የዓየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው የሙቀት መጨመር በመጪው ክፍለ ዘመን መባቻ በግሪንላንድ እና አርክቲክ (የሰሜን ዋልታ ንፍቀ ክበብ) ግግር በረዶ መቅለጥን መቀልበስ ወደማይቻልበት ጫፍ ሊያመራ እንደሚችል ላይቭ ሳይንስ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል::
በአሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት የሚገኘው ናሽናል ስኖው ኤንድ አይስ ዳታ ሴንተር (NISIDC) ይፋ ባደረገው መረጃ ከሁለቱ የበረዶ ንጣፍ መገኛ ቀጣናዎች ማለትም ግሪንላንድ እና አርክቲክ በ2021 እ.አ.አ በተደረገ ጥናት ስድስት ነጥብ ሦስት ትሪሊዬን ሜትሪክቶን በረዶን አጥተዋል:: በዚሁ ስሌት በትንበያው መሰረት የሙቀት መጨመርም አሁን ካለበት ደረጃ አንድ ነጥብ 47 ሴልሺየስ በ2100 እ.አ.አ ሦስት ነጥብ አራት ሴልሽየስ ሊደርስ እንዲሚችል ነው የማእከሉ መረጃ ያመላከተው::
የግግር በረዶ ክምችት ባለባቸው የሰሜን ንፍቀ ክበብ ማለትም የግሪንላንድ እና አርክቲክ ቀጣናዎች ግግር በረዶ ቀልጦ የመጨረሻ ጫፍ የሚደርስበትን ጊዜ ለመገንዘብ የዓየር ንብረት ምስለ ምርምር ንድፍ ቀርፀዋል::ይህ ማለት በበረዶ መከማቸት እና በመቅለጥ ሂደት መካከል ያለውን የተለያየ የሙቀት መጠን መሰረት ያደረገ ምስለ ምርምር መሆኑን ልብ ይሏል::
ባለፉት አስርት ዓመታት እንደ አውሮፓ ባሉ በርካታ ኗሪዎች ባሉባቸው ቀጣናዎች የበረዶ መሟሟት ፍጥነቱ ከመቼውም በላይ ጨምሮ ተስተውሏል:: ከ2000 እስከ 2023 እ.አ.አ ባሉት ዓመታትም ግሪንላንድ እና አንታርክቲክን ሳይጨምር ከጠቅላላው የበረዶ ክምችት አምስት በመቶ የሚሆነውን አጥቷል::
በአውሮፓ አህጉር ከ2000 እስከ 2013 እ.አ.አ ተመሳሳይ ወቅት የጠፋው ግግር በረዶ በአመት በአማካይ 273 ቢሊዮን ቶን ሲሆን ይህም በአንታርክቲክ ከጠፋው ወይም ከቀለጠው በእጥፍ የሚበልጥ ነው- የማእከሉ መረጃ እንዳሰፈረው:: የሚቀልጠው ግግር በረዶ መጨረሻ ማረፊያው ባህር እና ውቅያኖስ ናቸው፤ የዓየር ንብረት ሙቀት እየጨመረ በረዶው በቀለጠ እና ባህር በገባ ቁጥር የባህሩ ከፍታ መጨመሩ አይቀሬ ነው::
በዚህም በባህር እና ውቅያኖስ ዳርቻ በሚገኙ ኗሪዎች ላይ የሚያሳርፈው ጫና ወይም ተፅእኖው ከባድ እንደሚሆን በመግለፅ ነው ጽሁፉ ያጠቃለለው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም