“ሕግ እና ስርዓት ለሀገር መጽናት ወሳኝ ነገሮች ናቸው”

0
109

በክፍል አንድ ዘገባችን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ እና ኮኩሐ ሃይማኖት የትምህርት አበ ነፍስ እና የስብከት ዘዴ መምህር ከሆኑት ሊቀ መምህራን አዲስ ጤናው ጋር ቆይታ አድርገናል:: የሕይወት ተሞክሯቸውን፣ በሕይወታችን ወሳኝ በሆነው ሥነ ምግባር እና የሥነ ምግባር ጉድለቶች ያስከተሏቸው ችግሮች እንዲሁም ከችግሩ መውጫ መፍትሔዎች ዙሪያ ቆይታ አድርገን ነበር፤ ቀጣዩን እና የመጨረሻውን ክፍል እነሆ!

በአብነት ትምህርት ቤት የሥነ ምግባር ትምህርት ምን ምን አንኳር ጉዳዮችን ይዟል?

ዋናዎቹ የሥነ ምግባር ክፍሎች የ16ቱ ሕግጋት ናቸው:: ከዘጸዓት ምዕራፍ 20 ቁጥር ሁለት እስከ 18 እና በማቲዮስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ቁጥር 41 ያሉ ናቸው:: እነዚህም ግብረ ገብነትን የሚያስተምሩ እና የሚያሳስቡ ናቸው:: ማንኛውንም ሰው የማያስቀይሙም ናቸው:: በዘር እና በሃይማኖት ሳይለዩ ለሁሉም መመሪያ የሚሆኑ ናቸው:: ለአብነት አባት እና እናትክን አክብር፣ ፈጣሪህን አምልክ፣ አትስረቅ፣ አትቀማ፣ አታመንዝር፣ ወንድምህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ እና በሀሰት አትመስክር የሚሉ ይገኙበታል:: በእነዚህ ሕጎች መገዛት ከተቻለ ግጭት፣ ስርቆት፣ አለመግባባት እና ሌሎች መጥፎ ነገሮች ይወገዳሉ::

ሕግ እና ስርዓት ለሀገር መጽናት ወሳኝ ነገሮች ናቸው:: ሕግ እና ስርዓት በአንድ ሀገር ከሌሉ መነሻም ሆነ መድረሻ የለም ማለት ነው:: የምንጭ ውኃ በጉዞው ኃይለኛ ጅረት ካለው ከወገኑ ይቀላቀላል:: ከሌለው ግን ተቃጥሎ በመንገድ ይቀራል:: በመሆኑም አስራ ስድስቱ ጅረቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው::

በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን ችግር እንዴት ያዩታል፣ መፍትሔውስ ምንድን ነው?

በሦስት እና አራት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ችግሮች በሀገራችን እየተስተዋሉ ነው:: ግድያው፣ መታፈኑ፣ ዘረፋው፣ ሌብነቱ፣ ማጭበርበሩ በዝቷል:: የችግሩ ክፋት ወንጀሉን የሚፈጽመውን እገሌ ነው ብለህ አታውቀውም:: አባት እና ልጅ መተፋፈን ጀምሯል:: ይህ ትልቁ የሞራል ዝቅጠት ነው:: ልጆች ሆነን ስንማር እቃ ወድቆ እንኳ ስናገኝ የማን ነው ብለን ለባለቤቱ እንመልሳለን:: አሁን በአብነት ትምህርት ቤቶች ሳይቀር ዘረፋ ተስፋፍቷል:: ውድ መጽሐፎች ሳይቀር እየተሰረቁ ነው::

ትውልዱ ነገሮችን ከአንድ ጎን ብቻ ነው የሚያየው፤ ሥራየ በሌላው ላይ ምን ያደርሳል፣ በሰማይስ ምን ያመጣብኛል ብሎ ማሰብ አቁሟል:: ስለ ፍቅር፣ ስለመተሳሰብ፣ ስለመተዛዘን እና ስለትዕግስተኛነት አልተማረም:: የግብረ ገብ ትምህርት ስላልተማረ ጋጠ ወጥነት ይስተዋላል::

የአብነት ትምህርት መቀዛቀዝ እንደ አንድ ምክንያት ሆኖ በትውልዱ የምናየውን ችግር አስከትሏል:: በፊት የቄስ ትምህርት እየተባለ በየአካባቢው ልጆች ሁሉ ይማሩ ነበር:: ፊደል ከማወቅ ባሻገር በሥነ ምግባር የታነጹ ልጆችን ያወጣ ነበር:: ይህ መቆሙ ሀገርን ችግር ላይ ጥሏል::

ቤተክርስቲያን ተጎድታለች፤ መጽሐፍ ቅዱስን ተረድቶ ቅኔውን ዘርፎ ያልወጣ አስተማሪ እሱ ተሳስቶ ሌላውንም ያሳስታል:: አሁን የምናየው ውዥንብርም ከዚሁ የመጣ ነው:: የአብነት ትምህርቱን የተከታተለ በደንብ የበሰለ አስተማሪ ሌላውን ከጥፋት ይታደጋል::

ሀገራችን ኢትዮጵያ የዳቦ ቅርጫት መሆን የምትችል ናት:: እርስ በርሳችን እየተበላላን ሀብታችንን መጠቀም አላወቅንበትም:: ከመለያየት እና ከመጠላላት ይልቅ ወደ እድገት እና ቴክኖሎጂ ፊታችንን ብናዞር ይሻላል:: ሀብት ተቀምጦ ያንን አለመጠቀም ሞኝነት ነው:: ሁሉም ሰው ራሱን ሲያሳድግ፣ ግብረ ገብ ሲያደርግ ሀገር ያድጋል::

እንደ ሃይማኖት አባት ችግሮች ሲከሰቱ እነሱን ለመፍታት ምን አድርጋችኋል?

ግብረ ገብ ትምህርት ለአራት ዓመታት ተምሬያለሁ:: ያስተምሩን የነበሩትም መምህር የማነ ይባላሉ:: ሲበዛ መንፈሳዊ አባት ነበሩ:: ወደ ቤታቸው ሲሄዱ ነድያንን ካገኙ የያዙትን ብር ሰጥተው ነው የሚሄዱት:: እሳቸው ሲያስተምሩ ከማይረሱኝ ነገሮች መካከል “ኢትዮጵያዊያንን አንደኛው ዓለም (የበለጸጉ ሀገራት) በልጦን ሄዷል፤ ምክንያቱም እርስ በርሱ አይመቀኛኝም:: እኛ እርስ በርስ የመጠላለፍ ልማድ አለብን፤ በተለይ የተማረ ከወጣ ተጠልፎ ይወድቃል:: ለመማር ለማወቅ የሚጥረውም ይኮረኮማል፤ በዚህ ምክንያት ድሆች እና ኋላ ቀር ሆነናል” ብለው ያስተማሩኝን አልረሳውም:: ከዛ ጊዜ በኋላ ያለንን ድህነት እና መጥፎ ስም እንዴት መቀየር እንችላለን ብየ በልቦናየ አስባለሁ:: በዚህም የተነሳ ወጣቶችን ሳስተምር የማውቀውን ሁሉ አሟጥጬ ነው የምሰጠው:: ከሦስተኛው ዓለም በሂደት ወደ ሁለተኛው ከዚያም ወደ አንደኛው ዓለም መግባት እንዳለብን አምናለሁ::

ይህ ሲሆን ሂደቱን መጠበቅ አለብን:: በአንድ ጊዜ ወደ አንደኛው ዓለም መግባት አይቻልም:: የባቡር ሀዲድ አንድ ላይ የተያያዘ ነው፤ አንዱ ከተቋረጠ ሁሉንም ፉርጎዎች ይጥላቸዋል:: ስለዚህ ማስተሳሰር ያስፈልጋል::

ጉቦኛ ጉቦኛነቱን ቢተው፣ ሌባ ሌብነቱን ቢያቆም፤ ሁሉም ለሀገሩ መሥራት ቢጀምር ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትቀየራለች:: ተቀምጦ የሚበላው ሕዝብ ስለበዛ፣ የሚሠራው ስለአነሰ ችግሩም አብሮ በዝቷል:: መጽሐፍ ቅዱስም “ሊሠራ ማይወድ ሰው አይብላ” ይላል::

ትልልቅ ሀገራዊ ችግሮች ሲያጋጥሙ ምህላ ጸሎቶች ይደረጋሉ:: እኛም አውጀን አስደርገናል፤ አድርገናል:: ከጸሎቱ ባሻገር ምዕመናንን በተለይም ወጣቱን ወደ ጥፋት እንዳይገባ መምከር፣ መገሰጽ እና ማስተማር ያስፈልጋል:: ያልተመከረ ያልተገሰጸ ወጣት ልጓም እንደሌለው ፈረስ ፊት ለፊት ይነዳል::

ተከባብሮ እና ተቻችሎ ከመኖር አንጻር ሃይማኖታዊ አስተምሮዎች ምን አይነት መሆን አለባቸው?

ለማስተማር መጀመሪያ መማር ያስፈልጋል:: እድሉን ስላገኙ ብቻ መድረክ ወጥቶ ምኑንም ምኑንም ከመናገር መቆጠብ ያስፈልጋል:: በጥላቻ የተሞላ ሌላውን እምነት የሚያንቋሽሽ እና ዝቅ የሚያደርግ አስተምህሮ አያስፈልግም:: እግዚአብሔር ጠላታችሁን እንደራሳችሁ አድርጋችሁ ውደዱ ይለናል፤ ጠላት ከተወደደ ምንም ያላረገን፣ ጠላት ያልሆነን የሌላ እምነት ወገናችን እንዴት ይጠላል::

ስለሆነም በአስተምህሮ ጊዜ መጥላትም፣ መንቀፍም ሆነ መሳደብ አይገባም:: ወንጌሉ የሚለውን ብቻ ከርዕስ ሳይወጡ እና ሌላውን ማንቋሸሽ እና መሳደብ የስብከት ስልት አድርገው ሳይጠቀሙ ነው ምዕመኑን ማስተማር የሚገባው:: ሰላም በመከባበር በመግባባት የሚመጣ ነው፤ ንቀት እና መዘላለፍ ወደማንወጣው ቅርቃር ውስጥ ይከተናል፤ በሃይማኖት የመጣ ነገር ደግሞ ከሁሉም የከረረ አና የባሰ ነው፤ ጥንቃቄ ያሻል::

ልጆች ላይ መሰራት እንዳለበት ነግረውናል፤ እርስዎ ልጆችዎን እንዴት አሳድገዋል?

ልጆቼን ያሳደኩት በምክር ነው:: ጥፋት ባጠፉ ጊዜ ኃይል አልጠቀምም:: ይልቁንም ስህተታቸው እንዲታወቃቸው እና ስህተታቸው ሊያስከትል የሚችለውን ጥፋት አሳያቸዋለሁ:: ከባለቤቴ ጋርም አለመግባባት ከተፈጠረ ቤተሰቡ ትንሽ ልጅ ሳይቀር ስብሰባ ይጠራል:: ልጆቹም ባለቤቴም እኔም ሀሳባችንን እናቀርባለን፤ ጥፋተኛው ጥፋቱን ያምናል፤ በዚህ ችግሩ ይፈታል::

በዚህ አስተዳደግ ሁሉም ልጆቼ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰውልኛል:: በተሰማሩበት መስክም ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን እያገለገሉ ይገኛል:: ወላጆች ልጆቻቸው የት ወጡ? የት ገቡ? ብሎ መከታተል፣ ጥፋትም ሲኖር ተከትሎ መገሰጽ ሳይረፍድ ያስፈልጋል::

ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የካቲት 17  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here