በታይላንድ ከተወለደ ሦስት ዓመት ያስቆጠረው ጐሽ ከሸኮናው እስከ ጫንቃው አንድ ሜትር ከሰማኒያ ሴንትሜትር በላይ በተለካ ቁመቱ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ለክብረወሰን መብቃቱን ኤንዲቲቪ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::
ከሸኮናው እስከ ጫንቃው ቁመቱ ለሁለት ሜትር ጥቂት ሴንትር ሜትር የቀረው የተለካው በታይላንድ ገጠር ውስጥ ለእርሻ ሥራ የሚያገለግለው ጐሽ በቁመቱ በድንቃድነቅ መዝገብ ለመስፈር በቅቷል::
በታይላንድ ናኮን ራቻሲማ ውስጥ ኒላኔ መንደር በእርሻ በሚተዳደሩ ሲካርት ቦንቻሮን የተሰኙ አሳዳሪው ቤት ሚያዚያ 1/2021 እ.አ.አ መወለዱን ለክብወረሰን መዝጋቢ ባለሙያዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል- ባለንብረቱ እና ጐረቤቶች::
ግዙፉ እንስሳ በተፈጥሮው የማይተናኮል ወይም አስቸጋሪ አለመሆኑን፣ በቀጣናው ባለ ኩሬ ውስጥ መንቦጫረቅ የሚያዘወትር፣ ከሚንከባከቡት ሰዎች ጋር መቀራረብ እና መተሻሸት የሚሻ መሆኑን ነው የጠቆሙት- አሳዳሪው::
ጐሹ ከተወለደ ጀምሮ ቁመቱ ከፍ ያለ በመሆኑ “ኪንግ ኮንግ” በተሰኘው ፊልም ላይ ባለው ግዙፉ የጐሬላ ስም “ኪንግ ኮንግ” ተብሎ መጠራቱን አስረድተዋል-አሳዳሪ ባለቤቱ::
ግዙፉ ጐሽ በሚኖርበት የእርሻ ቦታ የሚሰሩት ቼርፓት ዉቲ የተባሉት ግለሰብ ለክብረወሰን መዘጋቢዎች ከሌሎች በአካባቢው ከሚገኙ ጐሾች ከውልደት ቀኑ ጀምሮ በቁመት ዘለግ ያለ ብልጫ እንደ ነበረው ነው የተናገሩት:: ከተወለደ ገና ሦስት ዓመቱ በመሆኑም ከዚህ የበለጠ ቁመቱ እንደሚጨምር እምነታቸው ስለመሆኑ መናገራቸውን ድረ ገጹ አስነብቧል::
በአካሉ ግዝፈት ሲያዩት አስፈሪ ቢመስልም ከሰዎች ጋር መቀራረብን የሚሻ፣ ለማዳ፣ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር ታዛዥ መሆኑንም ነው ያሰመሩበት – ቼርፓት ዉቲ::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም