ዓድዋ- አንድ የመሆን ምልክት!

0
92

ዓድዋ ሲነሳ ኢትዮጵያም አብራ ትነሳለች ምክንያቱ ደግሞ የአድዋ ድል ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስከብራ ዛሬ ድረስ እንድትዘልቅ ያስቻለ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ማሳያ የጥቁር ሕዝብ ኩራትም ነው።

ዓድዋ ላይ የተገኘዉ ድል በእድል አሊያም  በቀላሉ እና በአጋጣሚ  የተገኘ ሳይሆን ኢትዮጵያዉያን በሙሉ በአንድነት በከፈሉት   መሪር መስዕዋትነት  የተገኘ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ኩራት ነዉ። ዘንድሮም 129ኛው የድል በዓል መታሰቢያ እየተከበረ ነው፡፡

ጣሊያኖቹ ፍላጎታቸውን ዕውን ለማድረግ ያመቻቸዉ ዘንድ የውጫሌን ውል ስምምነት እንደ ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመዉበታል፡፡

የውጫሌ ውል ስምምነት 20 አንቀጾች የነበሩት ሲሆን ከነዚያ አንቀጾች መካከል ጣሊያን ኢትዮጵያን ያለ ጦርነት በእጅ አዙር የቅኝ ግዛቷ አካል ለማድረግ የተጠቀመችበት አንቀጽ 17 ነው፡፡

የዚህን አንቀጽ ውል ስምምነት የአማርኛ ትርጓሜ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ክብር የሰጠ ቢሆንም የጣሊያንኛ ትርጓሜ  ግን “ኢትዮጵያ ከአውሮፓውያን ነገሥታት ጋር ለምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጣሊያን በኩል ይሆናል” የሚል አስገዳጅ ስምምነት መሆኑን እቴጌ ጣይቱ አረጋገጡ።

አፄ ምኒልክ በእቴጌ ጣይቱ አማካኝነት የአንቀጹ ስምምነት የጣሊያንኛ ትርጓሜ  የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያሳጣ መሆኑን ከተረዱ በኋላ ውሉን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አደረጉት፡፡ የእጅ አዙር ውጊያው የከሸፈባት ጣሊያንም ኢትዮጵያን በኃይል ለማንበርከክ ጦርነት  ጀመረች፡፡

የጣሊያንን የጦርነት ፍላጎት  ያጤኑት አፄ ምኒሊክም የክተት አዋጅ አወጁ፡፡ ይህን የንጉሡን ጥሪ የሰማ   መላው ኢትዮጵያዊም  የተመቸ መጓጓዣን ሳይጠብቅ፣ እግሩን  ለጠጠር እና ደረቱን ለጦር ሰጥቶ፣ ፀሐይ እና ብርድ ሳይበግሩት፣ ስንቁን  እና ሌሎች መሳሪያወቹን  በግሉ  በማዘጋጀት ለሀገሩ ራሱን ሊገብር ዓድዋን  የግብዓተ መሬቱ መፈጸሚያ ሊያደርግ እና የሃገሩን ሉኣላዊነት ሊያስጠብቅ ሆ ብሎ  ተመመ፡፡

ጦርነቱም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በኢትዮጵያ ዉያን አሸናፊነት ተፈጸመ፡፡ ይህን የኢትዮጵያዉያን  አንጸባራቂ  ድል የተገነዘበዉ በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ራይሞንድ ዮናስ “የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ በተደራጀውን ግዙፍ የጣሊያን ሠራዊት ላይ የማይታሰብ ድል ተጎናጸፈች፡፡ ይህም ድል የአውሮፓን የመስፋፋት እንቅስቃሴ የገታ፣ ኢትዮጵያም ነጻነቷን ያስጠበቀችበት ድል” ሲል ገልጾታል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከልዩነታቸው በፊት ነጻነታቸውን እና ሉዓላዊነታቸውን እንደሚያስቀድሙ ዓድዋ ምስክር ነው፡፡ ለዚህ እሳቤ እንደማስረጃ   ለመጥቀስ ያህል  በወቅቱ ከአፄ ምኒሊክ ጋር ልዩነት የነበራቸው መኳንንት እና መሳፍንት ልዩነታቸውን በይደር ትተው በአንድነት የዘመቱበት ሌላው ከሀገር የሚበልጥ ጉዳይ ላለመኖሩ ማሳያ ነው፡፡

“እየመጣ ያለው እሳት እኔ ጋር አይደርስም” ብሎ የሚቀመጥ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ኢትዮጵያዊ ቀፎዋ እንደተነካ ንብ ሆ ብሎ የሚነሳ መሆኑን ዓድዋ አረጋግጧል።

የአሁኑ ትውልድም ታዲያ ታሪኩን በወጉ ተረድቶ የአያት ቅድመ አያቶቹን  ወኔ እና አንድነት አንግቦ የማይነጥፍ የሃገር ፍቅር ስሜትን ተላብሶ  የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እና ሃገሩ የምትጠይቀዉን ሃላፊነቶች     በመፈጸም የአድዋን የድል ታሪክ ለትዉልድ የማሻገር ሃላፊነቱን  ሊወጣ ገባዋል።

በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here