ከ1896 እስከ 1960 እ.አ.አ ድረስ ለ65 ዓመታት በፈረንሳይ ቅኝግዛት ሥር ስትማቅቅ የኖረች ሀገር ናት:: ፈረንሳውያኑም “የፈረንሳይ የላይኛው ቮልታ” እያሉ ነበር የሚጠሯት፤ በሀገሪቱ ውስጥ የሚፈሱትን ጥቁሩ ቮልታ፣ ነጩ ቮልታና ቀዩ ቮልታ የሚባሉ የሶስት ወንዞቿን ስም መሠረት አድርገው:: በ1968 ዓ.ም ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስትላቀቅ ደግሞ ስሟ “የፈረንሳይ” የሚለውን ሸክም አራግፎ “ሰሜናዊ ቮልታ” ተባለ:: የመጀመሪያ ፕሬዚደንቷም ማውሪስ ያሜኦጎ ነበሩ፤ የአሁኗ ቡርኪና ፋሶ::
ቡርኪና ፋሶ ዋና ከተማዋ ዋጋዱጉ ትባላለች። ከተማዋ የሀገሪቱ የአስተዳደር፣ መገናኛ፣ ኢኮኖሚ፣ ባሕል እና ሌሎች መስኮች ማዕከል ናት:: የቡርኪና ፋሶ ብሔራዊ ቋንቋ ፈረንሳይኛ ነው። በሥራ ቋንቋነት ሞሲ፣ ቢሳ፣ ዳይሉ እና ፉላ የተሰኙ ቋንቋዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ:: አጠቃላይ ስፋቷም 274 ሺህ 200 ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን በዓለም በቆዳ ስፋቷ 74ኛ ደረጃን ይዛለች:: የሕዝብ ብዛቷም እንደ አውሮፓዊያን ዘመን ቀመር በ2024 በተሠራ ግምት 23 ሚሊየን የሚጠጋ ነው። ይህም በሕዝብ ብዛት ከዓለም 60ኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አስችሏታል።
ቡርኪና ፋሶ ትሮፒካል የተሰኘው ዝናባማ እና ደረቃማ የአየር ጸባዮች የሚፈራረቁባት ሀገር ናት:: በክረምት ወቅት እስከ 900 ሚሊ ሜትር የሚደርስ ከፍተኛ ዝናብ ያጋጥማታል፤ በዚህም የተነሳ ለተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋዎች ተጋላጭ ናት:: በበጋ ወቅት ደግሞ እስከ 47 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ ከፍተኛ ሙቀት ያጠቃታል:: በዚህም ድርቅ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ዜጎቿ ለረሀብ ይጋለጣሉ:: የቡርኪና ፋሶ የአየር ሁኔታ በእርግጥ እንደየ አካባቢው ይለያያል::
ቡርኪና ፋሶ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ሀገር ናት። ለአብነት ወርቅ፣ ማግኒዢየም፣ ላይምስቶን፣ ማርብል፣ ፎስፌት፣ ፑሚስ እና ጨው ይገኙባታል:: የሀገሪቱ ሳራማ መሬት (ሳቫና ግራስላንድ) ለተለያዩ የዱር እንስሳት አመቺ ነው:: ዝሆኖች፣ አንበሶች፣ ነብሮች (ሊኦፓርድ) እና ጎሾች (ቡፋሎ) በስፋት ይገኛሉ:: ዳብዩ፣ አሪል እና ሌሎች ብሔራዊ ፓርኮች እንዲሁም ጥብቅ ደኖችም ይገኛሉ::
የአምባገነን አዙሪት ፅንስ
ማውሪስ ያሜኦጎ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግሥት የቮልታ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ከሚባለው የእርሳቸው ፓርቲ ውጪ ሌሎች የሀገሪቱን ፓርቲዎች በሙሉ ከእንቅስቃሴ አገዱ (ልማቱን ለማስቀጠል 60 ዓመት የእኛ ፓርቲ ሥልጣን ላይ መቆየት አለበት። ሌሎቹ ፓርቲዎች ፀረ ልማት፣ ፀረ ዴሞክራሲ፣ ፀረ… ወዘተ ናቸው ብለውም ዲስኩር አሰምተውም ነበር ተብለው ይታማሉ!):: በድርጊታቸው ያዘነው ፖለቲካዊ ተሳትፎው የታፈነበት ሕዝብ በ1966 እ.አ.አ ጀምሮ ተማሪዎች፣ የሠራተኛ ማኅበራት እና የመንግሥት ሠራተኞች ሀገሪቷን በአድማና በሰልፍ አንቀጠቀጧት::
የሀገር መረበሽን ለማስቆም በሚል ሰበብም ጦር ሠራዊቱ በጉዳዩ ላይ እጁን አስገባና ሕገ መንግሥቱን አገደ፤ ፓርላማውን በተነ፤ ፕሬዚደንት ያሜኦጎንም ከሥልጣናቸው አባረራቸው:: ከዚያ በኋላ ሀገሪቱ ምንም የተረጋጋና ሁሉን ያማከለ መንግሥት ልታገኝ አልቻለችም:: አንዱ ወታደር በሌላው እየተፈነቀለ እስከ 1987 እ.አ.አ ድረስ ሌተናል ኮሎኔል ሳንጎሌ ላሚዛና፣ ኮሎኔል ሳዬ ዜርቦ፣ ሜጀር ዣንክላውድ ኦዌድራኦጎ፣ ካፒቴን ቶማስ ሳንካራ የሚባሉ አራት ወታደሮችን መሪዎች አድርጋ አፈራርቃለች ይላል ብሪታኒካ ላይ ያገኘነው መረጃ::
ቶማስ ሳንካራ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ “ለውጥ ያስፈልጋል!” በሚል መፈክር ነበር:: “ሀገሪቱ ለውጥ ያስፈልጋታል፤ ለውጡ የሚጀምረው ደግሞ ከስሟ ነው” በማለትም የሀገሪቷን ስም ከሰሜናዊ ቮልታነት ወደ ቡርኪና ፋሶ ቀየሩት:: ስሙን የፈጠሩት ራሳቸው ቶማስ ሳንካራ ናቸው:: ቃሉን ለማበጀትም ሙሬ እና ዲዮላ ከሚባሉ የሀገሪቱ ሁለት ዐበይት ቋንቋዎች አንድ፣ አንድ ቃል ተውሰዋል:: በሙሬ ቋንቋ “ቡርኪና” ማለት “ሐቀኛ” ሲሆን፣ “ፋሶ” ደግሞ በዲዮላኛ “አባት ሀገር” ማለት ነው:: እነዚህን ሁለት ቃላት አገጣጠሙና ቡርኪና ፋሶ አሏት- “የሐቀኞች ሀገር”:: ይሁን እንጂ፣ የቶማስ ሳንካራ መንግሥት ብዙም አልከረመም:: በ1987 በካፒቴን ብሌይስ ካምፖሬ የተመራ መፈንቅለ መንግሥት ቶማስ ሳንካራን ገድሎ የመፈንቅለ መንግሥቱን መሪ ብሌይስ ካምፖሬን የሀገሪቱ ፕሬዚደንት አደረገ:: ከ1987 ጀምሮም እስከ 2014 ድረስ ካምፖሬ ሀገሪቱን ሕዝቧን እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ ገዛቸው:: በቅርቡ ደግሞ የ36 ዓመቱ ኢብራሂም ትራኦሬ ወደ ስልጣን መጥቷል::
ለውጡ
ትራኦሬ ገና በሁለት ዓመታት ውስጥ ቡርኪና ፋሶን በኢኮኖሚ እና ሌሎች መስኮች እየለወጣት መሆኑ ይገለፃ። ወደ ስልጣን ከመጣ በሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ ሀገሪቱ የሚገባውን የሴፍቲኔት እርዳታ በማስቆም ሀገሪቱ የነበረባትንም የውጪ ዕዳ ሙሉ በሙሉ ከፍሎ ከዕዳ ነፃ ሀገር አድርጓታል።
ወደ ስልጣን እንደመጣ የመጀመሪያው እርምጃ ፈረንሳይ እና ምዕራባውያንን ከነዲፕሎማቶቻቸው ከነሠራዊታቸው እና ከእነኩባኒዎቻቸው ቅሌን ጨርቄን ሳይሉ ተጠራርገው እንዲወጡ ማድረግ ነበር። ይህን አርዓያ በመከተል ሌሎች አፍሪካ ሀገራትም ምዕራባውያኑን አይናችሁን ለአፈር ብለው አስወጥተዋል። አሁንም ለማስወጣት እያኮበኮቡ ያሉ አፍሪካዊ ሀገራት አሉ:: ቡርኪና ፋሶ በኤሌክትሪክ እና በፀሐይ ኃይል የሚሰራ መኪና በራሷ ምርት፤ በራሷ ባለሞያዎች አምርታ ለገበያ አቅርባለች:: የምዕራባዊያኑ ፈተና ግን በዚህ መስክ እየፈተናት መሆኑ ተገልጿል::
ኢኮኖሚ እና ቱሪዝም
የቡርኪና ፋሶ የውጭ ንግድ ከነበረበት ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በ2011 እ.አ.አ ወደ 754 ሚሊዮን ዶላር አሽቆልቁሎ ነበር፤ ለዚህ ደግሞ በሀገሪቱ ተከስቶ የቆየው አለመረጋጋት እንደ ዋነኛ ምክንያት ይነሳል:: በዓለም አቀፉ ባንክ (አይኤም ኤፍ) መረጃ መሠረት የሀገር ውስጥ ምርት እድገት 92 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል::
ቡርኪና ፋሶን ሲጎበኙ ማየት ያለባችሁ 15 ነገሮች በማለት ትሪፕ አድቫይዘር ዶት ኮም ካወጣቸው መካከል ሪዘርዴ ናዚንጎ የተሰኘው ዝሆኖች በስፋት የሚገኙበት ፓርክ፣ ጥንታዊ ቅርጻቅርፆች የሚታዩበት ሲምፖዚየም፣ የኦጋዶጉ ገበያ፣ የቦቦ ደላሶ ጥንታዊ እና ማራኪ መስጅድ፣ የኦጋዶጉ ካቴድራል እና ሌሎች ተጠቅሰዋል::
በ20ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በቡርኪና ፋሶ ሞሲ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ሶሮኔ በመባል ይጠሩ የነበሩት ከመልከ መልካም ወጣቶች መካከል የሚመረጡት ወንዶች በሴቶች አልባሳት እና የጸጉር አሰራር የሚያጌጡ፤ በተለምዶ የሴቶች የሥራ ድርሻ የሆኑትን ሥራዎች የሚሠሩ ነበሩ::
ሶሮኔዎች ከሴቶች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲፈፅሙ አይፈቀድላቸዉም ነበር፤ ሆኖም እድሜያቸዉ ለጋብቻ ሲደርስ ሹማምንቱ ሚስት ሊሰጧቸዉ ይችላሉ። በዚህ ሁኔታ ትዳር የመሰረቱ ሶሮኔዎች ልጅ ከወለዱ እና የመጀመሪያዉ ልጅ ወንድ ከሆነ እንደ አባቱ ሶሮኔ የሚሆን ሲሆን ሴት ከሆነች ደግሞ በሹማምንቱ ለሶሮኔ በሚስትነት ትሰጥ ነበር።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም