ተናፋቂዉ የነገዉ ቀን

0
128

ክልሉ ባጋጠመው የሰላም መደፍረስ 2016 የትምህርት ዓመትን ከትምህርት ውጪ ሆኖ የከረመው ተማሪ አዲሱ ተስፋ ዘንድሮንም  በተመሳሳይ ሁኔታ ላለማሳለፍ   ከመኖሪያ ቀየው ለቋል:: አዲሱ ተወልዶ ያደገው በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ሊበን ከተማ ነው:: በ2015 ዓ.ም መጨረሻ እንደ ክልል ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ በ2016 ዓ.ም እሱን ጨምሮ ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ርቀው እንዲያሳልፉ  አድርጓል:: ዓመቱን ሙሉ “ከዛሬ ነገ ትምህርት ተጀምሮ ወደ ትምህርት እመለሳለሁ” የሚል ተስፋ ቢኖረውም  ዓመቱን ሙሉ ከትምህርት ውጪ ሆኖ ከርሟል::

የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዓመት ሲጀመር ለሁለተኛ ዓመት ከትምህርት ውጪ ሆኖ ላለመክረም ሲል መኖሪያ ቀየውን፣ ወላጆቹን እና ዘመድ አዝማዶቹን ርቆ ጉዞውን ወደ ባሕር ዳር አደረገ:: የትምህርት ቤት መዳረሻውም ቁልቋል ሜዳ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆነ:: በአሁኑ ወቅት የሥምንተኛ ክፍል ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል:: በክልላዊ ፈተና ውጤትም ከቀዳሚዎቹ አንዱ ለመሆን ተግቶ እየሠራ መሆኑ አስታውቋል::

ተማሪ  አዲሡ  ግጭቱ ያስከተለበትን ውጣ ውረድ  ሲያስረዳ፤ “ቤተሰቦቸ ገቢያቸው ዝቅተኛ ነው:: ትምህርቴን ወደ ባሕር ዳር መጥቼ ለመቀጠል ሳስብ ለቤት ኪራይ፣ ለትምህርት ቁሳቁስ ማሟያ፣ የዕለት ምግብ ወጪን ለመሸፈን አሳስቦኝ ነበር፤ ነገር ግን ቤተሰቦቼ እኔ ለትምህርት ያለኝን ፍላጎት በመረዳታቸው ሳይኖራቸው ለማስተማር ወስነው ልከውኛል፣ ትምህርት ቤቱ አንድ ሐሳብ አቅሎልኛል፣ የጀመረው የትምህርት ቤት ምገባ የዕለት ምግብ ለማሟላት ብዙም ሐሳብ ውስጥ ሳልገባ ትምህርቴ ላይ ብቻ እንዳተኩር አስችሎኛል፤ በአጠቃላይ ግጭቱ ባይኖር ኖሮ ሁሉም ባለበት ተረጋግቶ ትምህርቱን ማስቀጠል ይችል ነበር” በማለት ነው::

ትምህርት የትውልድ ቅብብሎሽን የማስቀጠል እና ያለማስቀጠል ጉዳይ ሆኖ ዛሬም መነጋገሪያነቱ ቀጥሏል:: በተለይ ከ2013 ዓ.ም ወዲህ መልካቸውን በመቀያየር በየጊዜ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች ከተፈጥሯዊ ክተቶች ጋር ተዳምረው የትውልድ ክፍተት እንዲፈጠር እያደረጉ ነው::

ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት እንዲርቁ የሆነበት ጊዜ ነው:: ከትምህርት ውጪ የሆኑ ተማሪዎች ትናንት ላይ ሆነው የዛሬ ዓመትን የተሻለ መሆን እና ወደ ትምህርት መመለስን እየተጠባበቁ አሁንም ይገኛሉ:: መምህራንም ከግጭት አዙሪት የመውጫ ጊዜን በጉጉት ሲጠባበቁ ከሚወዱት ሙያ መገናኘትን ናፍቀው ነው:: ወላጆችም ልጆቻቸው ከአጠገባቸው ርቀው እንዳይሰደዱባቸው፣ ወደ ሕገ ወጥ መንገድ እንዳይገቡባቸው፣ ለጉልበት ብዝበዛ እንዳይዳረጉባቸው የትምህርትን መጀመርን  በጉጉት ይጠብቁታል::

ይሁን እንጂ የትምህርት መጀመር ጉዳይ አሁንም ከጥያቄ ምልክት ውስጥ አልወጣም:: የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ስለአሳሳቢነቱ ተነጋግሯል:: በክልሉ ውስጥ 10 ሺህ 910 ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ:: የጸጥታ ችግሩ ከፍተኛ ሆኖ በከረመበት 2016 ዓ.ም ውስጥ በመደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ያለፉት 7 ሺህ 444 ትምህርት ቤቶች እንደነበሩ ርእሰ መስተዳደሩ በጉባኤው ወቅት አስታውቀዋል:: 3 ሺህ 466 ትምህርት ቤቶች ግን ተማሪን ከመምህር ሳያገናኙ የከረሙ ናቸው::

ክልሉ በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳ በአንጻራዊ የሰላም ሁኔታ ውስጥ ቢገኝም የትምህርት ጉዳይ ግን አሁንም በችግር ውስጥ እንደሚገኝ ተመላክቷል:: የክልሉ ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ.ም ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር ዕቅድ ይዞ በዓመቱ መጀመሪያ ተነስቷል:: የአንደኛው ወሰነ ትምህርት በተጠናቀቀበት ወቅት ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተመዝግበዋል:: በትምህርት ላይ የሚገኙት ደግሞ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን እንደማይበልጡ በክልሉ ትምህርት ቢሮ ተገልጿል:: ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ግን አሁንም ከትምህርት ቤቶች ጋር ተራርቀው ይገኛሉ::

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከክልሉ የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ ከሴቶች፣ ሕፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመሆን ግጭቱ ያስከተለውን ማኅበራዊ ምስቅልቅል በተመለከተ በቅርቡ ምክክር ማካሄዳቸው ይታወሳል:: በዚህ ወቅት እንደተገለጸው 4 ሺህ 917 ትምህርት ቤቶች ተማሪ ከመምህራን ጋር አልተገናኙባቸውም:: ከእነዚህ ውስጥ 3 ሺህ 805 ትምህርት ቤቶች እስከ ወርሀ ጥር 2017 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ  ምዝገባ አልተጀመረባቸውም::

ከ100 ሺህ በላይ መምህራን በአዕምሮ ጤና መቃወስ እና በሥነ ልቦና ጫና ውስጥ እንደሚገኙ የተናገሩት በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ባለሙያ የሆኑት አቶ ለዓለም መኩሪያው ናቸው:: መምህራን በገጠማቸው ከፍተኛ የሥነ አዕምሮ እና የሥነ ልቦና ችግር ከማንበብ፣ ከመጻፍ እና ከመመራመር ተግባራቸው እንዲነጠሉ ማድረጉን የግጭቱ ተጽእኖ ውጤት ማሳያ አድርገው አንስተዋል:: መምህራን እየተማሩ ለሚገኙ ተማሪዎች እውቀታቸውን ለማስተላለፍ የአዕምሮ ዝግጁነት እንደሚጎድላቸውም በጥናት መለየቱ ተጠቁሟል::

ባለሙያው የግጭቱ አሉታዊ ተጽእኖ ሌላው ማሳያ አድርገው የጠቆሙት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቀውሱን ሽሽት አካባቢያቸውን ለቀው እየተሰደዱ መሆናቸውን እና ላለ እድሜ ጋብቻ መዳረጋቸውን ነው:: ጭንቀት፣ ሀዘን፣ ድባቴ፣ የትኩረት ማነስ እና የእንቅልፍ ማጣት ችግሮች በተማሪዎች እና በመምህራን ላይ የሚታዩ የአዕምሮ እና የጤና መታወክ እክሎች ናቸው ተብሏል:: ይህም የትምህርት ጥራትን ዕውን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ዋና ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል::

የክልሉ ሰላም መሆን፣ የሕዝብን ደጀንነት፣ የተፋላሚ ወገኖች ከመንግሥት ጋር መደራደር የተማሪዎች፣ የመምህራን፣ የወላጆች እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት የዘወትር ፍላጎት ነው::

የክልሉ ትምህርት ቢሮ አሁንም እስከ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ የተማሪ ምዝገባ መርሀ ግብር አውጥቶ የተማሪ ምዝገባ እያከናወነ ይገኛል:: የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሕዝብን የሰላም ባለቤት ለማድረግ ያለመ ውይይት እያካሄዱ ይገኛሉ፤ የትምህርት ጉዳይ ደግሞ የክልሉ የተማረ የሰው ኀይል ወካይ ዘርፍ በመሆኑ ትምህርትን ማስጀመር፣ እንዳይቋረጥም ደጀን ሆኖ ማስቀጠል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩ ተደምጧል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 17  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here