ጀጎል

0
153

የሐረር ጀጎል ግንብ የተገነባው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከግራኝ አህመድ ጦርነት በኋላ በአሚር ኑር አማካኝነት ነው። ግንቡ የተገነባበት ዋናው ምክንያት የሐረር ከተማ ከወራሪዎች ለመከላከል ሲባል ነው።

አጠቃላይ ርዝመቱ ሶስት ሺህ 342 ሜትር፣ ከፍታው አራት ነጥብ አምስት ሜትር፣ የግንቡ ውፍረት ደግሞ ከ40 እስከ 50 ኢንች እንዲሁም ያረፈበት የቦታ ስፋት 48 ሄክታር ነው። በግንቡ ውስጥ የሚገኙ መስጅዶች ብዛት ከ90 በላይ ነው። በግንብ ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ ጥንታዊ እና ባህላዊ ቤቶችም ይገኛሉ።

በኪነ ህንፃ ውበት የተገነቡ አምስት ጥንታዊ በሮች እና ሁለት ከ1880 ዓ.ም በኋላ የተከፈቱ በአጠቃላይ ሰባት በሮች አሉ። የበሮችም ስያሜ ሁለት አይነት ሲሆን በአካባቢው ቋንቋ አጠራር እና በሰፊው የሚታወቅበት ስያሜ ናቸው።

ስያሜያቸውም የጥንቱ አምስት በሮች በአካባቢው ቋንቋ አጠራር በሰፊው የሚታወቁበት ስያሜ አስዲን በር፣ ሸዋ በር፣ በድሮ በር፣ ኩዳ በር፣ ሱክታት በር፣ ኤደር በር፣ አሱሚ በር እና ሰንጋ በር ናቸው። ከ1880 ዓ.ም በኋላ የተከፈቱት በሮች ደግሞ በርበር በር እና በሪ በር በመባል ይታወቃሉ።

በጥንት ጊዜ የአካባቢው ነዋሪዎች ለንግድ ወደ ጀጎል የሚገቡት በሙሉ የያዙትን የጦር መሣሪያ በየበሩ ላሉ ጥበቃ ሰራተኞች ሰጥተው እንደነበር ህብረ ኢትዮጵያ መፅሐፍ ላይ የሰፈረው ጽሁፍ ያስረዳል። ጀምበር ስትጠልቅ ሁሉም እንዲወጡ ተደርጎ በሮቹ ይቆለፋሉ። ቁልፎቹም ለአሚሩ ይሰጡ ነበር።

 

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የካቲት 17  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here