በቻይና ዚጂንግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተሰራው ባለ አራት እግሩ ሮቦት በሰከንድ አስር ሜትር በመሮጥ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገቡን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል::
ተመራማሪዎቹ በየካቲት ወር መጀመሪያ ለምረቃ ያበቁት “ብላክ ፓንተር” የተሰኘው ባለ አራት እግር ሮቦት በሰከንድ 10 ሜትር መፈትለክ የሚችል ነው:: ይኸው ፍጥነቱም በአጭር ርቀት ኘሮፌሽናል አትሌቶች ካስመዘገቡት ሰዓት ጋር የሚስተካከል መሆኑ ነው የተጠቆመው::
“ብላክ ፓንተር” ሮቦት በዚጂያንግ ዩኒቨርሲቲ በሃንግዙ ኢንተርናሽናል የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ማእከል ነው የተሰራው:: ሮቦቱ 63 ኪሎ ግራም ክብደት እና 63 ሴንቲ ሜትር ቁመትም አለው:: ሩጫው በጣም ፈጣን መሆኑን እና ከርቀት በዓይን ለማየት ብዥታ እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት- ተመራማሪዎቹ::
የሃንግዙ ዓለም አቀፍ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ማእከል ተመራማሪው ጂን ዮንግቢን “ብላክ ፓንተር” ሮቦት አሁን ያስመዘገበውን ፍጥነት ማሳደግ እንደሚቻልም ነው የተናገሩት:: ሮቦቱ አሁን ለደረሰበት እመርታ የተስተካከለ ሜዳ እና የተረጋጋ ወይም ቋሚ የኃይል አቅርቦት እንደሚሻም ነው የጠቆሙት:: በመሆኑም በተስተካከለ የቤት ውስጥ መሮጫ (ትሬድሚል)ላይ ብቻ መሞከሩን አስርድተዋል:: በቀጣይ ፍጥነቱን በሰከንድ አስራ አምስት ሜትር መሮጥ እንዲችል ለማሳደግ አቅደው በመስራት ላይ መሆናቸውን ነው ያስታወቁት- ተመራማሪዎቹ:: እቅዳቸው ለስኬት የሚበቃ ከሆነ የ“ብላክ ፓንተር” አተገባበርን በበርካታ አስፈላጊ በሆኑ መስኮች ለማስፋት አዲስ ምእራፍ እንደሚከፍትም አስገንዝበዋል::፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም