ኢትዮጵያ ባላት መሬት ልክ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ፣ በዓለም ገበያም ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በስፋት ለማምረት ለአፈር ማዳበሪያ ከፍተኛ ወጪ ታደርጋለች:: ለአብነት መንግሥት ለ2017/18 የምርት ዘመን የሚያስፈልገውን 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ 84 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን የግብርና ሚኒስቴር የጥር 30 መግለጫ ይጠቁማል::
ምንም እንኳ ይህ ከፍተኛ ድጎማ ሀገርን በምጣኔ ሐብት ከፍ ለማድረግ የወጣ ቢሆንም የታለመለትን ዓላማ እንዳያሳካ የሚያደርጉ ክስተቶች ግን ይስተዋላሉ:: የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከዓመት ዓመት መጨመር አንደኛው ተግዳሮት ነው:: ይህም አርሶ አደሩ በግብርና ምክረ ሀሳብ መሠረት የአፈር ለምነት ማስጠበቂያ ግብዓትን እንዳይጠቀም ያደርገዋል:: በዚህም የምርት መቀነስ ሊከሰት ይችላል:: ይህን ተከትሎም በዜጎች የምግብ ዋስትና ላይ ሊፈጥር የሚችለውን የምግብ ክፍተት ለመሙላት ሀገሪቱን ለሌላ ተጨማሪ ወጪ ይዳርጋታል::
የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ስርጭት መዘግየት እና መቆራረጥ ሌላው ፈተና ሆኖ ይነሳል:: መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የሚያስገባው የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ከአርሶ አደሩ እጅ እንዳይደርስ የሰላም መደፍረስ ቀዳሚው መሰናክል ሆኖ ይነሳል::
የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር በ2017/18 የምርት ዘመን ከ406 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በተለያዩ ሰብሎች ይሸፍናል:: 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ ደግሞ ዋና ግቡ መሆኑን የግብርና መምሪያው ምክትል ኃላፊ አዲሱ ስማቸው አስታውቀዋል::
ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያን ከተፈጥሮ ማዳበሪያ ጋር አቀናጅቶ መጠቀምን ለተባለው ምርት ማሳኪያ አድርጎ እየሠራ መሆኑን መምሪያ ኃላፊው ገልጸዋል:: በዓመቱ በዘር ለሚሸፍነው አጠቃላይ መሬት 856 ሺህ 660 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግም ተመላክቷል::
አቶ አዲሱ ይህንን ቃለ መጠይቅ ከበኵር ጋዜጣ ጋር በስልክ እስካደረጉበት ጊዜ ድረስ 171 ሺህ 51 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ብሄረሰብ አስተዳደሩ ገብቷል:: ከዚህም ውስጥ 60 ሺህ 843 ኩንታል የሚሆነው ወደ ቀበሌ እና መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማጓጓዝ ተችሏል::
እንደ መምሪያ ኃላፊዉ ማብራሪያ በክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ አሁንም የልማት እንቅፋት ሆኖ እንዳይቀጥል መሥራት ይገባል:: በተለይ የጸጥታ ችግሩ እንደ አፈር ማዳበሪያ ያሉ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ላይ ተጽእኖ ፈጥሮ በምርታማነት ላይ አሉታዊ ጫና እንዳይፈጥር ከመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው::
እስካሁንም በተደረገው የአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ ሂደት ያጋጠመ መስተጓጎል አለመኖሩን አስታውቀዋል። ያም ሆኖ ችግሩ አሁንም የግብርና ግብዓትን ወደ አርሶ አደሩ ለማሰራጨት በሚደረገው ጥረት መስተጓጎል እንዳይፈጠር ከኅብረት ሥራ ማኅበራት አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን አስታውቀዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ክፍያው ቀድሞ እንዲሰበሰብ በማድረግ አርሶ አደሮች ቀድሞ እንዲደርሳቸው ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
የአፈር ማዳበሪያ በዓለም አቀፍ ገበያ የሚዘወር መሆኑ፣ የማጓጓዣ ወጪ፣ የነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ከፍ ማለት በአፈር ማዳበሪያ ላይ ለታየው የዋጋ ጭማሪ ምክንያቶች ናቸው:: ዋጋ ጭማሪውም የአርሶ አደሩን የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት እንዳይገድበው ቀድሞ የማሳወቅ እና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሠራቱን ተጠቁሟል:: በተጨማሪም የአቅርቦት መጠኑን እና የስርጭት ሂደቱን አስመልክቶ ለ35 ሺህ አርሶ አደሮች ግንዛቤ መፈጠሩ ተመላክቷል::
የአርሶ አደሩ ዋነኛ ጥያቄዎች በቂ አቅርቦት፣ ፍትሐዊ ስርጭት እና በሚፈለገው ወቅት ስርጭቱ እንዲከናወን መሆኑን አቶ አዲሱ አስታውቀዋል:: ስርጭቱ ከመጋቢት አንድ ቀን ጀምሮ በብሄረሰብ አስተዳደሩ ሁሉም አካባቢዎች እንደሚጀመር አረጋግጠዋል።
ጃዊ፣ ዚገም እና አየሁ ጓጉሳ ወረዳዎች የብሄረሰብ አስተዳደሩን የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት አንድ ሦስተኛ ድርሻ የሚወስዱ አካባቢዎች ናቸው:: ለእነዚህ ወረዳዎች እና ከፍተኛ የዝናብ መጠን ለሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የአፈር ማዳበሪያን ቀድሞ ለማሰራጨት ትኩረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል::
ብሄረሰብ አስተዳደሩ የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያን የአቅርቦት እና የዋጋ ንረት ለማቃለል በዓመቱ አምስት ነጥብ 188 ሚሊዮን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ዕቅድ ነበረው:: በተጨባጭ አራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሜትር ኩብ ኮምፖስት ማዘጋጀት መቻሉን አቶ አዲሱ ጠቁመዋል:: ይህም የተፈጥሮ ማዳበሪያ 163 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው::
‘ቨርሚ’ ኮምፖስትን ሌላው የአፈር ለምነት መመለሻ፣ የምርታማነት መሠረት አድርጎ ለመጠቀም እየተሠራ መሆኑም ተጠቁሟል:: “ቨርሚ” ገለባ፣ የእንስሳት ፍግ፣ አፈር፣ ቅጠላ ቅጠሎችን እና ተረፈ ምርቶችን በትሎች (worm) አማካኝነት በአጭር ጊዜ እንዲበሰብስ በማድረግ የሚዘጋጅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አይነት ነው::
በብሄረሰብ አስተዳደሩ 17 ሺህ 800 ኩንታል ቨርሚ ለማምረት ታቅዶ እስካሁን 19 ሺህ 812 ኩንታል ማዘጋጀት መቻሉን አቶ አዲሱ ገልጸዋል:: የተፈጥሮ ማዳበሪያን ከባዮ ጋዝ በማዘጋጀት አማራጭን ማስፋት ተችሏል:: ከባዮ ጋዝ 18 ሺህ 324 ሜትር ኩብ ባዮ ሳለሪ ማምረት መቻሉንም አስታውቀዋል::
ከአንድ ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬትን በኖራ ለማከም ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም አቶ አዲሡ አስታውቀዋል:: ለዚህም የሚያስፈልገው የ45 ሺህ ኩንታል ኖራ ግዢ ተፈጽሞ የትራንስፖርት ጨረታ መውጣቱን አስታውቀዋል::
የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ከአቅርቦት እጥረት፣ በወቅቱ ካለመቅረብ እና ከዋጋ መናር ጋር በተገናኘ ሊፈጠር ከሚችል ችግር ለመውጣት አርሶ አደሮችም እንደ መውጫ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው:: በሰሜን ወሎ ዞን የዋድላ ወረዳ ነዋሪው አቶ ወርቁ ቢምር በበኩላቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት እንደሚያመርቱ ተናግረዋል:: የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከወጪ አኳያ ያገኙትን ጥቅም በመረዳታቸው በየዓመቱ በከፍተኛ ደረጃ እያመረቱ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል:: የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ዋጋ እየጨመረ ባለበት ወቅት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ሁነኛ መፍትሔ ሆኖ ማግኘታቸውንም አስረድተዋል:: ዞኑም ከአራት ሚሊዮን በላይ ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ዕቅድ ይዞ እየሠራ ይገኛል::
በ2015/16 የምርት ዘመን በዝናብ እጥረት ምክንያት ለድርቅ ከተጋለጡ ዘጠኝ ዞኖች ውስጥ አንደኛው የሰሜን ጎንደር ዞን ነው:: በእርግጥ ዞኑ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም ድረስ በቀጠለው ክልላዊ ቀውስ ከእርሻ እስከ ምርት ሲፈተን ቆይቷል::
በ2016/17 የምርት ዘመን ያጋጠመው የዝናብ መብዛት እና የመሬት መንሸራተት ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ የምርታማነት ፈተናዎችን ለመሻገር ፈተና ሆኖ መስተዋሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አዳነ አስታውቀዋል::
ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች እየፈጠሩት ያለውን የሰብል ምርት ክፍተት ለመሙላት የ2017/18 የምርት ዘመን ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል:: ምርታማነትን ማረጋገጥ ዋናው መውጫ መንገድ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ለዚህም ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያን አቀናጅቶ መጠቀም እንዲሁም የአፈር አሲዳማነትን ማከም ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ብለዋል::
በሰሜን ጎንደር ዞን ለ2017/18 የምርት ዘመን 151 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የሚያስፈልግ ቢሆንም በመንግሥት በኩል ግዢ የተፈጸመው 100 ሺህ ኩንታል መሆኑን አስታውቀዋል:: አቶ ጌታቸው ይህን ቃለ መጠይቅ እስካደረጉበት የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጊዜ ድረስ 27 ሺህ 596 ኩንታል የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዞኑ ገብቷል:: ባለፉት ዓመታት የአፈር ማዳበሪያ ይቀርብ የነበረው በአብዛኛው የዘር ሥራ በተጀመረበት ወቅት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፣ የዚህ ዓመት ግን ቀድሞ መጀመሩን አስታውቀዋል:: ይህም አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውን ረድቶታል ብለዋል::
የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ከመጋቢት 5 ቀን ጀምሮ እንደሚጀመር አስታውቀዋል:: በአሁኑ ወቅት የዋጋ ጭማሪውን የማሳወቅ እና የማስረዳት ሥራ እየተሠራ ነው::
አማራጭ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠን እና በጥራት ከፍ አድርጎ በማምረት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራም ይገኛል:: በዚህ ዓመት ሦስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት የታቀደ ቢሆንም ማሳካት የተቻለው አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሜትር ኩብ መሆኑን አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል:: ለዕቅዱ አለመሳካት ዋናው ምክንያት በጸጥታው ችግር ምክንያት የሁለት ወረዳዎች የማዘጋጃ ጊዜ በማለፉ ነው ተብሏል::
በአጠቃላይ አሁን ላይ እየተከናወኑ ያሉ የመኸር እርሻ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የዞኑን ዓመታዊ ምርታማነት ሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ያደርሰዋል ተብሎ ይታሰባል::
ክልሉ ለተያዘው ዓመት ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ለማቅረብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ አስታወቁ:: ለዚህም ከ79 ቢሊዮን ብር በላይ ዋስትና መገባቱን አቶ አረጋ ያስታወቁት የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ነው:: ለአፈር ማዳበሪያ የወጣው የገንዘብ መጠን በክልል ደረጃ ለመሰብሰብ ከታሰበው ገቢ ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑም አንስተዋል::
መንግሥት ግብርናን በከፍተኛ በጀት እየደገፈ መሆኑን ርእሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል:: በመሆኑም አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም ከገባበት መደናገር ወጥቶ በቤተሰብ ደረጃ ያለውን ኢኮኖሚ ሊያሳድግ በሚያስችልበት ደረጃ ማንቃት፣ ማዘጋጀት እና ማንቀሳቀስ የቀጣይ ጊዜያት ትኩረቶች ሊሆኑ እንደሚገባ ርእሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል:: ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር እና ባለሙያ ሰበብ ሳይፈጥር በትኩረት መደገፍ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል::
የማሪታይም ትራዚት አገልግሎት (MTS) ጅቡቲ ጽሕፈት ቤት እለታዊ የማዳበሪያ ኦፕሬሽን መረጃ እንደሚያመለክተው እስከ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ከሰባት ሚሊዮን በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ደርሷል:: ከዚህም ውስጥ ከስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚሆነው ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን አስታውቋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም