የዓየር ለውጥ ድቦችን ሲንጥ

0
113

የዓየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው የሙቀት መጨመር ግግር በረዶ  እየቀለጠ የሚበሉት በማጣት እየተፈተኑ ያሉት የዋልታ ድቦች ከመራባት እየተገቱ ቁጥራቸው መቀነሱን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡

በካናዳ የቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች በምዕራብ ሁድሶን ሰርጥ ባደረጉት ጥናት የድቦች ቁጥር ማሽቆልቆል ከበረዶ መቅለጥ ጋር እንደሚገናኝ ነው የደረሱበት፡፡ በዋልታ ቀጣና የሚገኙት ድቦቹ ለኅይል ምንጭነት የሚያውሉት በቂ ምግብ አድነው ማግኘት አለመቻላቸው ከመራባት ትቷቸዋል፡፡

በተመራማሪዎቹ በተሰራው  “ባዮ ኢነርጀቲክ” በተሰኘ ናሙና ጥናት ድቦቹ አድነው ከሚበሉት ለኃይል፣ ለማደግ፣ ለመራባት የሚያስፈልጋቸው  ተዘርዝሮ መጠኑን መገምገም ችለዋል፡፡

ጥናትና ምርምሩ በተካሄደበት  ቀጣና ከ1979 እስከ 2021 እ.አ.አ የተሰበሰበን መረጃ አነፃፅረው ቀምረዋል- ተመራማሪዎቹ፡፡ በውጤቱም የድቦች ቁጥር 50 በመቶ ቀንሶ ነው የተገኘው፤ ከዚሁ ጋር በተመሳሳይ የአካል ግዝፈታቸው እና ክብደታቸውም ሴት ድቦች በ39 ኪሎ ግራም አንድ ዓመት የሆናቸው ግልገሎቻቸው ደግሞ በ26 ኪሎ ግራም መቀነሳቸው ተረጋግጧል፡፡

በተመራማሪዎቹ የተሰራው ናሙና ጥናት ውጤት በክትትል በቦታው ከተሰበሰበው መረጃ ውጤት ጋር የተቀራረበ ሆኖ ተገኝቷል፤ ከሁነቱም የበረዶ መቅለጥ የሚቀጥል ከሆነ የዋልታ ድቦች የሚበሉት ለመፈለግ እየባዘኑ ረዢም ጊዜ እንደሚያሳልፉ እና ለኃይል እጥረት መዳረጋቸው አይቀሬ መሆኑን ነው የተመላከተው ፡፡ ይህም ለዝርያው ቁጥር ማሽቆልቆል በዋነኛ ምክንያትነት ተጠቃሽ መሆኑ ነው የተሰመረበት፡፡

በጥናትና ምርምሩ ከተሣተፉት በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ በስነ ህይወት ሳይንስ የትምህርት ክፍል ተባባሪ ኘሮፌሰር ፒተር ሞልናር ከጥናቱ የተገኘው ውጤት የበረዶ መቅለጥ እና መመናመን ከድቦች ቁጥር መቀነስ ጋር እንደሚዛመድ ከማስገንዘብ የዘለለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የግግር በረዶ መቅለጥ ድቦች በመብላት የሚያሳልፉትን ጊዜ እንደሚያሳጥር እና ኃይል ለማግኘት እንደሚቸገሩ ነው ያመላከቱት፡፡

ከሁሉም በላይ እናት ድብ እና ግልግሎች ከሁሉም የበለጠ ተጠቂ እንደሚሆኑ ነው ያሰመሩበት፡፡ ሲጠቃለል እናት ድቧ በቂ ምግብ አግኝታ ግልገሎችዋን ማጥባት፣ ማጥገብ ተስኗት ማሳደግ እና ዝርያዋን ማስቀጠል እንደሚሳናትም ነው በማደማደሚያነት ለንባብ የበቃው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here