የግብዓት አቅርቦት ለነገ የማይባል ተግባር ነው!

0
104

ኢትዮጵያ  የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ እና በዓለም ገበያ ተፈላጊ  ምርቶችን በስፋት ለማምረት ለአፈር  ማዳበሪያ ከፍተኛ ወጪ በየጊዜዉ   ታወጣለች፡፡ ለአብነት መንግሥት ለ2017/18 የምርት ዘመን የሚያስፈልገውን 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ 84 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን የግብርና ሚኒስቴር የጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም መግለጫ ይጠቁማል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከዓመት ዓመት እየጨመረ በመሆኑ  አርሶ አደሩ  የአፈር ለምነት ማስጠበቂያ ግብዓትን እንዳይጠቀም ሊያደርገዉ ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ እያደር የምርት መቀነስን ሊያስከትል ይችላል ፡፡

የምርት መቀነስም በዜጎች የምግብ ዋስትና ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል፤ የተከሰተውን የምግብ ክፍተት ለመሙላትም ሀገሪቱን ለሌላ ተጨማሪ ወጪ ሊዳርጋት ይችላል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በተለያዩ ምክንያቶች ይፈጠራል፤ ከምክንያቶች መካከልም የሰላም ጉዳይ ዋነኛው ነው፡፡ በመሆኑም  በክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ አሁንም የልማት እንቅፋት ሆኖ እንዳይቀጥል በጋራ መሥራት ይገባል፡፡ በተለይ የጸጥታ ችግሩ እንደ አፈር ማዳበሪያ ያሉ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ላይ ተጽእኖ ፈጥሮ በምርታማነት ላይ አሉታዊ ጫና እንዳይፈጥር ከመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በቅንጅት መሥራት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው፡፡

የአፈር ማዳበሪያ በዓለም አቀፍ ገበያ የሚዘወር በመሆኑ፣ የመጓጓዣ/ትራንስፖርት/ ወጪ፣ የነዳጅ  እና የውጪ ምንዛሪ ዋጋ ከፍ ማለት በአፈር ማዳበሪያ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲስተዋል ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ይህ የዋጋ ጭማሪ የአርሶ አደሩን የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት እንዳይገድበው በማጤን ቀድሞ ማሳወቅ እና ግንዛቤ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡

የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ዋጋ በሚጨምርበት ወቅት የተፈጥሮ ማዳበሪያን ሁነኛ መፍትሔ አድርጎ መወሰድም ይገባል፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በሰው  ሠራሽ ማዳበሪያ ከሚፈጥረው የአቅርቦት እጥረት፣  በወቅቱ ካለመቅረብ እና ከዋጋ መናር ጋር በተገናኘ ሊፈጠር ከሚችል ችግር ለመውጣት እንደ መውጫ መንገድ መጠቀም ተገቢ እና አዋጭ ነው፡፡

በተፈጥሮ መንገድ ከሚሠሩ አፈር ማዳበሪያዎች መካከል ‘ቨርሚ’ ኮምፖስት በማዘጋጀት እና በመጠቀም ወጪን መቀነስ እንደሚቻል እና የአፈር ለምነትን ለመመለስ እንደሚያግዝ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይጠቁማሉ፡፡ “ቨርሚ” ገለባን፣ የእንስሳትን ፍግ፣ አፈርን፣ ቅጠላ ቅጠሎችን እና ተረፈ ምርቶችን በትሎች (worm) አማካኝነት በአጭር ጊዜ እንዲበሰብስ በማድረግ የሚዘጋጅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አይነት ነው፡፡

በሌላ በኩል የተፈጥሮ ማዳበሪያን ከባዮ ጋዝ በማዘጋጀት አማራጭን ማስፋት ይቻላል፡፡ አማራጭ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠን እና በጥራት ከፍ አድርጎ በማምረት ምርታማነትን ለማሳደግ በሚሠራዉ ሥራ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ይፈልጋል፡፡

አሲዳማ አፈርም በክልሉ  እየተስፋፋ በመሆኑ ምርታማነት እየቀነሰ ነው፡፡ በመሆኑም ምርታማነትን ለመጨመር እና በምግብ ራስን ለመቻል  አፈርን በኖራ ማከም ሌላው አዋጪ መንገድ ነው፡፡

በየደረጃው ያለ አመራር እና ባለሙያ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ እንዲያገኝ እና ምርታማነቱን እንዲያሻሽል ማነቃቃት ይገባል፡፡ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያን በስፋት አዘጋጅቶ እንዲጠቀም መቀስቀስም ተገቢ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ አጠቃቀም ለመውጣት እንዲያስብ እና እንዲዘጋጅ በትኩረት መደገፍ ለነገ የማይባል ሁነኛ ተግባር ነው፡፡

በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here