አፍሪካውያን በአውሮፓ…

0
116

የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሕዝብ በላይ የሚኖርባት አህጉራችን አፍሪካ አስደናቂ ባህል እና የተፈጥሮ ሀብት እንዳላት ብዙዎች ይስማሙበታል። ነገር ግን በዚህ ብቻ ሳይሆን በታላላቅ የእግር ኳስ ባለተሰጥኦዎች  ጭምርም መባረኳን  ነው የኒውስ ሴንትራል መረጃ የሚነግረን።

አሁን ላይ በአምስቱ ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ከ140 በላይ አፍሪካውያን ተጫዋቾች እንዳሉ የካፍ ኦንላይን መረጃ ያስነብባል። አፍሪካውያን ተጫዋቾች በአውሮፓ ምድር ቁጥራቸው ብቻ ሳይሆን በላቀ ደረጃ ለመጫወት የሚያስችላቸው ጥራትም ከፍ ብሏል። እንደ ቀደሙት ጊዜያት አፍሪካውያን ተጫዋቾች በየክለቦች የመሰለፍ እድል ለማግኘት እና ተመራጭ ለመሆን የሚታገሉበት የጨለማው ዘመን ማብቃቱን መረጃው ያስነብባል።

በያዝነው የውድድር ዘመን በአውሮፓ አምስቱ ታላላቅ ሊጎች አፍሪካውያን ተጫዋቾች ብዙ ዋጋ እንዳላቸው እያሳዩ ነው። ግቦችን እያስቆጠሩ፤ ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችተው እያቀበሉ፤ የቡድናቸውን ሚዛንም እየጠበቁ ነው። ባለፉት ዐስርት ዓመታት  የአፍሪካውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች ጥራት እና ቁጥር በአውሮፓ እግር ኳስ መጨመር በዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን በአፍሪካ እግረኳስ እድገት ዙሪያ የተጠናው ጥናት ያመለክታል።

አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ክለቦች በገንዘብ፣ በሊግ ጥራት እና ጥንካሬ ከአውሮፓ ሊጎች ጋር ሲነጻጸር ደካማ በመሆኑ ባለተሰጥኦ ኮከቦች በየጊዜው ይኮበልላሉ። እነዚሀ  ተጫዋቾቸም ለአውሮፓ እግር ኳስ እድገት ዋነኛ መሳሪያ ሆነዋል። በየሊጉ በአሰልጣኞች፣ በክለቦች እና በደጋፊዎች እምነት የሚጣልባቸው መሆን ችለዋል።

በ2024/25 የውድድር ዘመን በሁሉም የሜዳ ክፍል ትንፋሽን የሚያስውጥ እና ደምን የሚያሞቅ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ አፍሪካውያን የእግር ኳስ ኮከቦች ብዙ ናቸው። ክብረወሰን እየሰበሩ ካሉ ግብ አነፍናፊዎች እስከ ፈጣሪ አማካዮች፣ እንደ አለት ጠንካራ ከሆኑ ተከላካዮች እስከ ድንቅ ግብ ጠባቂዎች፤ ዘንድሮ ምርጥ የውድድር ጊዜ እያሳለፉ ናቸው። በጠንካራ ሥራ እና በቁርጠኝነት የዳበረው ይህ ክህሎታቸው በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም እግር ኳስም ተጽእኖ እየፈጠረ ነው። ከእነዚህ መካከል አንዱ ግብጻዊው ሞሀመድ ሳላህ ነው።

ሳላህ በእግር ኳስ ታሪክ ከምርጥ የክንፍ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። በአጨራረሱ፣ ኳስ በመንዳት ክህሎቱ፣ በፍጥነቱ እና በጨዋታ አቀጣጣይነቱ በትውልዱ ካሉ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ያደርገዋል። ከቀዮቹ ጋር የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን አሳክቷል። በግሉ ደግሞ ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ መመረጡ አይዘነጋም። አሁን ላይም የፕላኔታችን ምርጡ አፍሪካዊ ተጫዋች ስለመሆኑ አያጠያይቅም።

የ32 ዓመቱ አጥቂ በአንፊልድ ሮድ የመጨረሻው ዓመት ላይ ይገኛል። በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ከመርሲሳይዱ ክለብ ጋር እንደሚለያይ እየተነገረ ያለው ሳላህ ዘንድሮ የእርሱን ያህል የተሳካ ጊዜ እያሳለፈ ያለ ተጫዋች ማግኘት ይከብዳል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ በ28 ጨዋታዎች 25 ግቦችን አስቆጥሯል። 17 ግብ የሆኑ ኳሶችን ደግሞ ለቡድን ጓደኞቹ አቀብሏል። የውድድር ዘመኑ ገና ሳይጠናቀቅ እስካሁን በ42 ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል። ይህ ማለት በየጨዋታው አንድ ግብ ማስቆጠሩን ነው መረጃው የሚያስረዳው። በእርግጥም ግብጻዊው ኮከብ የአርኔ ስሎት ዋነኛው የማጥቂያ መሳሪያ መሆኑ አይካድም።

ሳላህ ከገና በፊት ዐስር ግብ በማስቆጠር እና ዐስር ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ በማቀበል ዘንድሮ ቀዳሚ ተጫዋች ሆኗል። ሳላህ አሁን ላይ የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በ25 ግቦች እያመራ ይገኛል። ከተፎካካሪዎቹ እርሊንግ ሀላንድ በአምስት እና በአሌክሳስንደር ኢሳቅ በስድስት ግቦች ልዩነት ይበልጣል። ታዲያ ዘንድሮ የሊቨርፑል ስኬት የሳላህ አስደናቂ ብቃት ስለመሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ።

ጋናዊው አማካይ ቶማስ ፓርቲ  በኤምሬትስ ብዙ ያልተዘመረለት አፍሪካዊ ኮከብ ነው። የ33 ዓመቱ የመሀል ሜዳ ሰው በመከላከል እና የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ በዚህ ዓመት ድንቅ ሥራ እየሠራ ይገኛል። የሰሜን ለንደኑ ክለብ የፕሪሚየር ሊጉ ተፎካካሪ እንዲሆን ካስቻሉት ተጫዋቾች መካከልም ከግንባር ቀደሞች ይጠቀሳል። አማካዩ ዘንድሮ ድንቅ አቋሙን በማሳየት አርሴናል አሁን ላለበት ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ማንቸስተር ዩናይትድ በዚህ ዓመት አዲስ አሰልጣኝ ቢቀጥርም ሜዳ ላይ ግን የሚታይ ለውጥ አላመጣም። የቀድሞው ኃያል ክለብ ዘንድሮም አስቸጋሪ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ይገኛል። ምንም እንኳ እንደ ቡድን ክለቡ ጥሩ ባይሆንም ቡሩኖ ፈርናንዴዝ፣ አንድሪ ኦናና እና አማድ ዲያሎን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ጥሩ የውድድር ዘመን እያሳለፉ ነው።

ካሜሮናዊው ግብ ጠባቂ አንድሪ ኦናና ዘንድሮም ልክ እንደ አምናው ድንቅ አቋም እያሳየ ነው። ኦናና የመጀመሪያው የሜዳ ክፍል በራስ መተማመኑ ከፍ እንዲል ዋነኛው የጀርባ አጥንት እንደሆነ ይነገራል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ግብ ጠባቂው በስድስት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት ከሜዳ መውጣቱም አይዘነጋም። በየጨዋታው የሚያድናቸው ኳሶች ምናልባት ከግብ ጋር ተገናኝተው ቢሆን ኖሮ የላንክሻየሩ ክለብ ትልቅ የመውረድ አደጋ ይጋረጥበት ነበር። ታዲያ የኒውስ ሴንትራል መረጃ ዘንድሮ በአውሮፓ ሊጎች ድንቅ አቋማቸውን እያሳዩ ካሉ አፍሪካውያን ተጫዋቾች ኦናና አንዱ መሆኑን ዘግቦታል።

ሌላኛው የማንቸስተር ዩናይትዱ ተጫዋች አማድ ዲያሎም በዚህ ዓመት ድንቅ እንቅስቃሴ እያደረጉ ካሉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ኮትዲቫራዊው የ22 ዓመቱ የክንፍ ተጫዋች በኦልትራፎርድ በግሉ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ነው። እ.አ.አ በ2019/20 በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት የደረሰው አማድ በፕሪሚየር ሊግ ብቻ በ22 ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን አስቆጥሯል።

በተመሳሳይ  ስድስት ግብ የሆኑ ኳሶችን ደግሞ ለቡድን ጓደኞቹ አቀብሏል። ማንቸስተር ዩናይትድ ከሳውዝአምፕተን ጋር በነበረው የፕሪሚየር ሊግ መርሀግብር በ12 ደቂቃ ውስጥ ሀትሪክ መሥራቱ የሚታወስ ነው። ወጣቱ ኮከብ በመጪው ዘመን ለማንቸስተር ዩናይትድ ብቻ ሳይሆን ለኮትዲቫርም ወሳኝ ተጫዋች እንደሚሆን የዘንድሮው ድንቅ አቋሙ ያመለክታል።

ጊኒያዊው አጥቂ ሰሪሁ ጉራይሴ ዘንድሮም በጀርመኑ ክለብ ቦርሲያ ዶርትመንድ ቤት ምርጥ አቋሙን እያሳየ ነው። የ28 ዓመቱ አጥቂ አምና ባየርሊቨርኩሰን  የቡንደስ ሊጋ ዋንጫ ሲያነሳ ትልቁን ሚና ከተጫወቱት መካከል ዋነኛው ነው። ጉራይሴ ዘንድሮ በ21 ጨዋታዎች 13 ግቦችን ሲያስቆጥር ሦስት ግብ የሆኑ ኳሶችንም ለቡድን ጓደኞቹ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ምንም እንኳ ቦርሲያ ዶርትመንድ ጥሩ የማይባል ጊዜ እያሳለፈ ቢሆንም ጊኒያዊው አጥቂ ግን በግሉ የተሳካ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ነው።

አሸራፍ ሀኪሚ በዓለማችን ካሉ ምርጥ የቀኝ ተመላላሾች መካከል በቀዳሚነት ይቀመጣል። ሞሮኳዊው ተከላካይ በዚህ ዓመት እስካሁን በ23 ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ሲያስቆጥር ሰባት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ሀኪሚ በማጥቃቱ እና በመከላከሉ ከተዋጣላቸው ጥቂት ኮከቦች መካከል ቀዳሚው ነው። ተጫዋቹ ሁለገብ መሆኑ ለፓሪሱ ሀብታም ክለብ ፓሪሰ ዥርሜን እጅግ አስፈላጊው ተጫዋች ነው። ሞሮኳዊው ተጫዋች ልክ እንደ ባለፉት ዓመታት ዘንድሮም አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል።

ናይጀሪያዊው የባየርሊቨርኩሰኑ አጥቂ ቪክተር ቦኒፌስ፣ ሴኔጋላዊው የቸልሲው አጥቂ ኒኮላስ ጃክሰን፣ ጋናዊው የዌስትሀሙ አማካይ ሙሀመድ ክዱስ እና የመሳሰሉት በዚህ ዓመት በአውሮፓ ምድር እየደመቁ ያሉ አፍሪካዊ የእግር ኳስ ኮከቦች ናቸው።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here