“ጋሸና ያቺን ሰዓት እና ሌሎች ታሪኮች” መጽሐፍ በባለሙያዎች ዕይታ

0
176

በዓለም አሥራ ስምንት ሀገራት ብቻ የራሳቸው ፊደል አላቸው፤ ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን በአፍሪካ አህጉር ደግሞ ብቸኛዋ ሀገር ናት። የሀገራችን ነገር ግን ከሁሉም ሀገራት ይልቃል። ነገሩ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ!” በሚለው ኢትዮጵያዊ ብሂል የተደገፈ አይደለም። በአርበኞቻችን መስዋዕትነት በቅኝ ያልተገዛች መሆኗን ነው ለአስረጂነት በኩራት የምንጠቅሰው።

የዛሬን አያድርገውና ከሺዎች ዓመታት በፊት ከዓለማችን አምስት ኃያላን ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ በቀዳሚነት ትጠቀስ ነበር። ይህን ሃቅ ደግሞ በጣና ገዳማት ውስጥ የሚገኙ ትናንትናችንን የሚናገሩትን ቅርሶች እና የአክሱም ሃውልትን ጨምሮ በርካታ አብነቶች ህያው ምስክር ሆነው ይናገራሉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሺዎች ዓመታት የሀገረ መንግሥት  ባለታሪኳ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የነበሩ ነገሥታት አሻራቸውን አስቀምጠውላት አልፈዋል። አሻራዎቹን ደግሞ በራሷ ፊደል ሰንዳ ነው ለትውልዱ የምታወርሰው።

ድርሳናት እንደሚናገሩት ነገሥታት የየዕለት ተግባሮቻቸውን በየዕለቱ ይሰንዱ ነበር። ይህም ‘ዜና መዋዕል’ በሚል መጠሪያ በጸሐፊዎቻቸው በኩል ነበር የሚሰነደው።

ይሁን እንጂ “ይህ ታሪክ ነጋሪ፣ ቀጣዩ ትውልድ ስለ ሀገሩ ሙሉ ታሪክ እንዲኖረው የሚያስችለው የሥነ ጽሑፍ አሻራ በአሁኑ ወቅት እየተቀየረ ነው” ሲሉ በቁጭት የነገሩን በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ መምህር አንተነህ አወቀ (ዶ/ር) ናቸው። የምሁሩን ሐሳብ ያነሳነው ቁጭታቸውን ለማስተጋባት ብቻ ሳይሆን ለቁጭታቸው ማስታገሻ ነው ብለው ሙያዊ ሐሳብ ስላነሱበት መጽሐፍ ለማንሳት ነው።

መጽሐፉ “ጋሸና ያቺን ሰዓት እና ሌሎች ታሪኮች” ይሰኛል። ደራሲው ደግሞ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ባልደረባ ጋዜጠኛ እና ደራሲ እሱባለው ይርጋ ነው። በሰሜኑ ጦርነት በተለያዩ ግንባሮች ዘገባዎችን አድርሷል፤ ይህም የጦርነቱን ብዙ መልኮች እንዲመለከት አድርጎታል። ትኩረቱን በሰሜኑ ጦርነት ላይ ያደረገው የመጽሐፉ  ምልከታዎች ከገጠመኞች ጋር ተዋዝተው የቀረቡበት ነው።

በመጽሐፉ ላይ ሙያዊ ሂስ የሰጡት ዶክተር አንተነህ ሥነ ጽሑፍን በገጠመኝ መልክ ማቅረብ ብዙም ማሸት የማይፈልግ፣ የታየውን እና የታወቀውን ለአንባቢ ተደራሽ የሚደረግበት “ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ይህን መሰል አስፈላጊ የጽሑፍ ስልት እያጣነው መጥተናል፤  ከዚህ አኳያ ጋሸና ያቺን ሰዓት እና ሌሎች ታሪኮች መጽሐፍ አስተማሪነቱ የጎላ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ነገሥታት የዕለት ተግባሮቻቸውን በጸኀፊዎቻቸው አማካኝነት እንዲጻፍ ማድረጋቸው የሀገራችንን ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል፤ ትክክለኛ ታሪክን በማስገንዘብ ያልተገባ ትርክትን ያስወግዳል። ነገሩም “የተጻፈ ይወረሳል …” በመሆኑ ተሰንዶ መቀመጡ አበርክቶው ከፍ ያለ ነው።

የአሁኑ ትውልድ የተሰነዱ ታሪኮችን በመዘንጋት፣ አፈ ንግርት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሆኗል፤ የተዛባ ትርክት ለዓመታት መቀንቀኑም ትውልዱን በርዞታል። ይህ መሆኑ ታዲያ ታላቋን ስዕል ኢትዮጵያን በመዘንጋት ሁሉም በየብሔሩ እንዲታጠር አድርጎታል።

ጋሸና ያቺን ሰዓት እና ሌሎች ታሪኮች መጽሐፍ ታዲያ የአሁኑን ክስተት የነገው ትውልድ እውነትን ከምንጩ እንዲገነዘብ የጎላ አበርክቶ አለው፤ ዶክተር አንተነህ እንዳብራሩት ደራሲው በጦር አውደ ግንባሮች የታዘበውን እና የተመለከተውን ለአንባቢ፣ አድማጭ እና ተመልካች ከቀረበው ባሻገር ሰፋ አድርጎ ለማቅረብ አስችሎታል። ይህ ደግሞ የታሪክ ምንጭ ይሆናል። በመሆኑም በተለይ ነገ ላይ የዛሬን ታሪክ ለመሰነድ መጽሐፉ አበርክቶው የጎላ መሆኑን ነው ያብራሩት።

ምሁሩ ሙያዊ ዕይታቸውን ከትዝብታቸው ጋር እያዋዙ እንደሚከተለው ቀጠሉልን፤ የአሁኑ ትውልድ የማንበብ ባሕሉ በእጅጉ ዝቅተኛ ነው። የቴክኖሎጂው መራቀቅም የራሱ ድርሻ አለው። እንደዚህ ዓይነት መጻሕፍት ደግሞ የአንባቢን ቀልብ የሚስቡ ናቸው። ታሪኮቹ የተዋቀሩበት መንገድ እና በምልከታ መዳበራቸው በአንባቢ ዘንድ ተመራጭ ያደርገዋል።

ለሁለት ዓመታት ያህል ተካሂዶ እጅግ ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትን አስከትሎ በድርድር የተቋጨው የሰሜኑ ጦርነት የሀገራችን የታሪክ አካል ሆኖ ይቀጥላል።  ጋሸና ያቺን ሰዓት እና ሌሎች ታሪኮች መጽሐፍ ታዲያ “የነገው ትውልድ እውነታውን ከምንጩ እንዲረዳ የሚያደርግ፣ በነገው ትውልድ ዘንድ የተዛባ ትርክት እንዳይፈጠር የሚያደርግ ስጦታ ነው” ብለዋል የቋንቋና ሥ ነጽሑፍ ምሁሩ ዶክተር አንተነህ።

ከባሕል አኳያ ሙያዊ ሐሳብ የሰጡት ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የባሕል ጥናት መምህር ሰሎሞን ተሾመ (ዶ/ር) ናቸው። መጽሐፉ ለታሪክ እና ለባሕል ጥናት ግብዓት ከመሆን ባለፈ ለተማሪዎችም የማሟያ ጽሁፍ ማጣቀሻ እንደሚሆን ማሳያዎችን እያጣቀሱ አስገንዝበዋል።

በመጽሐፉ እንደተብራራው በጦርነቱ (ውድመቱ እንዳለ ሆኖ) ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችም በተግባር የታዩበት ነበር፤ መጽሀፉ ለታሪክ እና ባህል ጥናት ግብአት ነው። መጽሐፉ “እውነት ከምንጩ የቀረበበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል” ያሉት ምሁሩ አስተማሪነቱም መልከ ብዙ ስለመሆኑ ይናገራሉ፤ ለማሳያም ጦርነቱ ካደረሰው ውድመት ባሻገር መተዛዘኑ፣ መተሳሰቡ፣ በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ባሕሎች የተገለጹበት እንደሆነ አንስተዋል።

መጽሐፉ የተዋቀረበት መንገድ እና በውስጡ ያካተታቸው ገጠመኞች፣ ማኅበረሰባዊ ትውፊቶች “የባሕል መስታዎቶች ናቸው” ሲሉ ነው ያብራሯቸው። በጦርነቱ ስለደረሰው ነገር በሌላ አካባቢ ላለው በብዙኃን መገናኛዎች ከቀረበው ባለፈ ከመስታዎት ጀርባ ያሉ ነገሮችን፣ ቁስልን፣ ሕመምን ሁሉ ምናባዊ ስዕልን የሚከስት ነው።

ምሁሩ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር የምንታወቅባቸው ባሕሎቻችን እየተዘነጉ ነው፤ ይህም ለከፋ ነገር እየዳረገን ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ደግሞ የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት ግጭቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ ታዲያ እነዚህን ሁሉ በመቃኘት፣ በጦር ግንባር የታዘበውን ምልከታውንም በማካተት “እኔነት እና እናንተነት እንዴት ለከፋ ነገር እንደዳረገን ያሳየበት ነው” ብለውታል፡፡

ሚዛናዊነትን ጠብቆ የተጻፈ ስለመሆኑ በማንሳትም የፖለቲካ ባሕላችንን በሚገባ በማሳየት እንዴት ለውድቀት እንደዳረገን የተገለጸበት ነውም ብለዋል። ምሁሩ “እንደ አጠቃላይ” ሲሉ ሙያዊ ዕይታቸውን ማብራራታቸውን ቀጥለው “የአማራ ደግነት፣ እንግዳ ተቀባትነት፣ ከዚያም አለፍ ሲል የእርስ በእርስ መገዳደል አዙሪት መቆም እንዳለበት በማሳያ የቀረበበት ነው” ሲሉ ነው ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት።

በመጨረሻም የመጽሐፉን  ጋዜጠኛ እና ደራሲ እሱባለው ይርጋን ሐሳቡን እንዲያጋራን ጠይቀነው የሚከተለውም አጋርቶናል፤ ትክክለኛነት (Accuracy) በጋዜጠኝነት ሙያ ወርቃማው ሕግ ነው፡፡ በጦር ግንባር ቆይታ ምልከታዎችን፣ ክስተቶችን እና ገጠመኞችን ሚዛናቸውን በመጠበቅ ለአንባቢ እንዲደርሱ ሆኗል። የጦርነት ውሎ ዘገባ የጋዜጠኞች የዘገባ ልኬት (ከፍታ) መሆኑን ያነሳው ደራሲው ይህን ዕድል በማግኘቱም “ራሴን እንደ ዕድለኛ እቆጥረዋለሁ። ይህን ዕድል ለሰጠኝ አሚኮ ምስጋናዬ የላቀ ነው” ብሏል። ሌሎችም መሰል አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ነው መልዕክት ያስተላለፈው።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here