“እኔ ሴት ነኝ፤ ጦርነት አልወድም! ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ!” ይህ ንግግር ባርነትን አጥብቀው የሚጠየፉት የእቴጌ ጣይቱ ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ታሪክ የሆነው ዓድዋ ሲነሳ ሁሌም ስማቸው አብሮ ይጠራል፡፡
“ብርሐን ዘ ኢትዮጵያ” በሚል ቅፅል ሥም የሚታወቁት እቴጌ ጣይቱ ነሐሴ 12 / 1832 ዓ.ም በድሮው አጠራር በጌምድር አውራጃ ደብረ ታቦር ከተማ ተወለዱ። በጊዜው ይሰጡ የነበሩትን የኦርቶዶክስ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በታላላቅ አድባራት በመዘዋወር ያጠናቀቁ ስለመሆናቸው ታሪክ አዋቂዎች ይመሰክራሉ።
ከሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ጋር ጋብቻቸውን በሚያዝያ 25 ቀን 1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በሥርዓት ቁርባን ፈጽመዋል። ከስድስት ዓመታት በኋላም አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የሚለውን የማዕረግ ሥም በተቀዳጁ በማግሥቱ ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ.ም ወይዘሮ ጣይቱ ብጡል እቴጌ ተብለው ተሰይመዋል።
እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው የገነነው እና በሀገር አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት የጀመሩት ኢትዮጵያ ሚያዝያ 25ቀን 1981ዓ.ም የውጫሌን ውል ከጣሊያን ጋር በተፈራረመችበት ጊዜ ነበር፡፡ ውሉ ውስጥ “ኢትዮጵያ የውጭ ግንኝነቷን በጣሊያን በኩል ትፈጽማለች” የሚለው ጦር እንደሚያማዝዝ ከታወቀ በኋላ ማለት ነው። ይህ ለዓድዋ ጦርነት መነሳት ዋነኛ መንስዔ የሆነው ጉዳይ ሊታወቅ የቻለው እቴጌ ጣይቱ የውጫሌ ውል አንቀፅ 17 ላይ አለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ የተባሉት የታሪክ ምሁር አና የአፄ ምኒልክ አማካሪ ነገሩን ከደረሱበት በኋላ ነው፡፡
አለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ የውሉን ሰነድ በመመርመር የውሉ 17ኛ አንቀፅ የያዘውን የትርጉም መዛባት እንዳለበት በማሳወቅ ጉዳዩ ኢትዮጵያን እንደሚጎዳ አስረድተዋል፡፡ ይህን ጉዳይ እቴጌ ጣይቱ በቀላሉ ሊያልፉት አልቻሉም በጥንቃቄ መረመሩት ፤ አጤኑትም።
ዳንኤል ወ/ኪዳን የሚባል ጸሐፍት ማስረጃ እንደሚያሳየው በወቅቱ አጼ ሚኒሊክ የውሉን ሁኔታ በደንብ አልተረዱትም ነበር፡፡ ሁኔታውን ያስረዱት አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ ነበሩ፡፡ ይሁንና ጉዳዩን ሳይመረምሩ አፄ ምኒልክ አለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ እንዲታሰሩ አደረጉ፡፡ ሆኖም እቴጌ ጣይቱ እኒህ ሰው ትክክለኛ የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆናቸውን ለአፄ ምኒልክ በማስረዳት ከወህኒ አስወጥተዋቸዋል፡፡ በዚህ በኩል ሲታይ እቴጌ ጣይቱ የምኒልክ የቅርብ አማካሪ በመሆን በፖለቲካ ተግባሮች ምን ያህል አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ ማሳያ ነው፡፡
እቴጌ ጣይቱ የውጫሌው ውል ስለከነከናቸው “የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ፣ ሥር የሚነቅል፣ መሠረት የሚያፈርስ ጉዳዩን ሁሉ እኔ ሳላየው እንዳያልፍ ይፍቀዱልኝ?” ብለው ለንጉሡ ባመለከቱት መሠረት “አንቺ ሳታይው፤ ሳትመረምሪው አያልፍም” በማለት ተፈቅዶላቸዋል። ይህ ሁኔታ የሚያመለክተው እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸው ቦታ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ነው። ውሉንም ለማስተካከል አፄ ምኒልክ ያደረጉት የዲፕሎማሲ ጥረት ውጤታማ ሊሆን ባለመቻሉ ሚንሥትሮች የጦር አለቆች እና መኳንንቶች የሚገኙበት ጉባዔ ከተጠራ በኋላ ጦርነቱ የማይቀር ሆኗል፡፡
በሀገራቸው ሉዓለዊነት ድርድር የማያውቁት እቴጌ ጣይቱ ወደ ዓደዋ ሲዘምቱ ከሦስት ሺህ እስከ አምስት ሺህ እግረኛ እና ፈረሰኛ የጦር ሠራዊት እየመሩ መዋጋታቸውን ኢትዮጵያን ፓትሪዮትስ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያትታል፡፡
“ሴት ቢያውቅ በወንድ ያልቅ” የሚለው አባባል ልክ እንዳልሆነ ያሳዩ አስታዋይ እና ብልህ ሴትም ነበሩ፡፡ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ጠላት የሚጠቀመውን የውኃ ጉድጓድ በወታደሮቻቸው በማስከበብ ጠላት በጥም እንዲቃጠል አድርገዋል፡፡ ታዲያ ጠላት በውኃ ጥም ሲሰቃይ እና እንስሳቱ በውሃ ጥም ሲያልቁ አማራጭ ስላልነበረው እጁን ለወገን ጦር አሳልፎ ለመስጠት ተገዷል፡፡
እቴጌ ጣይቱ በወቅቱ ባልተለመደ መልኩ እንደ ወንድ ወታደሮቻቸውን በቀኝ እና በግራ አሰልፈው ዐይነ ርግባቸውን ገልጠው በእግራቸው እየተዘዋወሩ “ድሉ የእኛ ነው በለው!” እያሉ ሲያበረታቷቸው እንደ ነበር ብሩክ መኮንን ተክለየስ በፃፈው እቴጌ ጣይቱ ብርሐን ዘኢትዮጵያ በሚለው መፅሐፍ ላይ አስፍረዋል፡፡
እቴጌ ጣይቱ “የወደፊቱ የምኒሊክ መንግሥት መናገሻ ከተማ የት መሆን አለበት?” የሚለውን ውዝግብ መፍትሔ መስጠት ችለዋል፡፡ አዲስ አበባንም የንጉሡ መነጋሻ (የኢትዮጵያ ዋና ከተማ) ሆና እንድትቆረቆር ከማድረግ ባለፈ የምኒሊክ ቤተመንግሥታዊ ተቋማት እንዲመሠረት አድርገዋል፡፡ እንዲሁም በሀገር መንግሥት ግንባታም ሰፊ ድርሻ ነበራቸው፡፡ በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ የሚገኘው የከተማዋ የመጀመሪያው ሆቴል “ጣይቱ ሆቴል” ከአብርክቶቻቸው መካከል አንዱ ነው።
እቴጌዋ ነገሮችን እንደመጡ እና እንደወረዱ የማይቀበሉ፣ ተጠራጣሪ እና በብልጠት የሚመረምሩ፣ ጉዳት እና ጠቀሜታቸውን የሚያመዛዝኑ ብልህ ሴት ነበሩ፡፡ በዚህም በአፄ ሚኒልክ የዙፍን ችሎት ላይ በመገኘት መንግሥታዊ ክርክሮችን እና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን በመመርመር አስተያየታቸውን ይለግሷቸው እንደነበርም በዚሁ (እቴጌ ጣይቱ ብርሐን – ዘኢትዮጵያ) ከሚለው መፅሀፍ ላይ መረዳት ችለናል፡፡
ከዓድዋ ድል በኋላ የውጭ ሀገራት ጋዜጦች ጣይቱን ከግብጿ ንግሥት ኪሊዮፓትራ እና በ18ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረችው የሩሲያዋ ንግሥት ከታላቋ ካትሪን ጋር እያመሳሰሉ ስለጀግንነታቸው በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዝኛ ሰፊ የዘገባ ሽፋን ሰጥተዋል፡፡
በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት ለተፈፀሙ ዋና ዋና ሥራዎች አስተዋጽኦ ያበረከቱ እቴጌ ጣይቱ የጦርነት ስልቶችን በመንደፍ እና በመቀየስ የተካኑ እንደ ነበርም ይነገርላቸዋል፡፡ ነገር በማብረድ የሚታወቁት ጣይቱ በተለይም በሁለት የጦር አበጋዞች መሃል የሚፈጠር አለመግባባትን አግባብቶ በመፍታት በኩል ተወዳዳሪ አልነበራቸውም።
ጣይቱ ብጡል እውነተኛ የኢትዮጵያ መሪ ነበሩ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ያከናወኗቸው ተግባራት ኢትዮጵያን ከአውሮፓ ቅኝ ግዛት ከማዳን አልፈው ለአፍሪካዊያን ነጻነት በር ከፍቷል፡፡ ከሕዝቡ ጋር በነበራቸው ግንኙነት በተለይም ያሳዩት በነበረው ርህራሄ እና ልግስና በጣም የተወደዱና የተመሰገኑ ነበሩ።
የአፄ ምኒሊክ የጤንነት ሁኔታ በተዳከመበት ወቅት ሀገሪቱን የማስተዳደር ድርሻን በመውሰድ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ ሆኖም ባደረጉት ሹም ሽር ቅሬታ የተፈጠረባቸው አካላት ተባብረው ከሥልጣን ገለል ሊያደረጓቸው ችለዋል፡፡ እኒያ ለሀገር ክብር ዋና ተቆርቋሪ የነበሩት እቴጌ ጣይቱ በ1910 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም