ለመልሶ ግንባታ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል ተባለ

0
122

በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች በክልሉ የደረሰውን ጉዳት በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችል የምክክር መድረክ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች፣ አምባሳደሮች እና አጋር አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ መድረኩ የክልሉን አሁናዊ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅ እና የሰብዓዊ ርዳታን ለሕዝባችን ተደራሽ ለማድረግ ብሎም የወደሙ የመሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ክልሉ በጦርነት፣ በድርቅ እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዱን የገለጹት ርእሰ መሥተዳደሩ በአሁኑ ሰዓት በክልሉ ውስጥ የዘለቀው ግጭትም ትልቅ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል።

በሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉልህ አበርክቶ ያለውን የአማራ ሕዝብን ሰላም በማረጋገጥ ክልሉን መልሶ ለማልማት ከአጋር አካላት ጋር መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች በክልሉ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ርእሰ መሥተዳደሩ ጠይቀዋል።

የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ/ር) ክልሉ ባለፉት ዓመታት በደረሰበት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለከፍተኛ ችግር መጋለጡን አንስተዋል።

በክልሉ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከ10 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ (አንድ ነጥብ ሦስ ትሪሊዮን ብር ያህል) እንደሚጠይቅ ያነሱት ቢሮ ኃላፊው የክልሉ መንግሥት በየዓመቱ ለመልሶ ግንባታ በጀት መድቦ ሲሠራ ቢቆይም ከጉዳቱ መጠን አንፃር መሸፈን አለመቻሉን ገልጸዋል።

በመሆኑም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች እና የሲቪል ማኅበራት ትርጉም ያለው ድጋፍ እንዲያደርጉ በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ ነን ብለዋል።

ክልሉ አሁን ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ እና ሌሎችም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

(ቤተልሄም ሰለሞን)

በኲር የካቲት 24  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here