እስከአሁን በጨረር ይሰጥ የነበረው የካንሰር ህክምና የነበሩበትን የጐንዮሽ ጉዳቶች በሚያሻሽል ውጤታማ የኬሚካል ውህድ (cyanine- carborane salt) መተካት መቻሉን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::
በአሜሪካ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ለንባብ እንዳበቃው ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጣ የተመራማሪዎች ቡድን ባደረገው ጥልቅ ምርምር በጨረር ህብረ ህዋሳትን ዘልቆ ከታለመው ውጪ ጉዳት ከሚያደርስ እና ካንሰርን ሊያሰራጭ ከሚችለው የተለየ ስልት ዘይዷል::
አዲስ የተገኘው “ሳያንካርቦሬን ሳልት” የተሰኘው ውህድ ቀደም ብሎ ሲሰጥ የነበረው ህክምና የታዩበትን ችግሮች እንደሚያስቀር አረጋግጠዋል- የተመራማዎቹ ቡድኑ መሪ ኘሮፌሰር ሶፊያሉነት::
በጨረር ይሰጥ የነበረው የካንሰር ህክምና ለረጅም ጊዜ ከብርሃን መገለል ወይም አለመጋለጥን ግድ የሚል፣ ከታለመው አካል ውጪ ጉዳት ማድረስ እንዲሁም ወደ ጥልቅ አካል ክፍል አለመድረስ የመሳሰሉ እጥረቶች ነበሩበት – ተመራማሪዎች እንዳብራሩት::
ከዚህ በተጨማሪ የምግብ እና መድሃኒት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን (FDA)የጨረር ህክምና በታካሚው አካል ረጅም ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል አረጋግጧል:: በዚሁ ምክንያትም ታካሚዎች ከጨረር ህክምና በኋላ ለጨረር ብርሃን ሳይጋለጡ ከሁለት እስከ ሦስት ወራት ማሳለፍ እንደሚጠበቅባቸው ማሳሰቢያ ይሰጣቸው እንደነበረ ነው በድረ ገጹ የተጠቆመው::
በተመራማሪዎች ቡድኑ የተገኘው አዲሱ “ሲያን ካርቦሬን ሳልት” የተሰኘው የካንሰር ህክምና በሚፈለገው የአካል ክፍል ላይ ብቻ የሚያነጣጥር፣ የሚለቀቀው ኃይልም ዒላማውን ከመታ በኋላ ፈጥኖ የሚጠፋ መሆኑ ተሰምሮበታል::
አዲሱ የካንሰር ህክምና ጤናማ ህዋሳትን የማይጐዳ፣ የተፈለገውን ውጤት ካስገኘ በኋላ በፍጥነት ከአካል ውስጥ የሚወጣ ብቻ ሳይሆን መቆየት ባለበት አካል ውስጥ ግን መቆየት የሚችል መሆኑ ከነባሩ የተለየ፣ ተመራጭነቱን የሚያጐላ ምክንያት መሆኑን ነው ያበሰሩት – ተመራማሪዎቹ::
በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ ትምህርት ኘሮፌሰር እና ተባባሪ ዋና ተመራማሪዋ ቪንስንት ላቫሎ አዲሱ “ሳያን ካርቦሬን ሳልት” የተሰኘው ውህድ በታለመበት አካል ውስጥ የሚቆየው መጥፋት ያለባቸው የካንሰር አምጪ ህዋሳት እስኪወገዱ ድረስ መሆኑን ነው ያስታወቁት::፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም