ዓድዋ – የኢትዮጵያዊነት ልኬት

0
191

ዕውቁ የታሪክ ተመራማሪ ሪቻርድ ፓንክረስት “የኢትዮጵያውያን የአንድነት ማሳያ ልኬት፣ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ሕዝባቸውን ያለ አንዳች ልዩነት የመምራት ጥበብን ከፍታ የሚያረጋግጥ ድል” ሲሉ ይገልጹታል – የዓድዋን የድል በዓል። ተመራማሪው አክለውም “የአድዋ ድል ዜና በአውሮፓ ኃያላን ዘንድ የተሸናፊነትን ሥነ ልቦና ያስከተለ፣ በተለይ ሮምን በመሰሉ የአውሮፓ ከተሞች የፖለቲካዊ ቀውስ ምጽዓት መቅረቡን ያረጋገጠ፤ የእንግሊዛዊያንን ሸውራራ እሳቤ በአንድ ሌሊት የቀየረ” ሲሉ ነው ያብራሩት።

ከሰባት ዓመታት በፊት የዓድዋ ጦርነት ተካሂዶ የኢትዮጵያውያን አሸናፊነት በተረጋገጠበት በአድዋ ከተማ ሶሎዳ ተራራ ሥር በዓሉ በድምቀት ሲከበር የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ ታዳሚ ነበሩ፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት “እኔ እና አንተ (ዘጋቢውን መሆኑን ልብ ይሏል) እዚሁ የተገናኘነው፣ በነጻነት እና በእኩልነት የምንኖረው በዓድዋ ድል ምክንያት ነው። የአድዋ ድል በኢትዮጵያዊያን መስዋዕትነት የተረጋገጠ ቢሆንም ብስራቱ ግን የመላው ጥቁር ሕዝቦች ነው” ሲሉ ነበር ድሉን የገለጹት።

ማሜይሬ ሜናሴማይ የተባሉ ካናዳዊ የፍልስፍና ምሁር የአድዋ የድል በዓል ከበዓልነት የተሻገረ ልዩ መልዕክት ያለው መሆኑን ነው ያስገነዘቡት። ምሁሩ እንዳሉት የዓድዋ የድል በዓል በአንዲት አፍሪካዊት አገር የአውሮፓዊ ኃያል መንግሥት እጅ መስጠቱ ብቻ ሳይሆን የማይቻል መሰል እውነት በገሃድ የታየበት ሁነት ነው። የዓለም እሳቤ የተቀየረበት ከመሆኑም ባሻገር በመላው ዓለም በሚገኙ ጥቁሮች ዘንድ የነጻነት ትግል እሳቤ የተቀጣጠለበት ነው።

የዓድዋን ድል በማስመልከት የከተቡ ጸሐፍት እንደሚሉት የአድዋን ድል የኪነ ጥበቡ ዓለም በሚገባው ልክ ለመግለጽ አልተቻለም። በተሻለ ደረጃ ኪነ ጥበባዊ አሻራቸውን ካሳረፉት መካከል ግን አርቲስት እጂጋየሁ ሺባባው (ጂጂ) እና ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።

አርቲስት እጂጋየሁ ሺባባው “ዓድዋ“ በተሰኘ የሙዚቃ ሥራዋ የአድዋ የድል በዓል ከድልም በላይ በኢትዮጵያውያን ደምና አጥንት መስዋዕትነት የተገኘ መሆኑን ነው እንደሚከተለው ያቀነቀነችው:-

“የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነፃነት፣

ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት።’’

ከአርቲስቷ ስንኞች እንደምንገነዘበው አሁን ላይ የተሰጠን ነጻነት እና ሰላማዊ ሕይወት በቀደምት ኢትዮጵያውያን አርበኞች መስዋዕትነት ነው፤ ይህም ምትክ የለሹ የሰው ልጆች ደም እና አጥንት የተከፈለበት ነው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖት፣ ቀለም፣ ዘር፣ ጎሳ … ሳይለያቸው፣ ኢትዮጵያዊነት ብቻ በአንድነት አስተሳስሯቸው ሀገራቸውን ያላስደፈሩበት የአንድነት ገመድ ነው።

ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፣ ባሕል እና አወቃቀር ያጠኑት የታላቋ ኢትዮጵያ መጽሐፍ ደራሲ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሊቨን ኢትዮጵያዊያን በአንድነታቸው ያረጋገጡት የዓድዋ ድል  የጥቁሮች ሁሉ ኩራት መሆኑን ነው የሚያስገነዝቡት። ለዚህ ከሚነሱት አብነቶች መካከል ደግሞ የጥቁሮች መብት ታጋዩ ጃማይካዊው ማርክስ ጋርቬይ ይጠቀሳል። የመብት ተሟጋቹ የዓድዋ ድል ወኔ እና ስንቁ መሆኑን በማንሳት “ኢትዮጵያ እውነተኛዋ የአባቶቻችን ምድር” በማለት ለነጻነት ቅስቀሳው በስፋት ተጠቅሞበታል።

ከዓድዋ ድል ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተሳተፉት የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒሥትር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒሥትር ሚያ አሞር ሞትሌይ “በጉባኤው ባደረጉት ንግግር የዓድዋ ድል የመላው የጥቁር ሕዝብ ታሪክ ነው” በማለት መስክረዋል። በጽናት ማንኛውንም ፈተና ማሸነፍ እንደሚቻል የሚያሳይ ትልቅ የዓለማችን ታሪክ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።

የዓድዋ ድል “ኢትዮጵያዊያን ዘመናዊ መሣሪያ ከታጠቀ የቅኝ ገዢ ኀይል ጋር ተፋልመው ያሸነፉበት፣ በትብብር፣ በአንድነት እና በጽናት ማንኛውንም ፈተና ማሸነፍ እንደሚቻል ያረጋገጠ ታላቅ ታሪክ ነው” ሲሉ ነው በአጽንኦት የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒሥትር ሚያ ሞትሌይ እንዳሉት የዓድዋ ድል ለአፍሪካ ሕብረት ምሥረታ እና ለዛሬው የአህጉሩ ሀገራት መሰባሰብ መሠረት ነው። በመሆኑም በዓድዋ ድል መንፈስ ህብረቱ ጠንክሮ መሥራት ይጠበቅበታል። የአፍሪካ መሪዎችም የሚናገሩትን ንግግር ወደ መሬት አውርደው መሥራት ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የካቲት 17  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here