ዓድዋ የጥቁር ሕዝብ ድል

0
102

የዓድዋ ድል  ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስከብራ ዛሬ ድረስ እንድትዘልቅ፤ ኀያል ነን ባዮች አውሮፓውያን አንበርክከዋቸው የነበሩ አፍሪካውያን ነጻነታቸውን እንዲያውጁ ያስቻለ ታላቅ ድል ነው፡፡ የዓድዋ ድል  በመሪር መስዋትነት ውጤት የተገኘ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ኩራት ሆኖ ይታወሳል፡፡

ታሪኩ መነሻውን የሚያደርገው ከዛሬ 129 ዓመት በፊት ነው፡፡ ጦርነቱ በአጼ ምኒልክ የንግሥና ዘመን ከኃያሏ ጣሊያን ጋር የተካሄደ ነው፡፡

የጦርነቱ መሠረታዊ መነሻ ምክንያት የጣሊያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ የነበራት ፍላጎት  እንደሆነ ያስታወቁት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጌትነት ያሳቦ ናቸው፡፡ ጣሊያኖች ይህንንም ፍላጎታቸውን ዕውን ለማድረግ የውጫሌን ውል ስምምነት እንደ ምቹ አጋጣሚ መጠቀማቸውን አስረድተዋል፡፡

የውጫሌ ውል ስምምነት 20 አንቀጾች ነበሩት፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን ያለ ጦርነት በእጅ አዙር የቅኝ ግዛቷ አካል ለማድረግ የተጠቀመችበት አንቀጽ 17 ነው፡፡ የዚህን አንቀጽ ውል ስምምነት የአማርኛ ትርጓሜ አፄ ምኒልክ በወቅቱ ቢረዱትም በጣሊያንኛ በሰፈረው ትርጓሜ እንደተጭበረበሩ ግን እንዳላወቁ መምህር እና ተመራማሪ አስታውቀዋል፡፡ የጣሊያንኛ ትርጓሜ “ኢትዮጵያ ከአውሮፓውያን ነገሥታት ጋር ለምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጣሊያን በኩል ይሆናል” የሚል አስገዳጅ ስምምነት መሆኑን መምህር እና ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡

የአማረኛው ትርጓሜ  ደግሞ “ኢትዮጵያ ከአውሮፓውያን መንግሥታት ጋር ለምታደርገው ግንኙነት የጣሊያንን አጋዥነት ልትጠቀም ትችላለች” የሚል ነው፡፡ ይህ ስምምነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ክብር የሰጠ ሆኖ ይነሳል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ካልፈለገች ግን እንደ ሉዓላዊ መንግሥት ቀጥታ ከአውሮፓ ሀገራት ጋር የንግድም ሆነ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማድረግ እንደምትችል ዕውቅና የሰጠ ጭምር ነው፡፡

አጼ ምኒልክ በእቴጌ ጣይቱ አማካኝነት የአንቀጹ ስምምነት የጣሊያንኛ ትርጓሜ  የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያሳጣ መሆኑን ከተረዱ በኋላ ውሉን ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጋቸውን ታሪክ ሕያው ምስክር ነው፡፡ የእጅ አዙር ውጊያው የከሸፈባት ጣሊያን ኢትዮጵያን በኅይል ለማንበርከክ የጦርነት ጉሰማ ውስጠ ገባች፡፡

አጼ ምኒልክም የክተት አዋጅ አወጁ፤ “እግዚአብሄር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ፣ ሀገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለ እኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም ሀገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የሀገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የሀገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልምርህም፤ ማርያምን! ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡”

የታሪክ ምሁራን የዐጼ ምኒልክን የክተት አዋጅ ጥበብ የተሞላበት፣ የካበተ የአመራርነት ልምዳቸውን ያሳየ፣ ሕዝብን እንዴት መያዝ እና በፍቅር ከጎናቸው ማሰለፍ እንደሚችሉ ያረጋገጠ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ይህም የንጉሡ ጥሪ ታዲያ መላው ኢትዮጵያዊ የተመቸ መጓጓዣን ሳይጠብቅ፣ እግሩን ለጠጠር እና ደረቱን ለጦር ሰጥቶ፣ ፀሐይ እና ብርድ ሳይበግሩት ለሀገሩ ራሱን ሊገብር ዓድዋን  የግብዓተ መሬቱ መፈጸሚያ አድርጎ ተሟል፡፡

ጦርነቱም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተፈጽሟል፡፡ በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ራይሞንድ ዮናስ “የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ በተደራጀው  ግዙፍ የጣሊያን ሠራዊት ላይ የማይታሰብ ድል ተጎናጸፈች፡፡ ይህም ድል የአውሮፓን የመስፋፋት እንቅስቃሴ የገታ፣ ኢትዮጵያም ነጻነቷን ያስጠበቀችበት ድል!” ሲል ገልጾታል፡፡

ዓድዋ ዛሬም የኢትዮጵያውያ አይበገሬነት ማሳያ፣ የጥቁር ሕዝብ ሁሉ መብት መከበር ዋልታ፣ ጥቁር እና ነጭ ከቆዳ ቀለም በዘለለ የኅይል ሚዛን ወሳኝ እንዳልሆነ ያረጋገጠ ሆኖ ዘንድሮ 129 ዓመቱ እየተከበረ ነው፡፡ ዓድዋ ድል ያለ መስዋዕትነት እንደማይገኝ ያረጋገጠ የጦርነት ሜዳ መሆኑን መምህር እና ተመራማሪው ጌትነት ያሳቦ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያዊነት ከአምባላጌው ጦርነት ጀምሮ እስከ መቀሌው ከበባ፣ አለፍ ሲልም ዓድዋ ላይ ለሀገር ሉዓላዊነት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ተመራማሪው ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው የከፈለትን  መስዋትነት ያስረዱት ጣሊያኖች መቀሌ ላይ ገንብተውት የነበረውን ከፍተኛ  ምሽግ ኢትዮጵያውያን በገመድ፣ በመሰላል እና በሌሎችም መወጣጫ አማራጮች እየተንጠላጠሉ የጨበጣ ውጊያ እስከ ማድረግ የደረሱበትን ሁኔታ  በመጠቆም ነው፡፡

የጣሊያን ወረራ ኢትዮጵያውያን ለመስዋትነት የማይሳሱ መሆናቸው በተግባር የተገለጠበትም ነው ይሉታል መምህር እና ተመራማሪው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጦረኞች የጣሊያን መድፍ፣ መትረየስ እና ሌሎች ከባድ የመሣሪያ ድምጾች አላስበረገጋቸውም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን በወቅቱ ሆነው የሚያስቡት ነጻነትን ነውና፡፡

ኢትዮጵያውያን ከልዩነታቸው በፊት ነጻነታቸውን እና ሉዓላዊነታቸውን እንደሚያስቀድሙ ዓድዋ ምስክር ነው፡፡ ይህን መምህር እና ተመራማሪው በማስረጃ  ያረጋግጡታል፡- በወቅቱ ከአጼ ምኒልክ ጋር ልዩነት የነበራቸው መኳንንት እና መሳፍንት ልዩነታቸውን በይደር ትተው በአንድነት የዘመቱበት ሌላው ከሀገር የሚበልጥ ጉዳይ ላለመኖሩ ማሳያ ነው፡፡

“እየመጣ ያለው እሳት ከእኔ  አይደርስም” ብሎ የሚቀመጥ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ኢትዮጵያዊ ቀፎዋ እንደተነካ ንብ “ሆ!” ብሎ የሚነሳ መሆኑን ዓድዋ አረጋግጧል ሲሉ መምህር እና ተመራማሪው አንስተዋል፡፡ ለዚህ ማሳያቸው በተለይ በቅድመ ዓድዋ (መቀሌ) ጦርነት ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ጦረኞች ከፍተኛ ዋጋ መክፈላቸውን በመጠቆም ነው፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ ዳኛቸው ቶሎሳ በበኩላቸው ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመያዝ የነበራት ፍላጎት ሁለት ዓላማዋን ለማሳካት የተደረገ እንደ ነበር አስታውሰዋል፡፡ የመጀመሪያው አፍሪካ የምትታወቅበትን የጥሬ እቃ ግብዓት ለመውሰድ  እና ከአውሮፓውያን ኀያላን ሀገራት ጋር የሚስተካከል ኅይል እንዳላት ለማሳየት ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር ልጄን፣ ጨርቄን፣ ማቄን፣ መሬቴን፣ ሰብሌን … ሳይሉ በአንድነት ወጥተው በከፈሉት ውድ የሕይወት መስዋትነት የጣሊያንን ዓላማ ማክሸፍ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም የጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነጻነት የድል በዓል ሆኖ ዛሬም በትውልድ ቅብብሎሽ እየተከበረ ይገኛል፡፡

“ዓድዋ የኢትዮጵያውያን አንድነት ማሳያ የጥቁር ሕዝብ ኩራት ነው” በማለት የገለጹት ደግሞ በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ ናቸው፡፡ የዕዙ የሥራ ኃላፊዎች የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን በጎበኙበት ወቅት ሌተናል ጀኔራሉ እንዳሉት ድሉ መላው ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን ተሰባስበው በፅኑ የሀገር ፍቅር ስሜት እና አንድነት የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህም ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ቀንዲል በመሆን ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሠረት የጣለ ዘመን አይሽሬ ኩራት እና መገለጫ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

ሌተናል ጀኔራሉ “የአሁኑ ትውልድ ታሪኩን በወጉ ተረድቶ የአያት ቅድመ አያቶቻችንን ወኔ እና አንድነት አንግቦ በማይነጥፍ የሀገር ፍቅር ስሜት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ማለታቸውን  የሠራዊቱ የማኅበራዊ (ፌስቡክ) ትስስር ገጽ ዘገባ ያሳያል፡፡ ለዚህም ታሪኩን የሚመጥን የኢትዮጵያውያን አይበገሬነት እና አንድነት በጉልህ የሚያሳይ የድሉ መታሰቢያ ሙዚየም መገንባቱ ታሪካችንን አስጠብቀን ለትውልድ እንድናሻግር ያስችለናል ብለዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪዉ የአሁኑ ትውልድ የቤት ሥራ ምን መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የአሁኑ ትወልድ የሀገሬን ሉዓላዊነት አሳልፌ ከምሰጥ ሕይወቴን ልጣ ብሎ ያስረከበውን የእናት አባቶቹን ታሪክ በአግባቡ በመዘከር የነገ ዓድዋውን ኢኮኖሚያዊ ከፍታ አድርጎ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የኢኮኖሚ ጉዳይ የአሁኑ ዘመን ዋነኛ ፈተና ነው ያሉት አቶ ዳኛቸው፣ በመሆኑም ትውልዱ የሥራ ባሕልን በማዳበር በኢኮኖሚ ከፍ ያለች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ዓላማን አንግቦ ሊጓዝ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here