ሥራ በዝቶብኝ ስለዋልሁ አሥራ አንድ ሰዓት ከሩብ አካባቢ ከመሥሪያ ቤቴ ስወጣ ድክምክም ብሎኝ ነበር፡፡ እናም ወደ ቤቴ ከመሄድ ይልቅ የደከመ አእምሮየን እና አካሌን ዘና ማድረግ ፈለግሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ የመረጥሁት ምቹ ቦታ ጣና ሐይቅን ነበር፡፡ ጣና ሐይቅ ዳርቻ ቁጭ ብየ ዐይኖቼን ጣና ላይ አሳርፌ ቀዝቃዛውን አየር መሳብ እንዲሁም ሐይቁ በማዕበል ሲናጥ፣ አእዋፍ ሐይቁን አቋርጠው ሲበሩ፣ ሲዋኙ፣ ወደ ሐይቁ እየጠለቁ አሳ ሲያወጡ… ማየት ከምንም ነገር በላይ የደከመ አእምሮየን አካሌን አደሰልኝ፡፡ እናም ይህን የጣና ትርኢት ባይነ ኅሊናየ እያሰላሰልሁ ከመሥሪያ ቤቴ ወጥቼ ገጠር መንገድ ወደ ሚገኜው የታክሲ ፌርማታ በማምራት በታክሲ ተሳፈርሁ፡፡ ታክሲዋ በከተማዋ መሃል ከሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ስትደርስ ወረድሁና አስፋልቱን አቋርጬ ቁልቁል ወደ ማንጎ መናፈሻ አመራሁ፡፡
ለወትሮው ወደ ማንጎ መናፈሻ ለመግባት ፈቃደኛነቱ የሚጠየቅ ጥበቃም ሆነ ክፍያ አልነበረም፡፡ ዛሬ ግን ሁሌም በነጻነት በምንገባበት በር ላይ ሁለት የጥበቃ ሰራተኞች ቆመዋል፡፡ በሁነታቸው ግራ እንደተጋባሁ ለመግባት ወደ በሩ ስጠጋ አንደኛው “ወዴት ነው?!” አለኝ፡፡
“ወደ ጣና” አልሁት፡፡
***
አእምሮየ ሠላሣ ዓመታት ወደ ኋላ ሄዶ የጣና ሐይቅን ገጽታ እያሰላሰለ ነበር፡፡ ጥር 3 ቀን 1986 ዓ.ም. እግሮቼ ባሕር ዳርን ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጡባት ዕለት ነበረች፡፡ በወቅቱ ወደ ባሕር ዳር ያቀናሁት ላራት ዓመታት በሥነ ጽሑፍ አጥኚነት ከሠራሁበት አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ወደ ክልሉ ባህልና ስፖርት ቢሮ ተዛውሬ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆኜ እንድሠራ በመመደቤ ነበር፡፡ ከጥር 1 ቀን 1986 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ባሕር ዳር ተዛውሬ እንድሠራ የተወሰነ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ ከደረሰኝ ጀምሮ ባሕር ዳርን እስካያት ድረስ በእጅጉ ቸኩየ ሰነበትሁ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ባሕር ዳር በሀገራችን በስፋቱ አንደኛ የሆነው ጣና ሐይቅ የሚገኝባት ከተማ መሆኗ ነው፡፡ ባሕር ዳር ደርሼ ጣና ሐይቅን ለማየት እንደ ጓጓሁ የሁለት ቀን አድካሚ ያውቶቡስ ጉዞ አድርጌ ነው ጥር 3 ቀን 1986 ዓ.ም. ባሕር ዳር የገባሁት፡፡
በዕለቱ አልጋ ከያዝሁ በኋላ ትንሽ አረፍ ብየ ወደ ባሕልና ስፖርት ቢሮ ሄድሁ፡፡ አመሻሽ ላየው ወደ ጓጓሁለት ጣና ሐይቅ አመራሁ፡፡ በጊዜው የጣና ሐይቅ ዳርቻ አሁን “አቫንቲ ሆቴል” ከተሠራበት እስከ “ሌክሾር” ወይም የአልማ ሕንፃ ጀርባ ድረስ ክፍት ነበር፡፡ “አቫንቲ ሆቴል” የተሠራበት የጣና ሐይቅ ዳርቻ ያኔ በሰንሰለታማና ድንጋያማ ተራራ የተሞላ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በድንጋዩ እየተረማመዱ በመውጣት ምቹ ቦታ ሲያገኙ በመቀመጥ ጣናን እየተመለከቱ ይዝናናሉ፤ ነፋሻውን አየር እየሳቡ ዘና ይላሉ፡፡ እኔም በጣና ውበት በእጅጉ እየተደመምሁ ድንጋያማውን ተራራ ወጥቼ ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ ቁጭ አልሁ፡፡ ጣና በማዕበል ይታረሳል፤ አእዋፍ ጣናን እያቆራረጡ በተለያየ አቅጣጫ ወደ ማደሪያቸው ይበራሉ፤ ባለታንኳዎች ታንኳቸውን እየቀዘፉ ከዘጌና አካባቢዋ ወደ ባሕር ዳር ይገሰግሳሉ፤ ፔሊካን የተሰኙ ነጫጭ የወፍ ዝርያዎች በጣና ላይ ይዋኛሉ፤ ልዩ ልዩ ወፎች አሳ ለመያዝ ወደ ሐይቁ ይጠልቃሉ፤ ይወጣሉ፡፡ ዐይኖቼን ጣና ላይ እንደተከልሁ ይህን ሁሉ ትርኢት ባድናቆት ስመለከት ከቆየሁ በኋላ ጀምበር ላይን ያዝ ማድረግ ስትጀምር ጣናን አይቼ ሳልጠግበው ወደ ቤቴ እሄዳለሁ፡፡ ሆኖም እግሮቼ ወደ ቤት ያምሩ እንጂ፣ በእግረ ኅሊናየ ጣናን እየተመለከትሁ እያደነቅሁ ነበር፡፡
ከዚያች ዕለት ጀምሮ የሥራ ቀን ከሆነ ከሥራ ስወጣ እንዲሁም ቅዳሜ እና እሑድ ከሆነም በጧት ከቤቴ እየወጣሁ የጣናን ዳርቻ ይዤ መንሸራሸርን፣ ጣናን እያደነቅሁ በሥራ የደከመ አካል እና አእምሮየን ማሳረፍን ልማድ አደረግሁት፡፡ ይሁን እንጂ፣ በጊዜ ሂደት ጣናን አይቼ ሳልጠግበው ክፍት የነበረው ዳርቻ እየታጠረ፣ ሕንጻዎች እየተገነቡበት… እየተዘጋጋ ይሄድ ጀመር፡፡ እኔም ሳልወድ በግድ ከጣና እየራቅሁ መጣሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ነው እንግዲህ ወደ ማንጎ መናፈሻ የሄድሁት፡፡
***
ጣና በፈለግን ጊዜ እንጎበኜው፣ ጎብኝተንም ዘና እንል ዘንድ… ፈጣሪ የሰጠን ሀብታችን ሆኖ ሳለ ዙሪያዉ እየታጠረ በነጻነት እንዳንጎበኜው መከልከላችን እያሳዘነኝ ባለበት ወቅት የካቲት 2017 ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ እግሮቼ እንደቀልድ ወደ ማንጎ መናፈሻ ወሰዱኝ፤ በዚህ ጊዜ እንደ ሕጻን ልጅ ያስፈነደቀኝን ግሩም ክስተት ተመለከትሁ፡፡ ካመታት በፊት ዳርቻው ታጥሮ እንደልብ ማየት የናፈቀኝን ጣናን የዳርቻው አጥር ፈራርሷል፤ ጣና በሰፊው ፍንትው ብሎ ይታያል፤ ሰው ወደ ውስጥ በማምራት ጣናን እንደ ልቡ እያየ ይዝናናል፤ ንጹሕ አየር ወደ ባሕር ዳር ይነፍሳል፤ ሕዝቡ ጣና ዳር ቆሞ እንዲሁም ቁጭ ብሎ ጣናን ያለከልካይ ማየት በመቻሉ ደስታውን ሲገልጽ ይሰማል፡፡
እኔም ውስጤ በሀሴት እንደተሞላ ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ካሉት አንድ ጎልማሳ አጠገብ ቁጭ አልሁ፡፡ ከዚያም በደስታ ስሜት እንደተዋጥሁ ከሰውየው ጋር ሞቅ ያለ ወሬ ጀመርን፡፡ በወሬያችን መሀል ሰውየው፣ “የሚገርመው እኮ ጣናን እያጠረ የጣናን ነፋስ አፍኖ በመያዝ ባሕር ዳርን ለሙቀት የሚዳርገው ምድረ የጣና ዳር ነጋዴ ጣናን የገቢ ማግኛየ ነው፤ ጣና ከሌለ ገቢ ማግኜት አልችልም ብሎ ለጣና ደኅንነት ሲጠነቀቅ አይታይም፡፡ ጣናን ከማጠሩና ሕዝቡ ፈጣሪ የሰጠውን ጸጋ እንደልቡ እንዳይጎበኝ ከመከልከሉም በላይ ደረቅም ይሁን ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ጣና እየለቀቀ የሐይቁን ኅልውና እየተፈታተነ ነው፡፡ እሱ የሚያየው የዕለት ገቢውን ብቻ ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ሰነዘሩ፡፡
እኔም፣ “ምን ይሄ ብቻ! በጣና ዳርቻ ላይ ሕንጻዎች በተገነቡና የጣና ዳርቻ በታጠረ ቁጥር ሐይቁ ስለሚደርቅ እየሸሸ መሄዱ አይቀርም” ስል ስጋት አዘል አስተያየቴን ሰነዘርሁ፡፡
ጎልማሳውም፣ “እውነት ነው ወዳጄ፤ የሰው እግር መጥፎ ነው፤ ሐይቁን ሊያደርቀው ይችላል” ሲሉ ሀሳቤን አጠናከሩልኝ፡፡
“ትልቁ ችግር የግንዛቤ ማነስ ነው፤ ለግንባታ የሚሰጡትም ሆነ የሚቀበሉት ሰዎች የጣናን ዳርቻ እያጠሩ የንግድ ቦታ በማድረግ ገቢ ማግኜታቸውን እንጂ ለሐይቁ ኅልውና ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ አይረዱም” ስል የበኩሌን ሀሳብ ሰነዘርሁ፡፡
ጎልማሳውም ይህን የሚያደርጉ ሰዎች፣ “እኔ ከሞትሁ…” እንዳለችው እንስሳ እየሆኑ እንጂ ችግሩን ሳይረዱት የሚቀሩ አይመስለኝም አሉኝ፡፡ ጎልማሳው ይህን ሲሉኝ አንድ ገጠመኝ አስታወሱኝ፤ ከሁለት ወራት በፊት ይመስለኛል፡፡ በጣና ሐይቅ ዳርቻ እንዲሁም ከዳርቻው አልፈው ወደ ውስጥ በመዝለቅ ግንባታ በሚያካሂዱት ቦታ አንዱን ጠጋ ብየ፣ “ጣና ዳር ለመናፈሻ የሚሆን ሕንጻ የሚገነባው ጣናን ተማምኖ ነው፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው የሚገነቡት የጣና ዳር መናፈሻ እንደታሰበው ጎብኝዎችን ወይም የሚዝናኑ ሰዎችን በመሳብ የገቢ ምንጭ ሊሆን የሚችለው ጣና እስካለ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ጣና ባሁኑ ሰዓት በተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች እየተፈተነ ነው” ብየ ንግግሬን ልቀጥል ስል ግለሰቡ፣ “ጣና ምንም ፈተና አልገጠመውም” አሉኝ፡፡
በዚህ ጊዜ፣ “ለመሆኑ ስለእምቦጭ ሰምተው ያውቃሉ? ስል ጥያቄ አስከተልሁ፡፡
እምቦጭ ወደዚህ እንዳይመጣ የመናፈሻዎቹን አካባቢ እየተንከባከቡ እንደሆነ መለሱልኝ፡፡ንግግራቸዉ በሚቃጠል ጫካ መሀል ኩሬ ውስጥ ሆና ጓደኛዋ ጫካው እየተቃጠለ ነው፤ እናምልጥ ስትላት እኔ ያለሁት ኩሬ ውስጥ ነው፤ ምንም አልሆንም ያለችውንና በኋላ ከውኃው ጋር ተጠልቃ የእሳት ማጥፊያ የሆነችውን እንቁራሪት አሳዛኝ ዕጣ አስታወሰኝና ሳልወድ በግድ ፈገግ አልሁ፡፡
የሰውየው ምላሽ ባለሀብቱ ጣናን ለጥቅሙ ሲል ዙሪያውን እያጠረ ግንባታውን ያጧጡፍ እንጂ አንድም ቀን ደኅንነቱ አሳስቦት፣ ሕመሙ አሞት… እንደማያውቅ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ የጣናን ሕመም ዘንግተን ለዕለት ጥቅማችን የምናደርገው እንዲህ ዓይነቱ ሩጫ ጣናን ሊያሳጣንና የእኛን ሩጫም ከንቱ ሊያደርግብን የሚችል አደገኛ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም እንዲህ ዓይነቱ አጓጉል ተግባር ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት ከወዲሁ አጢነን ለጣና ኅልውና መረጋገጥ ሁላችንም ልንጥር የገባናል፡፡ የጣና ሐይቅ ዳርቻን ክፍት ማድረግ ደግሞ ለጣና ኅልውና መረጋገጥ ልንወስዳቸው ከሚገቡን ርምጃዎች አንዱና ቀዳሚው ነው፡፡ ይህን ወሳኝ ርምጃ ደግሞ መንግሥት የተዘጋውን የጣና ዳርቻ በመክፈት ጀምሮታል፡፡ በአማራ ልማት ማኅበር ሕንጻ በኩልም የሐይቁን ዳርቻ ክፍት የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
የእነዚህ ሁለት ዳርቻዎች መከፈት ካይናችን እየራቀብንና አደጋ ተጋርጦበት የነበረውን ውዱን የተፈጥሮ ስጦታችንን ጣናን እንድናይ እንዲሁም በዳርቻዎቹ አረፍ ብለን ንጹሕ አየር እየሳብን አእምሮ እና አካላችንን ዘና እናደርግ ዘንድ ዕድል የሚሰጥ፣ ለሐይቁ ኅልውናም የሚበጅ መልካም ጅምር በመሆኑ የዚህን መልካም ተግባር ባለቤቶች እናመሰግናለን፤ ይህ መልካም ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተስፋ እናደርጋለን፡፡
(ቦረቦር ዘዳር አገር)
በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም