የኮሪደር ልማት እመርታ

0
578

የመንገድ ኮሪደር ልማት በዓለማችን አያሌ ውድ እና ውብ ዘመናዊ ከተሞችን ፈጥሯል። በኮሪደር ልማት ከተሞች ማሕበራዊ ግንኙነታቸውን ማጠናከር፣ የእግረኞችን ደህንነት እንዲጠበቅ እና ንፁህ አየር እንዲነፍስ ማድረግ ተችሏል።

ለአብነት በሲንጋፖር የመንገድ ኮሪደር ልማት ከሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ሥርዓት ጋር ተዋህዶ የተነደፈ ነው። የኮሪደር ልማቱ ዘላቂ ልማት የሰፈነበት እና ለኑሮ ምቹ ከተማን እውን ማድረግን ያለመው ሰፊውን የከተማ ንድፍ አካል ነው። በሲንጋፖር የመንገድ ዳር ኮሪደሮቿ ባቡሮችን፣ አውቶቡሶችን እና ታክሲዎችን ጨምሮ የወንዝ ላይ ማመላለሻ አውታሮች ጋር ያለአንዳች ችግር ተዋህዷል። አካባቢው አረንጓዴ ገጽታ እና መንገዶቹም በእነዚህ ዛፎች አጊጠዋል።

ከወደ አውሮፓ የዴንማርክ መናገሻ የሆነችው ኮፐንሀገን በመንገድ ኮሪደር ልማት ተሞክሮ በአብነት ትነሳለች። ዘርፉ እንደ የብስክሌት ግልቢያ እና የእግር ጉዞ ላሉ ዘላቂ የትራንስፖርት አይነቶች ትኩረት የሰጠ ነው። ልማቱ ለእግረኛ ደህንነትም ቅድሚያ ይሰጣል። የብስክሌት መስመሮች ዝርጋታን እና የሕዝብ ማመላለሻ መቀላጠፍን እና የእግረኛ ደህንነትን ያስቀደመ ነው።

የኮፐንሀገን ከተማ ኮሪደሮቿ በትራፊክ ማረጋጊያ ምልክቶቻቸው ይታወቃሉ፤ የፍጥነት ቅነሳ ገደቦችን እና ውበትን የተላበሱ አደባባዮችን የመሳሰሉ ምልክቶችን ያሳያሉ። ይህም ይበልጥ ተደራሽ የሆነ የከተማ አካባቢን ለመፍጠር ያግዛል። እነዚህን ለአብነት አነሳን እንጅ በርካታ ከተሞች በዚህ ልማት ብዙ ተሞክሮ አላችው።

በሀገራችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተሞቻችን ከፍተኛ የመንገድ ኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ እየተከናወነ ይገኛል። በአዲስ አበባ የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋን እንደ ስሟ ውብ እና ሳቢ እያደረጓት ይገኛሉ።

የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲሁም የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን እንድታስተናግድ ይበልጥ ተመራጭ እያደረጓት ነው።

የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት በተለያዩ ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ዘላቂ የከተሞች ዕድገትን እና ትስስርን የሚፈጥር ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የኢትዮጵያን ከተሞች ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ የከተማ መሠረተ ልማቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ከዚህም ውስጥ የኮሪደር ልማት ተጠቃሽ ሲሆን፤ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በ31 ከተሞች እየተከናወነ ነው፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሮ ወደ ሌሎች ከተሞች የሰፋው የኮሪደር ልማት ሥራ ከተሞችን ለኑሮ ተስማሚ የሚያደርግ ነው፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ የኮሪደር ልማቱ ከተሞች ዘላቂ የሆነ ፕላን እንዲኖራቸው በማድረግ በየጊዜው ለማስፋት ሲባል የማፍረስ ሂደቶችን ያስቀራል፡፡ በተጨማሪም ዘመናዊ እና ስማርት ከተሞችን በመፍጠር ዘላቂ የከተሞች ዕድገትና ትስስርን የሚያሳልጥ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ከተሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከተሞች በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሠራርን እንዲከተሉ ከማድረጉም ባሻገር ንጹህ እና አረንጓዴ ገጽታ እንዲላበሱ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

በከተሞች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ አካታች የልማት ስራ እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከኮሪደር ልማት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ከተሞችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች  እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ዜጎች በልማት ሥራዎች ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ እንዲነቃቃ እያደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ታዲያ ይህን የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የክልል ከተሞችም ልምድ እየቀሰሙበት የሚገኝ፣ ለክልሎች መነቃቃት የፈጠረ ትልቅ ፕሮጀክት ሆኗል። በአማራ ክልል በባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ሌሎች ከተሞች የተጀመሩት የመንገድ ኮሪደር ልማት እንቅስቃሴዎች ለዚህ ማሳያ ናቸው።

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ ተሻገር አዳሙ እንደተናገሩት ከተማዋን ተጨማሪ ውበት ለማላበስ ይህ የኮሪደር ልማት ትልቅ አቅም እንደሆነ መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

የባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆኗ አንጻር የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ዋና ዋና ቦታዎችን እንዲያገናኝ ታስቦ እየተከናወነ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የአካባቢ ነዋሪዎችን እና ሰው ተኮር የኮሪደር ልማትን መሥራት አስፈላጊነት ነው። ይህንኑ ሐሳብ በማጠናከር በአማራ ክልል እየተሠሩ ስላሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ሐሳብ የሰጡት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን ሙሀመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የኮሪደር ልማቱ በሁሉም ሪጅኦፖሊታን ከተሞች መጀመሩን እና በባሕር ዳር ደግሞ የምሽቱን ጨምሮ በቀን 18 ሰዓት እየተሠራ ነው፤ በቀጣይም ወደ 24 ሰዓት ያድጋል፤ ሌሎች ከተሞችም በቀጣይ ይሠሩበታል ብለዋል።

በክልሉ 47 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር መንገድ እና 7 ነጥብ 6 ሔክታር አረንጓዴ ልማት የኮሪደር ሥራ ለመሥራት መታቀዱን ገልጸዋል።

ሥራውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በፍጥነት እየተሠራ ነው። የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመፍታት እና የከተሞችን የረጂም ጊዜ የእድገት ህልም ታሳቢ ያደረገ ሥራ ነው። ኅብረተሰቡ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ እና በዕውቀቱ እንዲሳተፍ ይደረጋል። ወጣቶች የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑም የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

ዶክተር አህመዲን እንዳሉት ልማቱ መላ ኅብረተሰቡ የሚጠቀምበት እንዲሆን ተደርጎ ነው የሚከናወነው፤ ይህም ሰው ተኮር ያደርገዋል።

በዋና ዋና ከተሞች የተጀመረው የኮሪደር ልማት ወደ ገጠሩ አካባቢም እንደሚስፋፋ ተነግሯል፤ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በሀገር ደረጃ እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት የኅብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ የሚቀይር፣ የተቀናጀ የመሠረተ ልማትን የሚያሟላ፣ የትራንስፖርት ፍሰትን የሚያሳልጥ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድልን የሚፈጥር እና ሌሎችንም ዓላማዎች ይዞ እየተተገበረ ያለው ሰው ተኮር ፕሮጀክት ወደ ገጠር አካባቢዎችም እንደሚስፋፋ ተናግረዋል።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here