እጁን ለሰብዓዊ ድጋፍ እየዘረጋ ያለው የዓለም ሕዝብ እየጨመረ ነው:: በ2019 እ.አ.አ ሰብዓዊ ድጋፍ ውስጥ ከነበረው 152 ሚልዮን ሕዝብ ውስጥ በ2024 እ.አ.አ ወደ 733 ሚሊዮን አሻቅቧል:: በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች እና ጦርነቶች መፍትሔ አጥተው መዝለቃቸው እና ተፈጥሯዊ ክስተቶች መጨመራቸው ለችግሩ መባባስ በመንስኤነት ይነሳሉ:: እነዚህ ክስተቶች ለኢትዮጵያም ፈተና ሆነዋል::
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ዓመት በገጹ ያሰፈረው ጽሑፍ እንደሚጠቁመው በኢትዮጵያ 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ የዕለት ደራሽ ምግብ ይፈልጋል:: ጦርነት፣ ግጭት እና የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ ለሰብዓዊ ተረጂዎች ቁጥር ከፍ ማለት በአብነት ተነስቷል::
የአማራ ክልልም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ አሁንም ድረስ መፍትሔ ባልተበጀላቸው ግጭቶች ውስጥ ይገኛል:: ድርቅ፣ ከፍተኛ የሆነ ዝናብ፣ በረዶ እና የመሬት መንሸራተት የክልሉን ምርታማነት ከመቀነስ አልፈው አምራች እጆች ለጠባቂነት እንዲዘረጉ አድርገዋል::
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ክልሉ ባጋጠመው የሰላም እጦት እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት የዕለት ደራሽ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን የመደገፍ ሥራው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠይቋል፤ እነዚህን ወገኖች ከጠባቂነት አውጥቶ ክልሉ ይታወቅበት ወደ ነበረው ከፍተኛ የማምረት እንቅስቃሴ እንዲገባ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት “ማን ምን ኃላፊነት ይወጣ?” የሚለውም ምላሽ እንዲያገኝ ተጠይቋል::
ባለፈው ዓመትም ይሁን በዚህ ዓመት ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እያጋጠመው ያለው የዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር እንደሆነ በምክር ቤቱ ጉባኤ ተጠቅሷል:: በብሄረሰብ አስተዳደሩ ተወካይ የምክር ቤት አባል የብሄረሰብ አስተዳደሩ ምርታማ የሆኑ ደጋማ እና ወይና ደጋማ የአየር ንብረት ያላቸው አካባቢዎች በጎርፍ፣ በበረዶ እና በመሬት መንሸራተት አደጋ መመታታቸው ተገልጿል:: በዚህም ከ45 ሺህ በላይ ሄክታር በሰብል የተሸፈነ መሬት ለጉዳት ተዳርጓል:: ደኀና፣ ጋዝጊብላ፣ ጻግብጂ፣ ሰቆጣ ወረዳ፣ ዝቋላ እና አበርገሌ በክስተቱ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ናቸው ተብሏል:: ይህም ክስተት በአጠቃላይ በዓመቱ ለማሳካት ከታቀደው ምርት ውስጥ ለ983 ሺህ ኩንታል ምርት መታጣት ምክንያት መሆኑን የምክር ቤት አባሏ አንስተዋል::
በአሁኑ ወቅት በብሄረሰብ አስተዳደሩ 242 ሺህ ሕዝብ ለዕለት ደራሽ ምግብ እጦት መዳረጉ ተገልጿል:: ይህም የተረጂ ሕዝብ ቁጥር ከሴፍቲኔት ተረጂዎች ውጪ መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል ተብሏል::
የዕለት ደራሽ ምግብ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከተለዩት ውስጥ 46 ሺህ ሰዎች ለስደት መዳረጋቸው ተመላክቷል:: ከዚህ ውስጥ 24 ሺህ የሚሆነው በአምራችነቱ ከሚታወቀው ደኀና ወረዳ የተሰደደ መሆኑ ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ማንቂያ ነው::
የምክር ቤት አባሏ የችግሩን አሳሳቢነት ካስታወቁ በኋላ እስካሁን ሲደረግ የነበረውን እና ወደ ፊት ሊደረግ የታሰበውን የሰብዓዊ ድጋፍ አስመልክተው ምላሽ ሰጥተዋል:: በምላሻቸውም ከተረጂው ቁጥር መጠን እና ችግሩ እየፈጠረ ካለው ተጽእኖ አኳያ እየተደረገ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ በቂ አለመሆኑን አንስተዋል:: ለጥር ወር የዕለት ደራሽ ድጋፍ መቅረቡን፣ ነገር ግን ለየካቲት ወር የተያዘ ድጋፍ አለመኖሩ በስጋትነት አንስተዋል:: ይህም ችግሩ ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት እንዳይሆን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል::
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል ከሰብዓዊ ድጋፍ ጋር በተገናኘ ለምክር ቤት አባላት ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል:: በክልሉ በተከሰተው ግጭት ምክንያት የተፈናቀለውን ጨምሮ በተለያዩ ተፈጠሯዊ አደጋዎች ምክንያት እጁን ለዕለት ደራሽ ምግብ እርዳታ የዘረጋው የኅብረተሰብ ቁጥር ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ መሆኑን አስታውቀዋል:: ከዚህ ውስጥ 664 ሺህ 840 የሚሆነው ተፈናቃይ መሆኑንም አክለዋል:: የክልሉ አደጋ መከላከል ኮሚሽን ለተፈናቃይ ወገኖች 27 ሺህ ኩንታል ሰብዓዊ ድጋፍ መመደቡን ጠቁመዋል::
በክልሉ ውስጥ በአጠቃላይ ይኖራል ተብሎ ከሚታሰበው ተረጂ ውስጥ በመተግበሪያ (ሶፍትዌር) አማካኝነት የተለየው 753 ሺህ ሕዝብ መሆኑን አስታውቀዋል:: ይህ ትንበያ ከጥር እስከ መጋቢት ያለውን የሚያጠቃልል እንደሆነ እና ቀጣይ ቁጥሩ ሊጨምርም ሊቀንስም እንደሚችል አስታውቀዋል::
መተግበሪያው ከለየው ውስጥ 405 ሺህ 25 የሚሆነው የተረጂ ቁጥር በረጂ ድርጅቶች ድጋፍ የሚሸፈን መሆኑን አስታውቀዋል:: ቀሪው 347 ሺህ 975 ተረጂ በመንግሥት እና በየአካባቢው አስተዳደር ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል::
የክልሉ መንግሥት ዝናብ አጠር አካባቢዎችን በተለየ ሁኔታ እየደገፈ እንደሚገኝ ዲያቆን ተስፋው አስታውቀዋል:: ማንኛውም ችግር በሚፈጥረው የምግብ አቅርቦት ክፍተት የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ክልሉ ካለው በጀት ቀንሶ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል:: ባለፈው ዓመትም በክልሉ በጀት የመጠባበቂያ እህል ግዥ ተከናውኖ ስለነበር ለችግሩ ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት ሊደርስ የሚችለውን ተጽእኖ መቀነስ ተችሏል ብለዋል::
ኮሚሽነሩ በተጨማሪም ከመጋቢት በኋላ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ እና ዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የተዘለሉ ወረዳዎች ነበሩ:: በመሆኑም እነዚህ ወገኖች እስከዚያ ጊዜ ድረስ መቆየት እንደሌለባቸው ታምኖ ድጋሚ የድጋፍ አቅርቦት መጠየቁን እና ምላሽ ማግኘቱን አስታውቀዋል::
የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደርም ለ242 ሺህ 9 ተረጂዎች ድጋፍ እንዲቀርብለት መጠየቁን ዲያቆን ተስፋው አስታውሰዋል:: ከዚህ ውስጥ ለ119 ሺህ 42 ተረጂዎች ድጋፍ መፈቀዱን አረጋግጠዋል:: ነገር ግን በግምገማው ዝቋላ እና ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ቀድሞ በተደረገው ግምገማ ተዘልለው እንደነበር አስታውሰዋል:: በአሁኑ ወቅት የዕለት ደራሽ ድጋፍ ድጋሚ ተጠይቆ ምላሽ ማግኘቱን እና ለመጓጓዝ በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል::
እንደ ኮሚሽነሩ የመንግሥት አቋም ከተረጂነት መውጣት ነው:: ይህም ማለት ተረጂነት አይኖርም ማለት ሳይሆን በተለያዩ ምክንያቶች ሊያጋጥም በሚችል ችግር ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን (ሰብዓዊ ድጋፍን) በራስ አቅም መሸፈን ነው:: ይህም በምክትል ርእሰ መስተዳደሩ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል::
እንደ ኮሚሽነሩ ሁሉም አካል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍ ጠይቀዋል:: ይህም ከረጂ ድርጅቶች ጠባቂነት ነጻ ለመውጣት አጋዥ ነው:: የዚህ ዓመት የሰብል ግምገማ መካሄዱን ያስታወቁት ዲያቆን ተስፋው፤ በዓመቱ የተመረተው አጠቃላይ ምርት ሁሉንም ሕዝብ መመገብ የሚችል እንደሆነ መረጋገጡን ገልጸዋል::
ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ክልሉ በሴፍቲኔት መደገፍ ከጀመረ 20 ዓመት እነደሆነው አስታውቀዋል:: እስካሁንም ወደ 43 ቢሊዮን ብር መመደቡን፣ ነገር ግን በእነዚህ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከሴፍቲኔት ያልተላቀቀ ማኅበረሰብ መኖሩን ገልጸዋል:: ይህም ክልሉ ካለው ጸጋ ጋር ፍጹም የሚቃረን ነው::
ክልሉ ራሱን ከመመገብ አልፎ እንደ ሀገር የሚጠበቅበትን ይወጣ ዘንድ በክረምት ወቅት ከማምረት በተጨማሪ ለበጋ መስኖ ልማት ትኩረት መስጠት ይገባል:: ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ የአመራረት ዘዴውን ማዘመን (የኩታ ገጠም አስተራረስን ማስፋት፣ የእርሻ ትራክተር እና የሰብል መሰብሰቢያ ኮምባይነሮችን ቁጥር ማሳደግ፣ የግብርና ግብዓትን በበቂ መጠን እና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ፣ የገበያ ትስስር መፍጠርን እና ሌሎችንም የምርት ማሳደጊያ አሠራሮችን እንደ መውጫ መጠቀም ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም