ፍርሃት ወዳጃችንም፤ ባላንጣችንም ነው። ህይወታችንን ከአደጋ ሊያተርፍልን ከህልማችንም ሊነጥለን ይችላል። አንዲትን ኪሳራን የምትፈራ ነጋዴ አስቧት፤ በመፍራቷ በጥንቃቄ ስታቅድ፣ በርትታ ስትሰራ እንዲሁም ከእርሷ የተሻሉ ሰዎችን ምክር ስትፈልግ በመጨረሻም የንግድ ስራዋን ስኬታማ እንዲሆን ያግዛታል። በተቃራኒው ደግሞ አንድ ክፍሉ ዉስጥ መናገርን አብዝቶ የሚፈራ ተማሪ ውድቀትን በመፍራት ብቻ አቅመ ቢስ ሆኖ ሲቀመጥ አስቡት። ፍርሃት እኛን ወደተሻለ ነጋችን የማስፈንጠር ወይም ወደኋላ ሸብቦ የመያዝ አቅም ያለው በሁለት አቅጣጫ የተሳለ ሰይፍ ነው።
“ዘ ጊፍት ኦፍ ፊር” በተሰኘው የጋቪን ዲ ቤከር መጽሐፍ ፍርሃት ከጥቃትና ጉዳት የሚጠብቀን ዉድ የሆነ የህይወታችን ረዳት ተደርጎ ተገልጿል። በ።ተጨማሪም በሱዛን ጄፈርስ “ፊል ዘ ፊር ኤንድ ዱ ኢት ኤኒዌይ” ፍርሃት ገጥመን ካሸነፍነው ወደ እድገት እና ስኬት እንደሚመራን የስሜት መሰናክል ተገልጿል። እነዚህን ሁለት አተያዮች በመመርመር ፍርሃታችን እንደ ድልድይ ወይም እንደ ማረሚያ ቤት ሆኖ በመንታ ገጽ እንዴት ሊገጥመን እንደሚችል ለመዳሰስ እንሞክራለን።
ፍርሃት ምንድን ነው?
ፍርሃት ሰዎች አጋጠመን ብለው ለሚያስቡት ስጋት የሚሰጡት ወሳኝ ግብረመልስ ነው። በፊዚዮሎጂያዊ አገላለጽ ፍርሃት በስጋት ጊዜ ልብ ምታችንን፣ ደም ዝዉዉራችንን እና ንቁነታችንን በመጨመር የመጋፈጥን ወይም የማምለጥን ምላሽ እንድንሰጥ የሚያነሳሳ ነው።
በስነልቦናዊ አገላለጽ ደግሞ እንደጭንቀትና የነገሮችን አሉታዊ ዉጤት በመጠበቅ መልኩ ይገለጻል። በስሜት ረገድም ፍርሃት ጭንቀትና ድንጋጤን ይቀሰቅሳል። እነዚህ ምላሾችም ካጋጠመን ስጋት ጋር ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ወይም ለመሸሽ እንድንዘጋጅ የሚያደርጉን ናቸው።
ፍርሃት ለቅጽበታዊ ስጋት የምንሰጠው ምላሽ ሲሆን ጭንቀት ደግሞ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ወደፊት ስለሚከሰት አደጋ የሚሰማን ስጋት ነው። ፍርሃት ማለት የኛን ትኩረት የሚፈልግ የሆነ ነገር እንዳለ የሚጠቁም ምልክትና ማስጠንቀቂያ ነው። ጭንቀት ግን ነገሮችን አግዝፎ በመገመት፣ የኛን የመቋቋምና የመመከት አቅም ዝቅ አድርጎ በማዬት የሚመጣ ነው።
ፍርሃት እንደወዳጅ
ዲ ቤከር እንደሚገልጸው ፍርሃት ስጦታችን ነው። የሚፈጠሩ አደጋዎችን ቀድመን እንድንተነብይና ደህንነታቸው ካልተጠበቁ አካባቢዎች እንድንርቅ ወይም አላስፈላጊ ከመሰሉን ሁኔታዎች ገሸሽ በማለት አስፈላጊ ቅድመ ጥንቃቄዎችን እንድናደርግ ያስገድደናል። ደመነፍሳችን ላይ ዕምነት ማሳደር ህይወታችንን ሊታደግልን ይችላል። ብዙ ጊዜ ተፈጥሯዊ (ደመነፍሳዊ) ስሜታችንን ስናዳምጥ አደጋዎች ግልፅ ሆነው ከመታየታቸው በፊት መረዳት እንችላለን።
ፍርሃት እንድንዘጋጅ፣ እንድንሰለጥን እና እንድንሻሻል ሊገፋፋን ይችላል። አትሌቶች፣ ተዋንያን እና ሌሎች ባለሙያዎች ክህሎታቸዉን በመሞረድ እና ልቆ በመገኘት ፍርሃታቸውን ወደ ብርታት ይቀይሩታል። በፍርሃት ጊዜ በሰውነታችን ውስጥ የሚፋጠነው የሆርሞን መመንጨት ትኩረትን ይጨምራል፤ ስራን ያቀላጥፋል፤ ሰዎች ገደቦቻቸዉን አልፈው እንዲሰሩ ያስችላል።
ፍርሃትን ማሸነፍ በስሜትና ስነልቦና ጠንካሮች እንድንሆን ያደጋል። ጀፈር በመጽሐፏ በዚያም በዚህም ብለን ነገሮችን ስናደርግ የምቾት ቀጠናችንን እንደምናሰፋ ትገልጻለች። ሃይለኛ ዉሻ ሊበላው እያሯሯጠው ያለ ሰው የማይዘለው አጥር ይኖር ይሆን? ፍርሃትም በራሳችን ራሳችን ላይ ካሰመርናቸው ገደቦች በላይ እንድንሻገር በማስገደድ በመጨረሻም እድገትንና በራስ መተማመንን ያጎናጽፈናል።
ፍርሃት እንደባላንጣ
ፍርሃት ልክ ያለፈ ሲሆን ምንም ነገር መከወን የማንችል “ሽባ” ያደርገናል። አሁን ላይ መጨረስ ያለብንን ነገሮች በይደር ማቆዬት፣ ነገሮችን መሸሽና እድሎችን ማጣት ፍርሃትን የመጋፈጥ ችሎታ በማነስ የሚመጡ ናቸው። ውድቀትን መፍራት ሰዎች ህልማቸውን ማሳደድ እንዲያቆሙ ሲያደርግ፤ ተቃዉሞን መፍራት ደግሞ ትርጉምና ዋጋ ያላቸው ግንኙነቶችን መመስረት እንዳይችሉ ያሰናክላል።
ስር የሰደደ ፍርሃት ህይወትን በእጅጉ ወደሚያቃዉስ ጤናማ ያልሆነ ጥላቻ /ፎቢያ/ የጭንቀት በሽታ እና መሰል የስሜትና የጤና መዛባቶች ያመራሉ። እነዚህ ሁኔታዎች የዕለት ከዕለት ህይወታችንን እንኳን ማሸነፍ እንዳንችል አድርገው ሊያዳክሙን ይችላሉ። ለአንዳንዶች ፍርሃት ምርጫቸዉን የሚወስን እና አቅማቸውን የሚገድብ ከልክ ያለፈ ሃይል ይሆንባቸዋል።
ያልተገራ ፍርሃት ንዴትን፣ ቅሬታን፣ ድባቴን ይወልዳል። ያልታወቁ ነገሮችን መፍራት ብዙ ጊዜ ሳያረጋግጡ መፍረድን እና በማህበረሰብ ዉስጥ መከፋፈልን ይፈጥራል። ፍርሃት ሲነግስ አለመተማመን እና የጠላትነት መንፈስን በማዳበር በግለሰቦች እና በማህበረሰቦች መካከል መሰናክል ይሆናል።
ከፍርሃት ጋር መኖር
ፍርሃትን በትናንሽና መቆጣጠር በሚቻሉ እርምጃዎች መጋፈጥ ሰዎች ጭንቀት ፈጣሪ ለሆኑ ሁኔታዎች ያላቸዉን ተጋላጭነት ይቀንሳል። ቀስበቀስ የሚደረግ ጥረት ፍርሃትን ማሸነፍ እንደማይቻል ግዙፍ ነገር ሳይሆን ልንቆጣጠርው የምንችለው ነገር እንደሆነ እንድንረዳ ያግዘናል። የሚያስፈሩንን ነገሮች ደግመን ደጋግመን በመጋፈጥ ፍርሃት በምናደርጋቸው ነገሮች ላይ አዛዥ ሊሆን እንደማይገባ እንማራለን።
ኮግኒቲቭ ቢሄቪያራል ህክምና ምክንያት የለሽ ፍርሃትን እንድናርቅ እና ምክንያታዊ በሆኑ እይታዎች እንድንተካቸው ያግዛል። ይህ ዘዴ ሰዎች የአሉታዊ አስተሳሰብን መጋፈጥ እንዲችሉ፣ የተዛነፉ አስተሳሰቦችን እንዲለዩ እና ጤናማ የሆነ ለፍርሃት ምላሽ መስጫ መንገድን እንዲያዳብሩ ያስተምራል።
ጥንቃቄ እና ተመስጦ ለፍርሃት የምንሰጠዉን ምላሽ መቆጣጠር እንድንችል በማገዝ ዉጥረትን መቀነስ እና ያለንበትን አፍታ ልብ እንድንል ያስችላሉ። በጥልቀት የመተንፈስ ልምምዶች፣ ነገሮችን በዓይነ-ህሊና የማዬትና ራስን ዘና የማድረግ ልምምዶች ተጨባጭ በሆነ መልኩ የጭንቀት ደረጃን ዝቅ ማድረግ ይችላሉ። ፍርሃት እንደተፈጥሯዊ ተቀብለን ማሸነፊያ መንገድ በማበጀት ምርጫዎቻችንን እንዳይቆጣጠር ማድረግ ይቻላል። ከፍርሃታችን ጋር አብረን መኖርን ስንማር ሃስቦቻችንን እና ድርጊቶቻችንን መልሰን መቆጣጠር የምንችልበትን ስልጣን እናገኛለን።
ቤተሰብ፣ ጓደኞች እና ሃኪሞች ፍርሃት ላይ ስኬት የምንቀዳጅበትን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ጠንካራ የድጋፍ ስርዓት ፍርሃትን መጋፈጥና መርታት ቀላል እንዲሆን በማበረታታት፣ በመምከርና በመምራት ማገዝ ይችላል።
በአጠቃላይ ፍርሃት ከመሰረቱ ጥሩ ወይም መጥፎ አይደለም፤ በህይወታችን ያለዉን ሚና የሚወስነው እኛ ምላሽ የምንሰጥበት መንገድ ነው። “ዘ ጊፍት ኦፍ ፊር” የሚለው መጽሐፍ ፍርሃታችንን እንደህይወት ረዳታችን እምነት እንድንጥልበት ሲያስተምረን፤ “ፊል ዘ ፊር ኤንድ ዱ ኢት ኤኒዌይ” ደግሞ ከገደቦች ሁሉ በላይ አልፈን እንድሄድ ያበረታታናል። ዋናው ቁልፉ ሚዛናዊነት ነው፡ ፍርሃታችን የሚያጎናጽፈንን ጥበብ ተቀብለን እንዲቆጣጠረን ግን አለመፍቀድ።
የፍርሃትን ምንነት እንደ ጥንቃቄ ምልክት እንጂ እንደ “ቁም!’ ምልክትነት ባለመዉሰድ ህይወታችንን በድፍረት፣ በንቃትና በጽናት መምራት እንችላለን። ጥያቄው የሚሆነው ፍርሃትን ማስወገድ ሳይሆን የበለጠ ለተሟላ እና ጭንቀት የለሽ ለሆነ ህይወት መወጣጫ መሰላል ማድረግ ነው። ፍርሃታችንን ተረድተን በአግባቡ ስንቆጣጠረው እዉነተኛ አቅማችንን መረዳት እና በሰፋፊ ዕድሎች የተሞላ ህይወትን መምራት እንችላለን።
(በታደለ ሞላ)
በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም