ወረርሽኙን ለመከላከል …

0
108

“ቫይብሪዮ ኮሌሬ (Vibrio Cholerae) በተሰኘ የባክቴሪያ ዝርያ ይከሰታል፤ አጣዳፊ ትውከትን  እና ተቅማጥ  በማስከተል  ሰውነትን ለድርቀት በመዳረግ በአጭር ጊዜ የሚገድል አደገኛ በሽታ ነው – ኮሌራ፡፡ ይሁን እንጂ ኮሌራን በቀላል ዘዴ እንዳይከሰት ከማድረግ በተጨማሪ በሺታው ቢከሰት እንኳ በቶሎ በሕክምና ማስቀረት ይቻላል” ሲል ሙያዊ ትንታኔን ያስነበበው ሜዲ ከቨርስ (www.medicovers.com) የተሰኘው ድረ ገጽ ነው፡፡

ድረ ገጹ እንዳስነበበው በበሽታው የተጠቃ ሰው ከባድ እና ቀላል  ምልክቶችን    የሚያሳይ ሲሆን  በአብዛኛው  እስከ   አምስት  ቀናት    ይታያል፡፡ አጣዳፊ  ትውከት እና ተቅማጥ እንዲሁም ድርቀት ዋና ዋናዎቹ ምልክቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ምልክቶች ታዲያ የሰውነትን ፈሳሽ በማሳጣት፣ በሽታ የመከላከል አቅምን በማዳከም እንዲሁም ሕዋሳት መደበኛ  ሥራቸውን እንዳያከናውኑ በማድረግ ታማሚውን በአጭር ጊዜ ሕይወቱን ይነጥቁታል፡፡

በሽታው በሀገራችንም በተለያዩ ጊዜያት በወረርሽኝ መልክ ተከስቷል፤ በቅርብ ዓመታትም ተከስቶ የዜጎችን ሕይወት ነጥቋል፡፡ ለአብነት  በአማራ ክልል በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም ወረርሽኙ ተከስቶ የዜጎችን ሕይወት እንደነጠቀ የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡ ይህን ተከትሎ በተሠራው ቅንጅታዊ ተግባር ወረርሽኙን መከላከል ተችሎ እንደነበርም የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

ይሁን እንጂ በቅርቡም በምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢ መከሰቱ ተረጋግጧል፤ ወረርሽኙን በተመለከተም ባለድርሻ አካላትን  ያካተተ ምክክር በባሕር ዳር ከተማ ከሰሞኑ ተካሂዷል፡፡ በወቅቱም  በአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ባለሙያ  አቶ ጥሩነህ ገነት   በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት ወረርሽኞች መከሰታቸውን ጠቁመዋል:: ከእነዚህ ውስጥም በአጣዳፊነቱ የከፋው የኮሌራ ወረርሽኝ መሆኑን በጽሑፉ መግቢያ ላይ ያሳናቸውን ምልክቶች በምክንያትነት አንስተው አስገንዝበዋል::

ወረርሽኙ በዋናነት በንጽሕና ጉድለት፣ በተበከለ ምግብ፣ በመጸዳጃ ቤት አጠቃቀም ክፍተት እና በመሰል ምክንያቶች ይከሰታል፤ ንክኪ ደግሞ የበሺታው አምጪ ባክቴሪያ ከበሽተኛ ወደ ጤነኛ ዋና መተላለፊያ መንገዱ ነው፡፡

ሊቀ አእላፍ አባ ኀይለ ማርያም ያሳይ የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ሥብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ናቸው፤ ከሰሞኑ በባሕር ዳር በነበረዉ ምክክር ነበር ያገኘናቸው፤ በአባቶች በኩል በአብያተ ክርስቲያናት እና ምዕመኑ በሚገኝባቸው ሁሉ የግንዛቤ ትምህርት እየተሰጠ ነው:: ይሁን እንጂ በቂ ውኃ አለመኖር እና የመጸዳጃ ቤት እጥረት በሽታው እንዲከሰት ያደረጉ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል::

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ሊቀ አእላፍ አባ ኀይለማርያም ያነሷቸውን ገፊ ምክንያቶች ተጋርተዋል፡፡ በዚህ ችግር ውስጥም ተሁኖ ታዲያ በተለይ የሃይማኖት አባቶች ያደረጉትን መልካም ተግባር (ግንዛቤ መፍጠርን ጨምሮ) አመስግነዋል፤ “ይህ ባይሆን ኖሮ ወረርሽኙ ይከፋ ነበር” ሲሉም ነው አባቶች ስላደረጉት በጎ ተግባር የመሰከሩት::

ሊቀ አእላፍ አባ ኀይለማርያም አክለውም ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ነግረውናል፤ ከእነዚህ ተግባራት መካከል ደግሞ ፕሮጀክት በመቅረጽ በቂ የውኃ እና የመጸዳጃ ቤት አቅርቦት ችግር እንዲፈታ እየተደረገ ያለውን ሥራ አንስተዋል:: ይሁን እንጂ በተለይ የመንግሥት አካላት ከመናገር ባለፈ በተግባር የመፈጸም ውስንነት እንዳለባቸው ነው የጠቀሱት፤ “መናገር እንደ መተግበር አያስቸግርም!” በማለት የተግባር ምላሽ እንዲሰጥም ነው አጽንኦት ሰጥተው ያሳሰቡት::

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በሽታውን ለመከላከል እንቅፋት ሆነዋል በሚል የተነሱትን ችግሮች ተጋርተዋል፤ ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት የተግባር ምላሽ እየተሰጠ ስለ መሆኑም አስታውቀዋል:: ዋነኛ የበሽታው ምንጭ እና አባባሽ ምክንያቶችን መለየትና ለባለሙያዎች ስለ ወረርሽኙ ቅኝት እና ምላሽ ሥልጠና መሰጠቱ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወኪሎች እና ሌሎች ድርጅቶች ወደ ቦታው እንዲሄዱ በማድረግ ፈጣን ምላሽ መሰጠቱ ደግሞ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው::

ወረርሽኙን የመከላከል ሥራው ቀጣይነትን እንደሚጠይቅ ያነሱት አቶ በላይ በአጠቃለይ በተከናወነው የቅንጅት ሥራ ወረርሽኙን መግታት መቻሉን አስታውቀዋል::

መጸዳጃ ቤትን በአግባቡ መጠቀም፣ ከመጸዳጃ ቤት መልስ ምግብን ከመንካት፣ ከማዘጋጀት እና ከመመገብ በፊት እጅን በሳሙና  መታጠብ፣ ውኃን አፍልቶ ወይም አክሞ መጠቀም፣ ምግብን በሚገባ አብስሎ እና በትኩስነቱ መጠቀም እና የአካባቢ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ በሺታውን ለመከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎች ናቸው::

ከዚህ በተጨማሪም የበሽታው ምልክት የታየበትን ሰው ፈጥኖ ወደ ሕክምና ቦታ መውሰድ፣ ከታማሚው ከሚወጣ ፈሳሽ ጋር ንክኪ ካላቸው ዕቃዎች እና ቦታዎች መራቅ ወይም በአግባቡ አጽድቶ መጠቀም በሽታውን ለመከላል መሠረታዊ ተግባራት መሆናቸውን ከሜዲ ከቨርስ (www.medicovers.com) ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያስገነዝባል::

የኮሌራ ወረርሽኝን መከላከል ላይ ትኩረቱን ባደረገው ምክክር የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አበበ ተምትሜ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር  በክልሉ የኮሌራ ሥጋት ባለባቸው 44 ወረዳዎች ባለሙያዎች እንዲሰለጥኑ ተደርጓል:: የሕክምና ቁሶችንም እያቀረቡ ነው:: ማኅበረሰቡም መከላከል ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ግንዛቤ እየተፈጠራ ሥራ እየተሠራ ነው:: ከዚህ በተጨማሪም የወረርሽኙ ስጋት ባለበት አካባቢ የመጸዳጃ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል::

ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ነጥብ ሦስት እስከ አራት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በየዓመቱ በኮሌራ ይያዛሉ፤ ከ21 ሺህ እስከ 143 ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ  በበሺታው ይሞታሉ::

(ጌትሽ ሀይሌ)

በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here