“እግር ኳስ ነፃነት ነው!”

0
102

በሬጌ ሙዚቃው የሚታወቀውን የዚህን ዝነኛ ሰው ፎቶ  በጉግል በመተግበሪያ ብትፈልጉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ  ታገኛላችሁ፤ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞች በጥልቅ ስሜት መድረክ ላይ ሲዘፍን የሚያሳዩ ናቸው፤ የተወሰኑት ደግሞ በተለያየ ቦታ እና አጋጣሚ ሲዝናና የሚያሳዩ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ የሚወደውን እግር ኳስ ሲጫወት የሚያሳይ ፎቶም ትመለከታላችሁ። “እኔን ማወቅ ከፈለክ ከእኔ ጋር እግር ኳስ መጫወት አለብህ” በማለት በአንድ ወቅት ለአንድ ጋዜጠኛ ተናግሯል- ታላቁ የሬጌ የሙዚቃ ንጉሥ ሮበርት ኔስታ ማርሌይ ወይም ቦብ ማርሌይ።

ቦብ ማርሌይ የሬጌን ሙዚቃ በመጫወት እና ለሕዝብ በማድረስ ፈር ቀዳጅ ነው። የሙዚቃ ስልቱ በዓለም አቀፍ ዝና እና እውቅና እንዲያገኝ በማድረግም ቀዳሚው ሰው ነው። ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ የተወለደው ቦብ ህይወቱን ለማሸነፍ ሙዚቃ የጀመረው ገና በለጋ እድሜው ነው። በ1960ዎች መጨረሻ ወደ ሙዚቃው ዓለም መግባቱን የግል የታሪክ ማህደሩ አስነብቧል።

ቦብ ማርሌይ የሬጌ ሙዚቃ ንጉሥ ነው። በዘፈን ሰላምን፣ አንድነትን እና ፍቅርን ሰብኳል። በጊታሩም ጥልን አክሽፏል። ስለሰዎች እኩልነት እና መልካም አስተሳሰብ አብዝቶ በመሥራት ይታወቃል። ጭቆናን በሚተቹ እና አንድነትን በሚሰብኩ ዘፈኖች ዝናን እና ተወዳጅነትን አትርፏል።

ከሙዚቃው ባሻገር ለእግር ኳስ ስፖርት ጥልቅ ፍቅር እና ክህሎት እንደነበረው የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል። እንደ አፈ ታሪክ ከሚነገረው ጥሩ ስብዕናው ባሻገር ለእግር ኳስ የነበረውን  የተለየ ፍቅር ግን ብዙዎች አያውቁትም። በአንድ ወቅት አንድ ጋዜጠኛ ስለ አንተ እንዴት ማወቅ እችላለሁ? ብሎ ይጠይቀዋል። ታላቁ የሙዚቃ ሰው ቦብ ማርሌይ “እኔን ለማወቅ ከፈለክ አብረህኸኝ እግር ኳስ መጫወት ይኖርብሀል” የሚል ምላሽ እንደሰጠውም የግል ፎቶ ባለሙያው ዴኒስ ሞሪስ ተናግሯል።

የእግር ኳስ ጥማቱን ለመወጣትም በመኖሪያ ቤቱ እና ለኮንሰርት በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች ሁሉ እግር ኳስ ይጫወት ነበር። እንዲያውም ብዙ ጊዜ ከጊታር ይልቅ ኳስ ይዞ ይታይ እንደነበር መረጃዎች አስነብበዋል። የቦብ ማርሌይ ነፍስ ከሙዚቃ ብቻ ሳይሆን ከእግር ኳስ ጋርም የተሳሰረች ነበረች። በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ ምልልስ “መጀመሪያ ሙዚቃን ነው የምወደው፤ ቀጥሎ እግር ኳስን ነው፤ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ከሆንኩ መዝፈን አልችልም፤ የእግር ኳስ ስነ ምግባር አይፈቅድልህም” ሲል ለእግር ኳስ የነበረውን ክብር እና ፍቅር ሲናገር ተደምጧል።

የሬጌው ንጉሥ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች እንደነበረ የግል የታሪክ ማህደሩ ያስረዳል። ምንም እንኳ በአካል ብቃቱ ጠንካራ ነው ባይባልም አልሸነፍ ባይነቱ ግን አስደናቂ እንደነበር ያዩት ሁሉ መስክረውለታል። እግር ኳስን በላቀ ደረጃ መጫወት የሚያስችል አቅም እንደነበረው ይነገራል። ይሁን እንጂ የሬጌ ሙዚቃ አሸንፎት እግር ኳስን በፕሮፌሽናል ደረጃ አልተጫወተም።

የሰው ልጅ ከምንም በላይ ነፃነት ናፋቂ መሆኑን “እግር ኳስ ነፃነት ነው” (football is freedom) በሚለው ዝነኛ ንግግሩ እና ፍልስፍናው ያታወቃል። እግር ኳስ ስፖርትን በፈራረሱ የኪንግስተን ጎዳናዎች ላይ ነው የለመደው። ኳስ እንኳ ቢያጣ በየትኛውም የተድቦለቦለ ኳስ መሳይ ነገር ይጫወት ነበር ይሉታል። በቢራ መያዣ ቆርቆሮ እና በተለያዩ ፕላስቲክ ነገሮች ይጫወታል። እግር ኳስን ይጫወታል፤ ይመለከታልም።

ቦብ ማርሌይ እግር ኳስ ሲጫወት አስደናቂ ተሰጥኦ እንደነበረውም ይነገራል። የፎቶ ባለሙያው ዴኒስ ሞሪስ “ቦብን እግር ኳስ ሲጫወት ብዙ ፎቶ አላነሳሁትም፤ ምክንያቱም እርሱ ሲጫወት ማየት ስለሚያዝናናኝ ተመስጬ መመልከት ነበር የምወደው” ሲል ከቢቢሲ ስፖርት ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ተናግሯል።

ማርሌይ በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች፣ በእግር ኳስ ሜዳዎች እና ሙዚቃ በሚያቀናብርበት ስቲዲዮ ሳይቀር እግር ኳስ መጫወትን ያዘወትር ነበር። ከሙዚቃ ባንዱ ጋር ኮንሰርት በሚካሄድባቸው ቦታዎች ሁሉ እግር ኳስ ይጫወታል።

በ1980ዎች ለበጎ አድራጎት የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ለማድረግ ወደ ብራዚል ባቀኑበት ወቅት ከፔሌ እና ሌሎች ዝነኞች ጋር እግር ኳስ ተጫውቷል። በወቅቱ ድንቅ ክህሎቱን የተመለከቱት የሳንቶስ ክለብ የቡድን አባላት አድናቆታቸውን ሰጥተውታል። የብራዚሉ ክለብ ሳንቶስ እና የቀድሞ ተጫዋቹ ፔሌ ደጋፊ እና አድናቂ እንደነበረም ይነገራል። ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ደግሞ የሰሜን ለንደኑ ክለብ ቶትንሀም ሆትስፐርስ ደጋፊ ነበር። እግር ኳስ ሲጫወት የነፃነት ስሜት እንደሚሰማው  ይገልጻል።

ቢቢሲ ስፖርት ሁለት የቦብ ማርሌይን የቅርብ ጓደኞች እና የግል የፎቶ ባለሙያውን ዴኒስ ሞሪስ ምን ያህል እግር ኳስን እንደሚወድ አነጋግሬአለሁ ብሏል። በህይወት ዘመኑ ከእግር ኳስ ርቆ አያውቅም። እግር ኳስን አብዝቶ በመውደዱ በጃማይካ በሚገኙ የተለያዩ ክለቦችን ጨዋታ ይመለከታል፤ ይደግፋል፤ አብሮም ይጫወታል።

ባገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ እግር ኳስ ይጫወት ነበር። ማራኪ እና ውበት ያለው እግር ኳስ ጥሩ ሙዚቃ ለመሥራት እንደሚያግዘውም በተደጋጋሚ ሲናገር መደመጡን መረጃዎች አስነብበዋል፡፡ እግር ኳስ አዕምሮውን ነፃ አድርጎ ከፈጣሪው ጋር እንዲነጋገር የሚያስችለው መሳሪያ እንደነበረም ተናግሯል። “ምድራዊ ከሆኑ ሀብቶቼ መካከል እግር ኳስ አንዱ ነው” ሲልም በተዳጋጋሚ ይናገር ነበር።

የእርሱ የእግር ኳስ ፍቅር ወደ ቤተሰቦቹም ተጋብቷል።በ2008 እ.አ.አ የጃማይካ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በገንዘብ እጥረት ምክንያት መፍረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን ቡድኑ ከፈረሰ ከዐስር ዓመታት በኋላ የቦብ ማርሌይ ልጅ የሆነችው ሴዴላ ማርሌይ ለብሄራዊ ቡድኑ ድጋፍ በማድረግ ድጋሚ ተቋቁሟል። ብሄራዊ ቡድኑ ፈረንሳይ ባስተናገደችው እ.አ.አ በ2018 የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፍ ችሏል።

ከቦብ ማርሌይ ዝነኛ ዘፈኖች መካከል አንዱ የሆነው ሦስት ትናንሽ ወፎች (Three little Birds) ለኔዘርላንድሱ ክለብ አያክስ አምስተርዳም ደጋፊዎች ብሄራዊ መዝሙር ሆኖ እያገለገለ ነው።  እ.አ.አ በ2018 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ውድድር ካይ ማኒ ማርሌይ በዩሀን ክራይፍ አሬና ስቴዲየም ይህን የአባቱን ዘፈን የመድረኩ ማድመቂያ ካደረገው በኋላ  አሁን ድረስ የደጋፊዎች መዝሙር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት  የሆነውን  ጃማይካዊውን ሙዚቀኛ  ቦብ ማርሌይ በየዓመቱ ይካቲት ወር በሚከበረው የጥቁር ሕዝቦች ቀን ( Black history month) እኛም እንዲህ ዘክረነዋል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here