ማኅበራዊ ሚዲያዎችን /Facebook, Twitter, Telegram, YouTube, WhatsApp, Viber, / በኃላፊነት ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለ በርካታ ጠቀሜታዎች ያመሆኑንሏቸው በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሕግ ምክር ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት አቃቢ ሕግ መስፍን መኮነን ለአሚኮ ገልፀዋል:: ከእነዚህም ውስጥ ዓለም አንድ መንደር እንድትሆን፣ ገዢ እና ሻጭ ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንዲገበያዩ፣ ከሌላው ዓለም ጋር አብሮ በመጓዝ ዘመናዊነትን ለመቅሰም፣ ዕውቀት ለመገብየት እና የነቃ ማኅበረሰብ ለመፍጠር፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃ ለማግኘት እና ለማሰራጨት፣ ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የማይገኙ ወይም ሲተላለፍ ያልተከታተልናቸውን መረጃዎች በቀላሉለ ለማግኘት፣ ጋዜጠኞች የማይደርሱበትን ክስተት ሰዎች በተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም ካሜራቸው በመቅረጽ ለሌሎች አካላት መረጃ ለማጋራት፣ በበይነ መረብ ሥልጠናዎችን ለማግኘት… እንደ ሚያስችሉ የሕግ ባለሙያው አብራርተዋል::
ማኅበራዊ ሚዲያዎች በርካታ ጥቅሞች እንዳሏቸው ሁሉ በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው ደግሞ የሠዎችን ክብር ይዳፈራሉ፣ ትውልዱ የኅብረተሰቡን የቆዩ ማኅበራዊ እሴቶች ሸርሽሮ የባዕድ ሀገራት ሰለባ ሊያደርጉት ይችላሉ፣ ከቤተሰብ መነጠልን እና ብቸኝነትን ያመጣል… ከዚህ ባለፈ ማኅበራዊ ኑሮ እንዲናጋ እና ሀገራዊ ሰላም እንዲታወክም ያደርጋሉ::
እንደ ባለሙያው ማበራሪያ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የበርካታ ሃይማኖት እምነት ተከታዮች እና በርካታ ቋንቋዎች ባሏት ሀገር ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በአግባቡ እና በኃላፊነት ካልተጠቀምንባቸው ጥላቻ ሊራመድባቸው ይችላል:: ይህን ተከትሎም ሀገራዊ አንድነትን በማናጋት ከችግር ፈችነት ይልቅ ችግር ፈጣሪ፣ ከልማት ይልቅ ውድመት፣ ከመደጋገፍ ይልቅ መገፋፋት፣ ከፍቅር እና ከይቅርታ ይልቅ ጥላቻን ያስከትላሉ::
ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚያስከትሉትን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመከላከል ሕግ ማውጣት አስፈልጓል:: ሕጉ የወጣበት ዓላማም ሕጉ ሊያሳካው የፈለገውን ግብ ታሳቢ አድርጐ ነው:: ሕጉ የወጣበት አስፈላጊነት ደግሞ የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ነው::
ለአብነት በጥላቻ ሕጉ በአዋጅ 1185/2012 በአንቀጽ ሰባት ንኡስ አንቀጽ አንድ “ማንኛውም ሰው የጥላቻ ንግግር ካደረገ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ የእርምት /እስራት/ ወይም ከ100 ሺህ ብር ያልበለጠ ቅጣት እንደሚወሰንበት ሰፍሯል:: በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ ሁለት ላይ በጥላቻ ንግግሩ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድኑ ጥቃት የተፈፀመ እንደሆነ ደግሞ ከአንድ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ ሕጉ ይደነግጋል:: በንኡስ አንቀጽ ሦስት ደግሞ “የሀሰት መረጃ ያሰራጨ ማንኛውም ሰው አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከ50 ሺህ ብር ባልበለጠ ይቀጣል” ይላል::
በተሰራጨው ሀሰተኛ መረጃ በግለሠብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ከተፈፀመ እንዲሁም ሁከት እና ግጭት ከተከሰተ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት እንዲቀጣ በሕግ ተደንግጓል::
ሀሰተኛ መረጃው ወይም የጥላቻ ንግግሩ ስርጭት ከአምስት ሺህ በላይ ተከታይ ባለው ማኅበራዊ ሚዲያ፣ በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የሕትመት ውጤት ከተሰራጨ ደግሞ እስከ ሦሶት ዓመት በሚደረስ እስራት እና ከ100 ሺህ ብር ያልበለጠ ቅጣት ሕጉ ይደነግጋል::
“የሰው ልጅ ሀሳቡን በነፃነት የመግለጽ በተፈጥሮ የተሰጠው መብት ነው:: ነገር ግን ማንም መሰደብ እንደማይፈልገው ሁሉ የሌላውን ክብር መንካት አይገባውም:: ይህም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 29 የተረጋገጠ መብት ነው:: ከዚህ አኳያ ማኅበራዊ ሚዲያን በቅጡ መጠቀም አለብን:: በሀገራችን ዜጎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን ከመዘላለፍ ይልቅ በጥንቃቄ ለበጐ ነገር፣ ለአንድነት… መጠቀም ይገባቸዋል” በማለት አቃቢ ሕግ ባለሙያው ምክራቸውን ለግሰዋል::
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች ዜጎችን ለሞት እና ለስደት እንደሚዳርጉ በማይናማር (በርማ) በሮሂንጂያ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ የዘርፉ ባለሙያ ለአብነት አንስተዋል:: በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚኖሩና እንደ ሀገሪቱ ዜጎች የማይቆጠሩት የሮሂንጊያ ማኅበረሰብ እ.አ.አ. በ2016 በሀገሪቱ ወታደሮች በተፈጸመባቸው ጥቃት ከአሥር ሺሕ በላይ ዜጎች ሲሞቱባቸው፣ ከ700 ሺሕ በላይ ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ በቅተዋል:: በዚች አብዛኛው ማኅበረሰብ ዜናም ሆነ ተያያዥ መረጃዎችን ከማኅበራዊ ገጾች በተለይም ከፌስቡክ እንደሚያገኝ በሚገለጽባት ሀገር በሮሂንጂያ ማኅበረሰብ ላይ በደል እንዲፈጸም ያደረገው በፊስቡክ የሚለቀቅ መረጃ ነበር::
በማይናማር የቡድሂስት መነኩሴ አሺን ዊራቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የፌስቡክ ተከታይ አሏቸው:: የተከታዮቻቸውን መብዛት ግን ለበጎ ሳይሆን የውሸት መረጃዎችን በማሠራጨት ለበርካቶች ሞት መንስዔ ሆነዋል:: እኒህ የማይናማር ቢን ላዲን በመባል የተሰየሙት መነኩሴ ለተከታዮቻቸው “ሙስሊም የሆነ አንድ ባለድርጅት አሠሪ የቡድሂስት እምነት ተከታይ የሆነችን ሴት ደፍሯል” የሚሉ የሐሰት መረጃ በማሰራጨታቸው ነበር::
በዚህ የማኅበራዊ ሚዲያዎች በተንሰራፉበት ዓለም እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ዜጐች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን መጠቀም ያለባቸው ለእድገት እና ለሰላም ነው:: ማኅበረሰቡም የሚለቀቁ መረጃዎችን እንደወረደ ከመቀበል ይልቅ ትክክለኛነቱን ማጣራት እንዳለበት የሕግ ባለሙያው አስገንዝበዋል::
(ሙሉ ዓብይ)
በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም