የመዋጥ አደጋ ያንዣበበባት

0
108

በብራዚል – አማዞን ቀጣና በምትገኘው 55 ሺህ ኗሪዎችን የያዘችው ቡሪቲኩፑ ከተማ ባለፉት ጥቂት ወራት በእጅጉ እየሰፋ በመጣው ግዙፍ ሸለቆ የመዋጥ አደጋ ያንዣበበባት መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡

የከተማዋ ባለስልጣናት እስከ አሁን ለኗሪዎች ከፍተኛ ስጋት ከፈጠሩ ቀጣናዎች 1200 ሰዎችን አስወጥተዋል:: ሆኖም የሸለቆውን እያደረ መስፋፋት ለመግታት የተወሰደ ርምጃ ባለመኖሩ መላዋን ከተማ ሊውጣት ይችላል የሚል ስጋት አስፍኗል፡፡

የቡሪቲኩፑ ከተማ አዘቅት  መጨመሩ 30 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ያስነበበው ድረ ገጹ ለመሸርሸር የተጋለጠ  አሸዋማ  አፈር፣  ረብ የለሽ የከተማ ኘላን ንድፍ እና የደን መጨፍጨፍ ለተስተዋለው  ችግር  በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የባለሙያዎች ቡድን ተዘዋውሮ ባደረገው መልከታ 26 ግዙፍ ጉድጓዶች ወይም አዘቅቶች እየተናዱ ወደ ከተማዋ እየቀረቡ መሆናቸውን ለይተው ነበር::ያንጊዜ ወይም ጉድጓዶቹን እየሰፉ ወደ ከተማዋ መጠጋታቸውን በለዩበት ወቅት ጥልቀታቸው እስከ 20 ሜትር ደርሶ እንደበር ነው የጠቆሙት – ባለሙያዎቹ፡፡

የከተማዋ አስተዳደር ወራትን እንደዘበት አሳልፎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው በያዝነው ወር የካቲት መጀመሪያ  መሆኑ በኗሪዎች ዘንድ ቅሬታን አስነስቷል፡፡

በከተማዋ በጉድጓዱ አቅራቢያ ከሚኖሩት አንዱ ናዝሬ ፊይቶሳ የአዘቅቱ ግስጋሴ አስፈሪ መሆኑን ጠቅሶ ምሽት በሚተኛበት ወቅት ዝናብ እንዳይዘንብ እንደሚፀልይ ነው ያስረዳው፤ ምነው ቢሉ? በዝናብ  የራስ ዳርቻ ተደርምሶ አዘቅቱ ውስጥ ላለመግባት፡፡

በተመሳሳይ ሌላው የከተማዋ ኗሪ ዝናቡ ከባድም ይሁን ቀላል መጣል ከጀመረ ከመናድ ወይም ተንሸራቶ ከመስመጥ ለመዳን ነቅቶ እንደሚጠባበቅ  ነው እማኝነቱን የሰጠው፡፡

ባለፉት 10 ዓመታት አዘቅቱ ሦስት ጐዳናዎችን እና 50 የሚደርሱ መኖሪያ ቤቶችን ውጧል:: የከተማዋ ችግርም ከአስተዳደሩ አቅም በላይ መሆኑን አንስተዋል- አስተያየት ሰጪዎቹ:: በመሆኑም ከስጋት ቀጣናው ለሚፈናቀሉ ኗሪዎች ከሸለቆው ራቅ ብለው ዳግም መጠለያ እንዲቀለሱ ማድረጉን እንደ መፍትሄ መፍቀዳቸው ነው በማደማደሚያነት የሰፈረው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here