማሚው መልካምድሯ፣ ከአንድ ሺህ በላይ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ታሪኳ እና ከሌላ አካባቢ ተነጥሎ ለዘመናት የቆየ ባህሏ ተዳምረው መላ ሀገሪቱ በአፈታሪኮች፣ በተረቶች እና ተረት ነጋሪዎች የተሞላች መሆኗ አያስደንቅም።
በየቀኑ ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆነው የአይስላንድ ሕዝብ በየቀኑ በቋሚነት መፅሀፍ ያነብባል። ማንበብ ብቻ አይደለም የአይስላንድ ሕዝብ ብዙ ፀሀፊዎችን ያፈራ ነው። በዓለም እውቅ ፀሀፊዎች አፍርታለች። ብዙ መፅሃፍ ያሳተሙ፣ ብዙ ያነበቡ እና ብዙ መፅሃፍ የገዙ ብዙዎች ናቸው። በሀገሪቱ በርካታ የመፅሃፍ መደብሮች፣ ቤተመፃህፍት ይገኛሉ። መዲናዋ ሪካቪክ በራሷ በዩኔስኮ የዓለማችን የስነፅሁፍ ከተማ የሚል ክብርን በ2003 ዓ.ም ተጎናፅፋለች።
አይስላንዳውያን ክቮልድቫካ የተሰኘ ጠንካራ ባህል አላቸው፣ ይህ በየቀኑ ምሽት የሚሰባሰቡበት እና ስላነበቡት መፅሀፍ የሚወያዩበት በመላ ሀገሪቱ የሚተገበር ትውፊት ነው። በዚህ አጋጣሚ እርስ በርስ ታሪክ ይጋራሉ፤ ያነበንባሉ ወይም ይጠያየቃሉ። አይስላንዳውያን መፅሀፍ የክብር ስጦታ አድርገው ይቆጥራሉ። ስለዚህች ውብ እና አስደማሚ ደሴት ብዙ ማለት ይቻላል። እኛ ግን በዚሁ አበቃን።
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም