በቱርክ ካያኮስ ደሴቶች ጥልቀት በሌለው የባሕር ዳርቻ በመዝናናት ላይ የነበረች የ55 ዓመት ካናዳዊት በአቅራቢያዋ የነበረን ዓሣ ነባሪ በሞባይል ስልኳ ፎቶ ግራፍ ለማንሳት ስትሞክር በመነከሷ እጅዎችዋን ማጣቷን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጹ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
ስድስት ጫማ ወይም ሁለት ሜትር ያክል ርዝመት በነበረው ዓሳ ነባሪ የተነከሰች ባለቤቱ ባሰማችው ጩኸት ተደናግጦ በፍጥነት ወደ ውኃው የገባው ባለቤቷም ዓሳ ነባሪውን በማስፈራራት ተጐጂዋን ወደ ባህር ዳርቻ ማውጣት ችሏል፡፡
በየካቲት ወር የመጀመሪያው ሳምንት ጥቃት የደረሰባትን ሴት በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል ማድረስ ቢቻልም እጆችዋን ከመቆረጥ ማዳን አለመቻላቸውን ነው ሀኪሞቹ ያስታወቁት፡፡
በቱርክ ካያኮስ እና የአካባቢው የባህር ዳርቻ ሀብቶች ልማት መምሪያ ሁነቱን አስመልክቶ ጐብኚዋ ወደ እንስሳው ቀርባ ምስል ለመቅረፅ “ሰልፊ” ለማንሳት ሳትሞከር እንዳልቀረች ነው ያስታወቀው፡፡ እንደ ቀጣናው ባለሙያዎች ገለፃ ጐብኚዋ የያዘችው የእጅ ስልክ በዓሳ ነባሪው ለመጠቃቷ መንስኤ ሆኗል፡፡
ጥቃት የደረሰባት ጐብኚ በባለቤቷ ወደ ዳርቻው መውጣት ብትችልም፣ በአቅራቢያው በነበሩ ጐብኚዎች የቆሰለ እጅዋን በጨርቅ ቢጠቀልሉም፣ ደሟ መፍሰስን ባለማቆሙ የተሻለ ህክምና ለማግኘት ወደ ካናዳ መላኳ ነው የተገለፀው፡፡
ስለሁኔታው ሙያዊ አስተያየት ከሰጡ መካከል የኒውዮርክ ዓሳ አጥማጅ እና ጥበቃ ባለሙያ ክሪስ ስቲፋን ተጠቂዋ የያዙት የስማርት የእጅ ስልክ ለደረሰባት ጥቃት መንስኤ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ ለዚህም ሻርኩ ረሀቡን ለማስታገስ ያለው ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ እና የእጅ ስልኳ እንደማጥመጃ ግራ ሊያጋባ እንደሚችልም ነው ግምታቸውን የሰጡት፡
በመጨረሻም የቀጣናው የባህርዳርቻ ሀብቶች ጥበቃ ባለሙያ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመቀነስ በባለሙያ በተፈቀዱ የተመረጡ ቦታዎች መዋኘት፣ ጨለማ ወይም በቂ ብርሃን በማያገኝ ቀጣናዎች አለመንቀሳቀስ እና ዓሳ ነባሪዎችን ከተመለከቱ ፈጥኖ መራቅ ተገቢ መሆኑን ነው ያሰመሩበት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም